የኢትዮ-አሜሪካዊው ጦማሪ ቃላት ወይስ የአትዮጵያ ልጅ የፅሁፍ ማስታዎሻዎች?

ከፕሮፌሰር አለማየሁ ገብረማርያም

ትርጉም በነጻነት ለሀገሬ

ይህ ትቸት ምናልባትም  የጦማሪ ቃላት ብለው እስከ አሁን ድረስ ከነበሩት ትችቶች ሁሉ የበለጠ ገላጭ እና ረዥም ነው፡፡ ለምንድን ነው በመቶዎች ለሚቆጠሩ ሳምንቶች በየሳምንቱ ሰኞ፣ ሰኞ ረዥም ትችቶችን የምጽፍ? የእኔ ትችቶች “በጣም ረዥም” የሚሆኑት ለምንድን ነው? በኢትዮጵያ ባለው ገዥ አካል ቡድንና መሪ እና አሁን በህይወት በሌለው በመለስ ዜናዊ ፖሊሲዎች እና የማስፈጸሚያ ስልቶች ላይ ጠንከር ያለ ትችት የማቀርበው ለምንድን ነው? በየሳምንቱ ከማዘጋጃቸው ትችቶቼ ምንን አሳካሁ ብዬ እጠብቃለሁ? ለምን እና ምንድን ነው የማደርገው? ባለፉት በርካታ ዓመታት እነዚህ እና የመሳሰሉትን ዓይነት ጥያቄዎች ስሰማ ቆይቻለሁ፡፡ የረጅም ጊዜ አንባቢዎቼ እውነትነት፣ ታማኝነት፣ ቀጥተኛ የሆኑ መልሶች ለነዚህ ጥያቄዎች ከኔ ማግኘት መብታቸው ነው::

የመጀመሪያ የማብራሪያ ነጥብ፡ ትችቶችን በየሳምንቱ የምጽፍ ቢሆንም እራሴን በጨቋኝ አገዛዝ ላይ የታሪክ ድርሳናት እና የፖለቲካ መጣጥፍ ደራሲ ሰው አድርጌ እቆጥረዋለሁ፡፡ “ከጡመራ ዘመን” በፊት በወንዶች (አንዳንድ ጊዜም በጥቂት ሴቶች) ጠንካራ የሆኑ ሀሳቦችን በማፍለቅ በጊዚያቸው የተመለከቷቸውን ሀሳቦች በማንሸራሸር የታሪክ ድርሳናትን እና የፖለቲካ መጣጥፎችን በመጻፍ በጊዚያቸው የነበሩትን ምልከታዎች በመክተብ ለመጭው ትውልድ የማስተላለፍ ባህል በየቦታው በዓለም ዉስጥ ነበር :: እንደዚሁም ሁሉ የእኔ ሳምንታዊ መጣጥፎቸችም በዚያ በጊዜ ብዛት በነበረ የተከበረ ባህል ላይ መሰረት በማድረግ የዘመኑን ቴክኖሎጂ በመጠቀም እየጻፍኩ እንዳለሁ እገነዘባለሁ፡፡ የእኔን የትችት መጣጥፎች “የጡመራ ጽሑፎች” (ስለስያሜ ወደፊት የምመለስበት ይሆናል) ብዬ ለመጥራት እመርጣለሁ፡፡ የእኔ የጡመራ ጽሑፎች ለአሁኑ የኢትዮጵያ ትውልድ እና ለመጭውም ትውልድ ጭምር በዘመናችን የነበረውን ከአንድ ሰው እይታ አንጻር ምስቅልቅል ያለ ደንቆሮ የጨቋኝ እና የአምባገነን ስርዓትን በማጋለጥ እውነትን በመናገር እና በመጻፍ ለአዲሱ ትውልድ መረጃን አሰጣለሁ፡፡

በጡመራ ስራው ላይ እራሴን ለምን እንዳስገባሁ ግልጽ ላድርግ::  እ.ኤ.አ በ1990 የመጀመሪያዎቹ ዓመታት በየወሩ ለሚታተመው ኢትዮጵያን ሪቪው ይባል ለነበረው መጽሔት ዋና አርታዒ በመሆን ሳገለግል ነበር፡፡ እንደዚሁም ደግሞ አልፍ አልፎ በአንዳንድ ርዕሰ ጉዳዮች ላይ አንዳንድ መጣጥፎችን እያዘጋጀሁ አበረክት ነበር፡፡ ሆኖም ግን ከስነልቦና ምልከታ ጭምር ነበር ሳዘጋጅ የነበረው፡፡ ስለኢትዮጵያ እና ስለ አፍሪካ ከመጻፍ ይልቅ ስለኢትዮጵያ ምንም ዓይነት ነገር አለመናገር ይቀለኝ ነበር፡፡ በእርግጠኝነት በዚያን ጊዜ ሁሉም ነገር ለእኔ ተስፋ አስቆራጭ ነበር ምክንያቱም የአፍሪካን ዋና የሰውነት አካል እንደ ነቀርሳ ቡርቡር አድርገው የበሉት ረኃብ፣ የእርስ በእርስ ጦርነት እና ሙስና የተንሰራፉበት ጊዜ ስለነበር ነው፡፡ አቅመቢስነት፣ ድንቁርና እና ወንጀለኛነት በአፍሪካ የስልጣን ኮርቻ ላይ ተቀምጠው የሚጋልቡበት ወቅት ነበር፡፡ ሁኔታው ልብን የሚሰብር እና ተስፋ አስቆራጭ ነበር፡፡

ከአሜሪካ የዕለት ከዕለት ኑሮ በመላቀቅ በኢትዮጵያ እና በአፍሪካ ደህና የሆነ የመደበቂያ ቦታን አገኘሁ፡፡ በእነዚህ ቦታዎች እኔ እና መሰል የአካዳሚ ጓደኞቼ ስለኢፍትሀዊነት፣ ጭቆና፣ ስለእኩልነት ማጣት፣ ድህነት፣ በሽታ፣ ማይምነት፣ ሙስና- በእነዚህ እና በሌሎች የህግ እና የአካዳሚ ረቂቅ ቋንቋን በሚጠይቁት የሰብአዊ መብት ጉዳዮች ላይ ትኩረት በማድረግ እና ገንቢ ትችቶችን በማቅረብ ማስተማሩን እና መስበኩን ተያያዝነው፡፡ በአፍሪካ ችግሮች ላይ ትኩረት በሚያደርጉ የአካዳሚ መጽሔቶች እና መጽሐፎች ገጸች ላይ ገንቢ ጽሑፎችን እና ትችቶችን በማቅረብ የምሁርነት ሞራላዊ ግዴታችንን ስንወጣ ደስታ እየተሰማን ነበር፡፡ ጥቂቶቻችን ስልጣናቸውን ከህግ አግባብ ውጭ በሚጠቀሙ እና የዜጎችን ሰብአዊ መብቶች በሚደፈጥጡ አምባገነኖች ላይ ያለምንም ፍርሀት እና መሸማቀቅ እውነቱን አፍረጥርጦ በማውጣት እና በመናገር (አካዳሚያዊ እና ሳይንሳዊ የሆኑ ውስብስብ እና አደናጋሪ የሆኑ አገላለጾችን በማስወገድ እና በቀላል ቋንቋ በመጠቀም) በቀጥታ የማቅረብ ድፍረቱ ወይም ዝንባሌው ነበረን፡፡

ከዕለት የዕለት ኑሮዬ ከመጀመሪያው እረድፍ ላይ ካሉት ተግባሮች እንደ አንዱ በመቁጠር በኢትዮጵያ ላይ እየተከሰቱ የቆዩትን እና አሁንም በየጊዜው በመከሰት ላይ ላሉት ጉዳዮች አጽንኦ በመስጠት ከአካዳሚያዊ እና ከምሁርነት ተግባሬ ሳልለይ በአገሪቱ ላይ እየተፈጸሙ ያሉትን ክስተቶች በሩቅ ስከታተል ቆይቻለሁ፡፡ አሁን በህይወት ስለሌለው መለስ ዜናዊ እና ስለእርሱ አገዛዝ በጣም ጥቂት ነገሮችን ነበር የማውቀው (ስለእርሱ ብዙ ማወቅም ጉዳዬ አልነበረም)፡፡ በአጠቃላይ መልኩ ስመለከተው መለስ እና ግብረአበሮቹ ምንም ዓይነት ጉዳት የማያመጡ መስለው ይታዩኝ ነበር፡፡

እ.ኤ.አ በ2005 የተደረገውን አገር አቀፋዊ ምርጫ ሂደት በአንክሮ እከታተል ነበር፡፡ ስለምርጫው ነጻ፣ ፍትሀዊ እና ተዓማኒት እንዲሁም እንከን የለሽ መሆንን እና ነጻ ውድድርን አስመልክቶ በአቶ መለስ ስለት ምላስ በእራሱ አንደበት ሲናገር ስሰማ አድናቆቴ የላቀ ነበር፡፡ ለተቃዋሚ ፓርቲዎች፣ ሲቪል ማህበረሰብ ድርጅቶች፣ እና ለሰብአዊ መብት ተሟጋቾች ተሰጥቶ የነበረውን የፖለቲካ መድረክ መስፋት ስመለከት እና ስሰማ በጣም እገረም ነበር፡፡ መለስ ዴሞክራሲን እና የዴሞክራሲ አስተሳሰቦችን በማስመለክት ይናገራቸው በነበሩት ንግግርች እንዲሁም ቢል ክሊንተን እና ቶኒ ብሌር መለስን “የአፍሪካ አዲስ ዝርያ መሪ” እያሉ እያንቆለባበሱ በየአጋጣሚው ሲያሰሟቸው በነበሩት ዲስኩሮች እደነቅ እና እደሰት ነበር፡፡ እንዲያውም ለበርካታ አስርት ዓመታት የዴሞክራሲን ጣዕም ሳታጣጥም በአምባገነኖች መዳፍ ስር ስትማቅቅ ለቆየችው ኢትዮጵያ መለስ የጥሩ እድል እና የመልካም አጋጣሚ ባለእጣ ሆኖ አገሪቱ እስካሁን ድረስ አጥታው ለቆየችው የዚህ ታሪካዊ የሽግግር ስርዓት መሪ ይሆናል የሚል ጽኑ አቋምን ሰንቄ ነበር፡፡ (ሞኝ ልትሉኝ ትችላላችሁ፣ ግድ የለም በሉኝ::)

ለኢትዮጵያ ሰብአዊ መብት ተሟጋች ሆኘ በተለያዩ ፖለቲካዊ፣ ኢኮኖሚያዊ እና ማህበራዊ ጉዳዮች ላይ የጡመራ ስራየን ለመጀመር ትግሉን ስቀላቀል ድንገተኛ እና ያልታሰበ ነበር፡፡ እ.ኤ.አ የ2005 ድህረ ምርጫን ተከትሎ ተከስቶ በነበረው ውዝግብ ሳቢያ አቶ መለስ የደህንነት እና የፖሊስ ኃይሉን በቀጥታ በእራሱ ቁጥጥር ስር በማድረግ ባልታጠቁ በንጹሀን ኢትዮያውያን/ት ዜጎች ላይ የፈጸመው እኩይ የእልቂት ተግባር እና በተቃዋሚ መሪዎች እና አባላት፣ በሰብአዊ መብት ተሟጋቾች፣ በሲቪል ማህበረሰብ መሪዎች እና ጋዜጠኞች ላይ የተደረገው የጅምላ እስራት በህይወቴ አይቸው የማላውቀው “ፍጹማዊ የእልቂት ጥቃት” ፈጠረ፡፡ የገዥው አካል ቁንጮ በሆነው በእራሱ በመለስ የተሰየመው አጣሪ ኮሚሽን እ.ኤ.አ በ2007 ባወጣው ዘገባ መሰረት በመለስ ታጣቂ ኃይሎች 193 ያልታጠቁ ሆኖም ግን በሰላማዊ መንገድ ተቃውሟቸውን ለማሰማት የወጡ ንጹሀን ዜጎችን መግደሉን እና ሌሎች ወደ 800 አካባቢ የሚጠጉ ዜጎች ደግሞ የቆሰሉ መሆናቸውን ይፋ አደረገ፡፡

ይህ እልቂት ለእኔ በጣም አሳዛኙ እና በሰው ልጆች ላይ ሊፈጸም የማይገባ አሳዛኝ የታሪክ ጠባሳ ነው፡፡ እ.ኤ.አ በ2005 በመለስ ጭራቃዊ ትዕዛዝ በንጹሀን ዜጎች ላይ የተፈጸመው እልቂት እ.ኤ.አ በ1960 በደቡብ አፍሪካ በአፓርታይድ የዘረኝነት ፖሊሲ እኩይ ምግባር ምክንያት በታጣቂ ፖሊሶች ሻርፕቪሌ በምትባል ከተማ በ69 ያልታጠቁ ጥቁር አፍሪካውያን/ት ንጹሀን ዜጎች ላይ ከተፈጸመው እልቂት የበለጠ የከፋ እና የከረፋ ነበር፡፡ እ.ኤ.አ በ1960 በሻርፕቪሌ ከተማ የተፈጸመው እልቂት ለዓለም ህዝብ ህሊና ሰቅጣጭ እና አስደነጋጭ ሰይጣናዊ ድርጊት ነበር፡፡ ሆኖም ግን የመለስ የ2005 እልቂት በዓለም ህዝብ እይታ የዓይን ቅንድብን የሚያረገበግብ አልነበረም፡፡ ምናልባትም ይህ ድርጊት በእኔ ላይ ቁጣን ፈጥሮ እንደ አሳተ ጎሞራ በመፈንዳቱ እስከ አሁንም ድረስ እያንገበገበኝ በመዝለቁ ምክንያት የፈጠረው ስሜት ለመሆኑ ትንሽ ፍንጭ ይሰጣል የሚል ግምት አለኝ፡፡ በዚያ እልቂት ተዋንያን የነበሩ እጃቸው በደም የየተጨማለቀ 237 በስም፣ በመልክ  እና በማንነት የሚታወቁ ወሮበላ ነፍሰ ገዳዮች (ፖሊሶችና የደህንነት አባሎች) ማንም አይጠይቀንም በሚል የታበየ አንደበት በመመካት በአሁኑ ጊዜ በኢትዮጵያ አውራ መንገዶች ላይ ደረታቸውን ነፍተው ሲንገዋለሉ ይውላሉ! በሌላ በኩል ደግሞ የእነርሱ የእብሪት ጭፍጨፋ ሰለባ የሆኑ የሙት መንፈሶች ከመቃብር ውስጥ ሆነው የፍትህ ያለህ በማለት ይጮሀሉ፡፡

የመለስ አሳዛኝ የእልቂት ተውኔት በምዕራቡ ዓለም የሰለጠኑ ምሁራንን በተለይም እንደ እኔ ያሉት የኢትዮ-አሜሪካ ምሁራን የማህበራዊ እና የፖለቲካ ኃላፊነት ከምን ላይ እንደሆነ ጥልቀት ባለው መንገድ እንድጠይቅ አስገድዶኛል፡፡ “የፍሬይሪያን ተቃርኖ” (ከደራሲ ፓውል ፍሬይሬ “የተጨቋኞች ስነ ትምህርት”) እያልኩ በምጠራው በጣም አስባለሁ፡፡ ፍሬይሪ እንዲህ በማለት ይሞግታሉ፣ “ትምህርት ወጣቱን ትውልድ አሁን ባለው ስርዓት አመክንዮ መስተጋብር በመፍጠር እና ስምምነት እንዲመጣ በማድረግ ወይም ደግሞ የነጻነት ቀንዲል እና ተምሳሌት በመሆን እዲሁም ወንዶች እና ሴቶች ነገሮችን በውል በማጤን እና የፈጠራ ክህሎትን በማከል በእውነት ላይ በመመስረት ችግሮችን መፍታት እንዲችሉ እና ይህችን የእነርሱን ዓለም እንዴት መለወጥ እና ማሸጋገር እንዲችሉ በማድረግ ትምህርት የማሳለጥ ስራን በመስራት ቁልፍ ማና አለው፡፡” ምሁር እንደ ሰብአዊ መብት ተሟጋች ምን ማድረግ አለብኝ? በማለት የምሁር ልሳን አንደበት መሆን አለበት፡፡

የመለስ እልቂት በህይወቴ በዘግናኝነቱ አንድ ቋሚ ምዕራፍ ይዞ ይኖራል እናም በሌሎች መለስ መሰሎችም ጥርጣሬ ያድርብኛል፡፡ ከእልቂቱ በኋላ መለስ ለአይኖቸ አውሬ ሆኖ ታየኝ፡፡ ለብዙ ጊዜ (አሁንም ቢሆን) እንዲህ በሚል በአንድ ጥያቄ እወጠር ነበር፡ በ21ኛው ክፍለ ዘመን እንዴት አንድ ሰው ብቻውን ስልጣንን እንደ ሲባጎ ጠቅልሎ በመያዝ በመቶዎች በሚቆጠሩ ምንም ዓይነት ትጥቅ በሌላቸው ንጹሀን ዜጎች ላይ እልቂትን ይፈጽማል? ይህ የሚያሳበብድ ጥያቄ ነበር ለኔ፡፡

የመለስ እልቂቶች በህሊናዬ ላይ ጥልቅ ስሜቶችን ፈጥረውብኛል፡፡ በአለፉት አስርት ዓመታት በኢትዮጵያ ውስጥ የሌለሁ ብሆንም ለመጀመሪያ ጊዜ አገሬ እኔን እንዳልተዎችኝ ግንዛቤ ወስጃለሁ፡፡ እኔ በአካል ከኢትዮጵያ ለዘለቄታው የራቅሁ ብሆንም በመለስ እልቂቶች ምክንያት ኢትዮጵያ ለዘላለም ከአዕምሮዬና ከልቤ  እንዳትጠፋ አድርገውኛል፡፡ ይህንን ስሜት በአሁኑ ጊዜም ቢሆን እንኳ በትክክል ለመግለጽ ያስቸግረኛል፡፡ ማለት የምፈልገው ባልታጠቁ ንጹሁን ዜጎች ላይ የተደረገው እልቂት እና በድረ ገጽ ላይ የተለቀቀው አስደንጋጩ ፎቶግራፋቸው በእራሴ ላይ እንደ አሳት ገሞራ በመፈንዳት የቁጣ ጅረት አንዳፈስ አርገዉኛል፡፡ (አንዳንዶቹ ይህ የቁጣ ጅረት አሁንም ቢሆን ባለማቋረጥ በተጠናከረ መልኩ በመንፈሴ ዉስጥ በመፍሰስ ላይ ይገኛል)፡፡ አንደሚባለው ተስፋ በተሟጠጠበት ጊዜ እኛ እራሳችን ሁኔታውን እንወስነዋለን ወይም ደግሞ ሁኔታው እኛኑ እራሳችንን ይወስነናል፡፡ በዚህን ጊዜ ነው በመለስ ዜናዊ የአምባገነንነት አገዛዝ እና አንድ ዓይነት ዩኒፎርም በለበሱ በእርሱ ህገወጥ ወሮበሎች ላይ የጡመራ ስራየን በመወሰን የጀመርኩት፡፡

አልፍ አልፎ የምጽፋቸውን ጽሑፎች በኢትዮጵያ ጉዳይ ላይ ተጽፈው በሚለቀቁ በወቅቱ በነበሩ ጥቂት ድረ ገጾች ላይ በማቅረብ የጡመራ ስራዬን ጀመርኩ፡፡ በወቅቱ መረጃ የሚሰጡ ጦማሮችን ከመከታተል በስተቀር አጠቃላይ በሆነ መልኩ በጡመራ ስራዎች ላይ ሙሉ በሙሉ አልገባሁበትም ነበር፡፡ የመጀመሪያውን የጡመራ ስራየን እ.ኤ.አ በ2006  (http://almariamforthedefense.blogspot.com) በሚለው ድረ ገጽ በመጠቀም ማውጣት ጀመርኩ፡፡ የጡመራ ስራዎች እና አልፍ አልፎ የሚወጡት ያለተፈረሙ የአርትኦ ስራዎች በተለያዩ ድረ ገጾች በየሁለት ሳምንቱ መውጣት ጀመሩ፡፡ በዚህ ሁኔታ ሁፊንግተን ፖስት እና ኦፐን ሳሎን/Huffington Post and Open Salon የተባሉ ደረ ገጾችን በመክፈት የተጠናከረ ስራ መስራት ጀመርኩ፡፡

አሁን ለበርካታ ዓመታት በብዙ አንባቢዎቼ ዘንድ በተደጋጋሚ እየተነሱ እጠየቅ ወደነበርኩባቸው ጥቂት ጥያቄዎች እመለሳለሁ፡፡ ለምንድን ነው ለበርካታ ዓመታት የሰኞ ትችት/Monday Commentary የተባለውን ትችት በተከታታይነት የምጽፈው? ያንን ጥያቄ እ.ኤ.አ በ2007 “የምትጮኸዋ ትንሿ ወፍ እና የጫካው እሳት: የዲያስፖራው የሞራል ትረካ/ The Humming Bird and the Forest Fire: A Diaspora Morality Tale“ በሚል ርዕስ በመጻፍ ለጥያቄው ምላሽ ለመስጠት ሞክሪያለሁ፡፡ የእኔ አጭሩ መልስ በታላቁ የአፍሮ-አሜሪካ የህግ ባለሙያ እና የህጻናት ፈንድ ተንከባካቢ ድርጅት/Children’s Defense Fund መስራች እና ፕሬዚዳንት በሆኑት በማሪኦን ራይት ኤድልማን አባባል ቃላት ላይ የተመሰረተ ነበር፡፡ እኒህ ምሁር እንዲህ ነበር ያሉት፣ “በኢፍትሀዊነት ላይ ቁንጫ መሆን ይኖርባችኋል፣ በቂ የሆኑ ቁንጫዎች ስልታዊ በሆነ መልኩ ተደራጅተው የማጥቃት ስራቸውን የሚሰሩ ከሆነ ታልቁ ውሻ እንዳይመቸው ማድረግ ይችላሉ፡፡” በተመሳሳይ መልኩም ትልቁን አገር መለወጥ እና ሽግግር ማድረግ ይቻላል“ የምትጮኸዋ ትንሿ ወፍ/ቁንጫዋ ለውሻ እንዳልተመቸችው ሁሉ፡፡ (እ.ኤ.አ በ2011 ማጊ ሀካላ የተባለች ወይዘሮ “የምትጮሆዋ የኢትዮጵያ ትንሿ ወፍ“ በሚል ርዕስ የጡመራ ድረ ገጽ ከፈተች፡፡ እንዲህ በማለትም ጻፈች፣ “ይህ ታሪክ በኢትዮጵያ ለሚደረገው የዴሞክራሲ ትግል አገልግሎት ውሏል፣ ሆኖም ግን በእራሴ ላይ ትንሽ ድፍረት ሴጥቶኝ ልጠቀምበት ችያለሁ አለች፡፡ ምንጊዜም ቢሆን ታታሪ እና መንፈሰ ጠንካራ ሁኑ፡፡“) ማጊ ሀካላን አመሰግናለሁ፡፡

የእኔ ትችት ውስጣዊ ይዘት ምንድን ነው? በእኔ ትችት ላይ አንድ ዋና የሆነ መርህን እከተላለሁ፣ ይኸውም በስልጣን መንበር ላይ ተጣብቀው ለሚገኙ እና ስልጣናቸውን ከህግ አግባብ ውጭ ለሚጠቀሙ እና ሰብአዊ መብትን ለሚደፈጥጡ እስከ እፍንጫቸው እውነት እውነቱን መናገር ነው፡፡ ለምን? 1ኛ) እውነት ሁሉንም የሰው ልጆች ዘር ነጻ ያደርጋል፡፡ እውነተኛውን ነገር በመቀበል ነው ለሰራናቸው ስህተቶች ተጠያቂ የምንሆነው እና ትክክለኛውን ነገር ብቻ ለመስራት ተነሳሽነት እና ቁርጠኝነት የምናሳየው፡፡ እውነት አእምሯችንን ብሩህ ያደርጋል፡፡ በስልጣን ላያ ላሉ እውነትን መናገር በቀዛቃዛ የአየር ጸባይ ወቅት በቀዝቃዛ ዉሃ ሻወር እንደመውሰድ ያህል ነው፡፡ በመጀመሪያ ደረጃ የሚያስፈራ እና የሚያንቀጠቅት ይመስላል፣ ሆኖም ግን በሂደት የበለጠ በኃይል እንዲሞሉ ያደርጋል፣ ከፍተኛ የሆነ ፍላጎት ያሳድራል እናም በዚህ የተሟላ ኃይል እንዲኖር ያደርጋል፡፡ 2ኛ) ስልጣናቸውን ከህግ አግባብ ውጭ የሚጠቀሙ ከሁሉም በላይ እውነትን ይፈራሉ፡፡ ለምንድን ነው አምባገነን ጨቋኞች ጋዜጠኞችን በእየእስር ቤቱ እየወሰዱ የሚያጉሩ እና የጋዜጣ ህትመቶችን የሚዘጉ? የዚህ ምክንያቱ እውነትን ስለሚፈሩ ብቻ ነው! የፈረንሳይ አምባገነን የነበረው ናፖሊዮን ቦና ፓርት  እንዲህ በማለት ምልከታውን አስፍሯል፣ “አራት ተቃዋሚ ጋዜጦች ከአንድ ሺ ጎራዴዎች የበለጠ ይፈራሉ፡፡“ ሁሉም አምባገነኖች የነጻውን ፕሬስ ነጻ መረጃዎች አጥብቀው ይፈራሉ፡፡ እናም በየጊዜው የሚፈጽሟቸው ወንጀሎች እንዳይጋለጡ እና በነጻ ጋዜጦች አማካይነት ለህዝብ እና ለዓለም አቀፉ ማህበረሰብ ይፋ እንዳይሆኑ አጥብቀው ይፈራሉ፡፡ በእርግጥ ማንም ቢሆን በእውነት፣ በእውቀት እና ክብር ላይ ጠቅላይ የበላይነትን ሊጎናጸፍ አይችልም፡፡ ለዚህም ነው እውነትን ለመለዋወጥ የሚያስችል ምንም አይነት ደንቃራ ሳይኖር በገበያ ላይ እንዲገኙ ማድረግ አስፈላጊ ሆኖ የሚገኘው፡፡ እንዲህ የሚል አባባል አለ፣ “አንጸባራቂዋ እውነት ፍንትው ብላ የምትመጣው ብዙ ሀሳቦች ከተፋጩ እና ከተጋጩ በኋላ ብቻ ነው፡፡“ የሀሳቦች ግጭት እንዲኖር ከተፈለገ ነጻ ጋዜጦች እዲኖሩን እናድርግ፣ ጦማሪያን/ት (ጡመራ አድራጊዎች) በጦማራቸው አማካያነት እዲፋጩ እና እንዲጋጩ እናድርጋቸው፣ ጋዜጠኞች ያለምንም ፍርሀት፣ ገደብ እና ክልከላ በጋዜጦቻቸው በመጠቀም በነጻ እንዲዘግቡ እናድርጋቸው፣ ደራሲያን ያለምንም መሸማቀቅ በነጻ መጽሐፎቻቸውን እንዲጽፉ እናድርጋቸው፣ ተችት አቅራቢዎች እና ሀያስያን ያለምንም ፍርሀት በትችቶቻቸው ትኩረት ሰጥተው እንዲፋጩ እና እንዲጋጩ እናድርጋቸው፡፡ በሀሳብ እንድንፋጭ እና እንድንጋጭ እናድርግ፣ በክለሽንኮብ አንጋጭ፣ እውነቱ የቱ እንደሆነ ህዝቡ እንዲወስን እናድርግ!

የእኔ ትችቶች በኢትዮጵያ በስልጣን ላይ ላለው ገዥ አካል እና የእርሱ አመራሮች “ፍትሀዊ ያልሆኑት” እና ጠንካራ ትችትን የሚያቀርቡት ለምንድን ነው?

ከእኔ ሀሳቦች እና አመለካከቶች ጋር የማይስማሙ ወገኖች እኔ የምጽፈው እነርሱን ለማጥቃት፣ ለማዋረድ እና በስልጣን ላይ ባለው መንግስት እና በእርሱ አመራሮች ላይ አሉታዊ ተጽእኖ ለማሳደር እንደሆነ አድርገው ያስባሉ፡፡ እኔ በገዥው አካል ላይ ጨካኝ እንደሆንኩ አድርግው ይናገራሉ፣ እናም በተከታታይ በመጻፍ እና በመናገር እነርሱ በጣም አስፈሪዎች እና መጥፎዎች አሳያለሁ ይላሉ፡፡ እነርሱ ላስመዘገቧቸው መልካም ስኬቶች እና ለማንኛውም ላከናውኗቸው ተግባራት- ለገነቧቸው አንጸባራቂ ህንጻዎች፣ ለሰሯቸው መንገዶች (መሰረተ ልማት)፣ ላቆሟቸው ትምህርት ቤቶች እና ዩኒቨርስቲዎች ወዘተ ሁሉ ምንም ዓይነት ምስጋና እንደማልሰጥ አድርገው ያቀርባሉ፡፡ ምንጊዜም ቢሆን በገዥው አካል በአገሪቱ ውስጥ የሚደረገውን የኢኮኖሚ እድገት እና ልማት ጥረት በማሳነስ ጥላሸት የምቀባ አድርጌ እንደማቀርብ አድርገው ያቀርባሉ፡፡

በእኔ ትችቶች ላይ ስምምነት የሚያደርጉ ሰዎች የእኔን ትንታኔ እና የአመክንዮ ጭብጦች ሙሉ በሙሉ ትክክል ናቸው ይላሉ::

እውነተኛው እና ሊሰመርበት የሚገባው መሰረታዊ ነገር ግን እኔ በኢትዮጵያ በስልጣን እርካብ ላይ ተፈናጥጦ ለሚገኘው ገዥ አካል የህዝብ ግንኙነት ወይም ፕሮፓጋንዳ ኃላፊ አይደለሁም፡፡ እኔ ትችቶችን መጻፍ የጀመርኩት በኢትዮጵያ በስልጣን ላይ ሆነው ስልጣናቸውን ከህግ አግባብ ውጭ ለሚጠቀሙ እና የዜጎችን መብቶች በሚሸራርፉ እና በሚደፈጥጡ አምባገነኖች ላይ የሚስተዋለውን እውነታ በማውጣት ለኢትዮጵያ ህዝብ እና ለዓለም አቀፉ ማህበረሰብ እንደቀተር ጸሐይ ፍንትው አድርጎ ለማሳየት እንጂ እነርሱ ሰራነው ለሚሉት ፍሬከርስኪ ስኬት እንደዘምር አይደለም፡፡ እውነታውን አንጠርጥሮ አውጥቶ መዘገብ “ኢፍትዊ” ከሆነ ጎሽ እንኳን ሆነ:: ሆንም ግን የማያጨቃጭቁትን እውነታዎች እስቲ እረጋ ብለን እንመልከት፡፡ ገዥው አካል “ባለፉት አስርት ዓመታት ውስጥ ባለሁለት አሀዝ የኢኮኖሚ እድገት አስመዝግቢያለሁ ይላል፡፡ ከጥርጣሬ በዘለለ መልኩ መለስ እና የእርሱ አገዛዝ “የመለስ ዜናዊ የውሸት የኢኮኖሚ እድገት” በሚል ርዕስ ትችት ማቅረብ ከጀመርኩበት ጊዜ ጀምሮ ባለሁለት አሀዝ የኢኮኖሚ እድገት አስመዝግቢያለሁ በማለት የእድገቱን እውነትነት ለማሳየት በሚል የሸፍጥ ስራ አቶ መለስ ከእኔ ትችት ጀምሮ መጽሐፎችን ሁሉ ሲያስስ ከርሟል፡፡ በአዲስ አበባ ከተማ ውስጥ ተገንብተው በማንጸባረቅ ላይ የሚገኙት ህንጻዎች ለእኔ ብዙም ትርጉም የሚሰጡኝ አይደሉም፣ ምክንያቱም አብዛኞቹ በሚባል መልኩ የግንባታ እና የማስዋብ ስራዎች ደረጃቸውን ያልጠበቁ እና ከተያዘላቸው መስፈርት በታች በመሆናቸው እና የግንባታ አዋጁን (የኢትዮጵያ ህንጻ አዋጅ ቁጥር 624/2009ን ይመለከቷል) በመጣስ በሙስና የተገነቡ በመሆናቸው ነው፡፡ ብዙዎቹ ከፍ ብለው የተገነቡ ህንጻዎች መሰረታዊ የሆኑ አገልግሎቶች ማለትም ውኃ፣ የኃይል አቅርቦት እና ሌሎች ፋሲሊቲዎች እጥረት ይታይባቸዋል፡፡ ብዙዎቹ ሰዎች በእግር በመጠቀም ብዙ ደረጃ ያሏቸውን ህንጻዎች ለመጓዝ ይገደዳሉ ምክንያቱም የአሳንስሮች አገልግሎቶች ከእነአካቴው የሉም ወይም ደግሞ በህንጻው ባለቤቶች ሆን ተብሎ ከአገልግሎት ውጭ እንዲሆኑ ይደረጋሉ፡፡ በዋናዋ መናገሻ ከተማ በአዲስ አበባ ምንም ዓይነት የፍሳሽ እና የቆሻሻ ማስወገጃ ስርዓቶች የሉም፡፡ ገዥው አካል ገና የመጀመሪያው ኃይለኛ ዝናብ መጣል ሲጀመር የሚሰነጣጠቁ እና በጎርፍ የሚታጠቡ በቻይና እገዛ የሚገነቡ “ሽሮ ፈሰስ መንገዶች” አሉት፡፡ በቅርቡ በፎቶ እና በቪዲዮ ተቀርጸው ለደካማ እና ለሽሮ ፈሰስ መንገዶች በማስረጃነት የቀረቡትን መንገዶች ከዚህ ስር በመጫን መመልከት ይቻላል፡፡

በአገሪቱ ውስጥ ለተገነቡት ለሁሉም ዩኒቨርስቲዎች እና ኮሌጆች ለገዥው አካል እውቅና መስጠት እና ምስጋና ማቅረብስ? “አምባገነንነት በአካዳሚው ዓለም” በሚል ርዕስ ባቀረብኩት ትችት የምሁርነት ሽባነት እና የሞራል ኪሳራ በኢትዮጵያ የከፍተኛ ትምህርት ተቋማት ስርዓት ውስጥ ተማሪዎች ጥራት ያለው ትምህርት ያለማግኘት እና ቀደምት በሆነው በመቀሌ ዩኒቨርስቲ የህግ ፋኩልቲ የሚደረገው ማስፈራራት የትምህርቱን ጥራት አፈር ድሜ ያስበላ እና በአገሪቱ ውስጥ ያሉ ተቋማት ነጻ የአካዳሚ አየር የማይጎበኛቸው መሆናቸውን በተጨባጭ ያመላክታል፡፡

በኢትዮጵያ ውስጥ ያለ ማንኛውም የሚያብለጨልጭ ነገር ሁሉ ወርቅ ነው ለምን አይልም አንደሆነ የሚሉት ይቅርታ እንድታደርጉልኝ በትህትና እጠይቃለሁ!

እኔ በመለስ ላይ ያለኝ ተቃውሞ በፍጹም ግለሰባዊ አይደለም፡፡ ግለሰቡን በፍጹም አልጠላሁትም ምክንያቱም በፍጹም አላውቀውምና፡፡ አንድን በፍጹም አግኝተውት እና አናግረውት የማያውቁትን ሰው መጥላት ኢምክንያታዊ ነው፡፡ ሆኖም ግን ሰውየውን በሚያደርጋቸው ስራዎቹ፣ ፖሊሲዎቹ፣ በሚሰጣቸው ጋዜጣዊ መግለጫዎቹ፣ በሚያደርጋቸው ንግግሮቹ እና በእራሱ ትዕዛዝ በወጣት ጋዜጠኞች ላይ በፈጸማቸው አስደንጋጭ እልቂቶች፣ በዘረጋው የጎሰኝነት ስርዓት ውስጥ እንደ ካንሰር ባስፋፋው የሙስና ባህል እና በኢትዮጵያ ውስጥ በፈጠራቸው ባንቱስታንስ (ክልሎች) ምክንያት በደንብ አድርጌ አጥንቸዋለሁ፡፡

መለስ ባለብሩህ ጭንቅላት፣ የማመዛዘን ችሎታ ያለው እና አንደበተ ርትዑ ሰው ነው እየተባለ ይነገርለታል፡፡(እንደ ዊኪ ሊክስ ከሆነ ከእርሱ ግንኙነት ያላቸው አንዳንድ የአሜሪካ ዲፕሎማቶች  ነገሮችን በአንክሮ የማየት ችሎታውን እና እርሱ በመረጣቸው ጉዳዮች ላይ ተናግሮ ሰውን የማሳመን ችሎታ እንዳለው በመቁጠር አድናቆታቸውን ይገልጻሉ)፡፡ እኔ እንዳየሁት ከሆነ መለስ የአስመሳይነት የምሁር ባህሪን የተላበሰ፣ እርሱ የሚፈልገው ነገር እንዲደረግለት በተከታታይ የሚወተውት የምሁርነት ካባን ያጠለቀ ሆኖም ግን እውነተኛ ያልሆነ ምስለ ምሁር ነበር፡፡ ሁልጊዜ የበታቸችነት ስሜት የሚሰማው ሰው ነበር፡፡ ግልፍተኛ እና ከመቅጽበት በመነሳት ሰውን በነገር ውርጅብኝ የሚጠዘጥዝ፣ አዋራጅ፣ መዘዘኛ እና ሰው ጤፉ ዓይነት ፍጡር ነበር፡፡ ተቃዋሚዎች በጠየቁት ጊዜ ሁልጊዜ በግንፍልተኝነት ይመልሳል፡፡ በእኔ እይታ እንደዚህ ዓይነት ድርጊቶችን የሚፈጽሙ ሰዎች ሁልጊዜ የበታችነት ስሜት የተጠናወታቸው እና እንደዚህ ያሉ ምግባር የጎደላቸው ድርጊቶችን ከመፈጸም የማይመለሱ ናቸው፡፡ የእብሪተኛነት፣ የአታላይነት እና የሰው ዘርጣጭነት ጭንብሉን በማጥለቅ የበታችነት ስሜት የማይታይበት ለመምሰል ይሞክራል፡፡ ሆኖም ግን ሊሆንለት አልቻለም፡፡ ባልተስተካከለ ሻካራ መሬት ላይ ይቆማል፡፡ በሁሉም ነገር ላይ ከእርሱ ጋር አልስማማም ነበር ምክንያቱም ተጫባጭነት ባለው ሁኔታ ከእርሱ ጋር እንድስማማ የሚያደረግኝ በጎ ነገር ፈጽሞ የለውምና፡፡

መለስ በሚያሳፍር ሁኔታ አፈዘራፍ ነበር፡፡ አሳፋሪ በሆነ መልኩ የእርሱን ተቀናቃኞች በአደባባይ በመዘለፍ እና ዓለም አቀፍ የምርጫ ታዛቢዎችን እና የሰብአዊ መብት ተሟጋች ድርጅቶችን በመስደብ እራሱን የተዋረደ አድርጓል፡፡ እራሱን እንደ የመንገድ ላይ ዘራፊ ወሮበላ የሚቆጥርን ሰው ለማክበር ለኔ በጣም አስቸጋሪ ነገር ነው፡፡ ለዚያም ነው “የወሮበላ ንግግር” የሚሉ ቃላትን ያያዝኩለት፡፡

ያለምንም ጥያቄ በገዥው አካል ላይ የውዳቂዎች እና እርባና የለሾች ምርጥ ነው፡፡ እናም ባለፉት ሁለት ዓመታት እውነታዎች እንዳሳዩን ከመለስ ውጭ ገዥው አካል አንገቷን በስለት ተቆርጣ በባዶ ክብ መስመር ላይ እንደምትሽከረከር ዶሮ ሆነዋል፡፡ መለስ የድርጊቶች ሁሉ ቀያሽ አንቀሳቃሽ ሞተር ለመሆኑ ምንም የሚያጠራጥር ነገር የለም፡፡ ይህንን ሁሉ ካልኩ ዘንድ ለሁሉም አንባቢዎቸ ግልጽ እንዲሆን የምፈልገው ነገር በመለስ የገዛዝ ስርዓት ላይ ያለኝ ሁነኛ ጥላቻ በእራሱ በመለስ ስብዕና ላይ ካለኝ ጥላቻ ጋር በፍጹም የሚያሳስት መሆን የለበትም፡፡

በትችቴ ላይ “መለስ መልካም ጉዞ” በማለት እንደጻፍኩት ሁሉ መለስ ከእድል ጋር ቀጠሮ ነበረው፣ እናም በማንዴላ ጫማ የማንዴላን አርዓያ በመከተል ረዥሙን ጎዳና ተጉዞ ነጻነትን ያጎናጽፍ ነበር፡፡ እንደ ማንዴላ ሁሉ አስተባባሪ እና አደራጅ መሆን ይችል ነበር፡፡ አንዲቷን ሰላም እና ፍቅር የሰፈነባት የተከበረች እና የታፈረች ኢትዮጵያን መፍጠር ይችል ነበር፡፡ በጎሳዎች መካከል ህዝቡን ለማገናኘት ድልድዮችን መገንባት ይችል ነበር፡፡ የዜጎችን ልቦች እዕምሮዎች ሊያስተሳስሩ የሚችሉ መንገዶችን መስራት ይችል ነበር፡፡ እ.ኤ.አ በ2005 በእርሱ ትዕዛዝ ለተፈጸመው የንጹሀን ዜጎች እልቂት እውነታው በአጣሪ ኮሚሽኑ ከተረጋገጠ በኋላ እንደ ማንዴላ ሁሉ የይቅርታን እና የእርቀ ሰላምን መንገድ መምረጥ ይችል ነበር፡፡ ይልቁንም መለስ በአጣሪ ኮሚሽኑ በተለይም ታላቅ ምስጋና ሊቸራቸው በሚገቡት አመራሮች ትክክለኛ የምርመራ ውጤት ላይ ተራ የሆነ ፕሮፓጋንዳውን ይነዛ ነበር፡፡ እነዚህ የአጣሪ ኮሚሽኑ አባላት አመራሮች ለእኔ ጀግናዬ ናቸው ምክንያቱም ስብዕናቸውን በጥቂት ጌጣጌጦች እንዲሸጡ በተጠየቁ ጊዜ እምቢኝ አሻፈረኝ በማለት እውነተኛ የህዝብ ልጅ መሆናቸውን በአደባባይ አስመስክረዋል፡፡

የማንዴላን እርምጃዎች ተከትሎ ከመሄድ ይልቅ መለስ የጎሳ ክፍፍልን በማራመድ፣ አገረ አቀፋዊ ክፍፍልን እና የእራሱን የጥላቻ መንገድ መረጠ፡፡ መለስ ሊመለስ ወደማይችል የሰይጣን እኩይ ምግባር ያስገባውን ኃይልን የበለጠ ግልጽ ለማድረግ የስልጣን ኃይልን ጠቃሚነት በሚገባ ይገነዘብ እንደነበር እገነዘባለሁ፡፡ ሸክስፒር በጁሊየስ ቄሳር ላይ በግልጽ እንዳመለከተው “የሰው ልጅ የሚፈጽማቸው ጭራቃዊ ተግባራት ከጀርባው ሆነው ይኖራሉ፡፡“ መለስ ዜናዊ በህይወት በነበረበት ዘመኑ ብዙ ጭራቃዊ ተግባራትን ፈጽሟል፣ አሁንም ቢሆን የእርሱ የጨለማ ጭራቃዊ ትሩፋቱ በኢትዮጵያ ላይ በመተንፈስ እና በመኖር ላይ ይገኛል፡፡ የመለስ እኩይ ምግባራት ተግባራዊ እየሆኑ እንዲቀጥሉ የቀየሳቸው እና በኢትዮጵያ ህዝብ ጫንቃ ላይ የጫናቸው ጭራቃዊ እኩይ ምግባሮች ማለትም የባንቱስታንስ የጎሳ ክፍፍል /ክልል፣ የንጹሀን ዜጎችን በመደፍጠጥ እያጋዘ ለማጎር የገነባቸው በርካታ እስር ቤቶች፣ በሙስና የተጨማለቀው ከንቱ ስርዓት እና የበርካታ ወጣቶችን ማለትም ርዕዮት፣እስክንድር፣ ሰርክዓለም፣ ብርቱካን፣ ውብሸት፣ አንዷለም፣ እና የሌሎችን ለመቁጠር የሚያዳግቱ ወጣት ኢትዮያውያን/ት ህይወት በአደጋ ላይ የጣለው የእርሱ የምህንድስና እና የመሰረተ ልማት ስራዎች ላይ ነፍስ ዘርተው በመተግበር ላይ ይገኛሉ፡፡ መለስ የሰራው ምንም ዓይነት በጎ ነገር “ከአጥንቱ ጋር ተቀብሯል::” ሆኖም መለስ አሁንም ከመቃብር ውስጥ ሆኖ ይገዛል፡፡ አስቀድመው በተዘጋጁ አሻንጉሊቶቹ፣ አስመሳዮች እና ቅጂዎቹ አማካይነት ፈጣጣ ካድሬዎቹ “የመለስን ራዕይ ለማስፈጸም” በሚል ከንቱ ጩኸት ጧት ማታ የሬዲዮ እና የቴሌቪዥን ፕሮግራሞችን ያጣብባሉ፡፡ በውሸት ጠገቦች ጋዜጦች ያትማሉ፡፡ እኔን የማታምኑኝ ከሆነ በቪዲዮ እና በኦዲዮ የተቀረጹትን የደቀመዝሙሮቹን እና የአሻንጉሊቶቹን ቅጂዎች በጥሞና ማዳመጥ ትችላላችሁ፡፡ መለስ በእነዚህ አሻንጉሊቶቹ ድምጽ እና የማስመሰያ የአካል ቅርጽ አካሎቻቸው ምክንያት በህይወት የሚኖር መስሏል!

ትችቶቼን ለመገንዘብ ቀላል በሆነ የእንግሊዝኛ ቋንቋ መጻፍ ይኖርብኛልን? በሌላ አገላለጽ የእኔን ትችቶች በጣም ተራ እና ቀላል ማድረግ ይኖርብኛልን? ትችቶቼን ማለሳለስ እና የማይኮሰኩሱ ማድረግ በአንባቢ ደንበኞቼ የምሁርነት ክህሎት ላይ ስድብ የመሰንዘር ያህል ነው፡፡ ከዚህም በላይ በህግ እና በህዝብ አስቸጋሪ የፖሊሲ ጉዳዮች ላይ ትኩረት በማድረግ ጠንካራ ትችቶችን በማቅረብ ለህዝብ ማስተማሪያነት ይውላል፡፡ ሁልጊዜም ቢሆን እንደዚህ ባሉ ጉዳዮች ላይ በጣም አሳንሶ እና አቅልሎ ማቅረብ የሚሞከር ቢሆን ትክክለኛ ትርጉማቸውን ከማደብዘዝ የዘለለ አይሆንም፡፡ በሌላ በኩል ደግሞ ከኢትዮጵያ ዩኒቨርስቲ ተማሪዎች ከሚደርሱኝ ዘገባዎች እንደተረዳሁት (በአጠቃላይ ከወጣቱ የህብረተሰብ ክፍል ማለት ይቻላል) የእኔ ትችቶች ወጣቶች ቃላትን በስፋት የማወቅ አድማሳቸውን ከፍ እንዳደረጉላቸው፣ ነገሮችን ጥንቃቄ በተሞላበት ሁኔታ ተመልከቶ ትንታኔ የመስጠት ችሎታን እንዳሻሻለላቸው እና የሞጋችነት እና የማገናዝብ ክህሎቶቻቸው ስለት እንዲሆኑ እንዳስቻሏቸው ግልጽ አድርገዋል፡፡ በስራ ላይ ያልተፈለገ ውጤት የመምጣት ህግ? ለጥቂት ግለሰቦች ጥቅም ሲባል እያንዳንዱን ድምጽ አሳንሶ ከማየት ይልቅ ለእያንዳንዷ ድምጽ ዋጋ በመስጠት በጥንቃቄ መመልከት የተሻለ ነገር ነው፡፡

የእኔ ትችቶች በጣም ትልቆች ናቸው ሆኖም ግን አጭር ማድረግ እችላለሁን? ይኸ በጣም ደስ የሚል እና ስሜትን የሚስብ ነገር ነው፡፡ በሂደት ከሚስተዋሉት ነገሮች በመነሳት የእኔ ትችቶች ለመዝናኛነት እና ለደስታ ተብለው የሚዘጋጁ እንዳልሆኑ ማስታወቅ አፈለጋለሁ፡፡ እኔ ዘጋቢ ጋዜጠኛ አይደለሁም ወይም ደግሞ ሰልፍ በመያዝ ለማስታወቂያ ሽያጭ የአምድ አዘጋጅም አይደለሁም፡፡ ትችቶቼን የምጽፍ በሚከተሉት ምክንያቶች ነው፡ 1ኛ) ፍቅር በተሞላበት መልኩ መርሆዎች እና ህጎች እንዲከበሩ ቅስቀሳ ለማድረግ እና ለማስተማር፣ 2ኛ) የእኔን አንባቢ ደንበኞች በአወዛጋቢ ጉዳዮች ላይ ግንዛቤ እና የጠራ አመለካከት እንዲኖራቸው በማድረግ ምሁራዊ አቅማቸው እንዲጎለብት ለማስተማር፣ 3ኛ) በምክንያት የተደገፉ ማስረጃዎች እና አሳማኝ  በሆኑ ወቅታዊ ጉዳዮች ላይ (አንዳንድ ታሪካዊ ሁነቶች) ፖለቲካዊ፣ የህግ እና የማህበራዊ ጉዳዮች ላይ ትንታኔ በመስጠት እውነተኛ እና ትክክለኛ የሆነ ትችት በማቅረብ ለፍትህና ለእውነት ሲባል መሞገት እንዲቻል፣ 4ኛ) ወጣት የሰብአዊ መብት ተሟጋቾች በዚህ ሙያ ላይ እንዲበረታቱ እና ወደ ሙያው በገፍ እንዲገቡ እና ለሰብአዊ መብት መጠበቅ ተሟጋች ዜጎች እንሆኑ ለማስቻል ነው፡፡

አጭር የሆኑ ትችቶችን እንድጽፍ የሚፈልጉትን አላከብርም አላልኩም፣ ይልቁንም እነዚህን ትችቶች በትርፍ ጊዚያቸው ማንበብ አለባቸው የሚል እምነት አለኝ፣ ወይም ደግሞ በከፊል አንብቧቸው፣ አለበዚይም ረዥም በመሆናቸው ምክንያት ብቻ ያለማንበብ ይችላሉ፡፡ እውነት ለመናገር እኔ እንደ ግለሰብ አንድ ሰው 2,500 ወይም ደግሞ 3,000 ቃላትን ለማንበብ  አስቸጋሪ ሆኖበት ቅሬታ ያቀርባል ብዬ ለማመን በጣም ይከብደኛል፡፡ ማንበብ ለ21ኛው ክፍለ ዘመን የዴሞክራቲክ ትውልድ ምሁራዊ ህይወት ጠቃሚ ነው ወይም ደግሞ መደረግ ያለበት ዋና አብይ ጉዳይ ነው የሚል እምነት አለኝ፡፡ ያለማንበብ (ብዙ ሰዓት) ጥቂት እውቀትን ብቻ እንድንገበይ ነው የሚያደርገን፡፡ የገለብ ገለብ ንባብ ግልብ እውቀት ብቻ እንዲኖረን ነው የሚያደርገው ይህም በእራሱ መሰረታዊ የሆነ ዋና እውቀትን ከመሸመት ይልቅ አንዳንድ አደናጋሪ እና የሽያጭ ቃላትን ብቻ እንድናነበንብ ያደርገናል፡፡ ፍሬደሪክ ዳጉላስ የተባሉት አፍሪካ-አሜሪካዊ የባሪያ ንግድ ተቃዋሚ መሪ እንዲህ በማለት ጥቆማ አድርገው ነበር፣ “ማንበብን በተማርክ ጊዜ ለዘላለሙ ነጻ ትሆናለህ“ ብለዋል:: አዲስ ነገር ለማወቅ የምሁራዊ ጉጉት መኖር የዚያ ነጻነት አንጸባራቂ ነበልባል ነው፡፡ እውቀት ኃይል ነው በተለይም በተግባር ላይ ሲውል እናም የዚህ ኃይል ምንጩ ማንበብ ነው፡፡ ነጸ ሆኖ ለመኖር አንድ ሰው ሁልጊዜ እና በጣም ማንበብ አለበት፡፡

ብዙ ሰዎች ስራ እንደሚበዛባቸው እና በሌሎች የተለያዩ ምክንያቶች የትኩረት አድማሳቸው ሊሰናከል እንደሚችል እገነዘባለሁ፡፡ በኢንተርኔት ዘመን እያንዳንዱ ሰው በማህበራዊ ገጾች የተሳሰረ እና ከላይ እና ከታች የተገናኘ እና የተቆራኘ ነው፡፡ የመረጃ መታጨቅ የሳይበርስፔስ አስተዳደራዊ ህግ ነው፡፡ በአሁኑ ጊዜ በመገናኛ ብዙሀን የሚሰጡትን አጭር መግለጫዎች ለማስወገድ በመረጃ የተጠናከሩ በእወነት ላይ የተመሰረቱ ትንታኔዎችን ለማሳደድ የማያቋርጥ ግፊት አለ፡፡ “ጉግል ደደብ አደረገን?” በሚል ርዕሰ የቀረበ ቀስቃሽ ጽሑፍ ኒኮላስ ካር እንደተመለከተው “የሰውን ልጅ እውቀት ከሚኮተኩቱ ወደ ኤልክትሮኒክ የጫካ ዳታ አዳኞች/አሳዳጆች እና መረጃ ሰብሳቢዎች ነው የተፈጠርነው“ ማለት የፈለግሁት የእኔ ትችቶች ለኤሌክትሮኒክ ጫካ አዳኞች/ሳዳጆች እና ሰብሳቢዎች ጥቂት ጠቀሜታ ነው ያላቸው፡፡ “በመገናኛ ብዙሀን አጭር መግለጫ ለመስጠት የሚራቡ ምግብ ለማሰብ ከሚሉት የእኔ ትችትች ጋር ሲነጻጸሩ ትንሽ ዋጋ አላቸው፡፡

መልስ ማግኘት የሚፈልጉ በርካታ ጥያቄዎች አሉ፡፡ ይህንን ጉዳይ ለማፋጠን ፍላጎት አለኝ አዚህ ትችት ላይ፡፡ ለምንድን ነው በየሳምንቱ የምጽፈው? ምክንያቱም ሳምንቱ ስላለ ነው፡፡ በየሳምንቱ ትችት ለማቅረብ ለትችቱ ርዕስ እና ዋና ጉዳዮችን የምመርጠው እንዴት ነው? እውነታውን አራሱን ያቀርብለኛል፡፡ ምናልባትም ስልጣናቸውን ከህግ አግባብ ውጭ የሚጠቀሙ እና የሰብአዊ መብት ደፍጣጮች? የጉግል መንፈስ ብቻ ያውቀዋል፡፡ ለማን ነው መጻፍ የሌለብኝ? በኢትዮጰያ በጣም ከልብ በሆነ መልኩ፣ በሰብአዊ መብት ጥበቃ ላይ ቀስቃሽ፣ መረጃን መሰረት ባደረገ እና ሀሳብን ባካተተ ውይይት በሰብአዊ መብት ጥበቃ እና በመንግስት ስህተቶች ላይ ለመሳተፍ ፍጎት ለሌላቸው የኔ  ጦማር አያገለግላቸዉም:: እኔ ማን ነኝ በእርግጠኝነት በዉነተኛነት ለማንስ ነው የምጽፈው? ለቀጣዩ የኢትዮጵያ ትውልድ ነው በአውነቱ የምጽፈው::

በእውነት ስለምንድን ነው መጻፍ የምፈልገው?  መነሻዎች እና መርሆዎች፡፡ አምባገነኖች እና ዴሞክራቶች ይመጣሉ ይሄዳሉ፡፡ ሆኖም ግን እነዚያ የሰውን ልጅ ክብር እና ነጻነት ከፍ የሚያደርጉ መርሆዎች የሰው ዘር በመሬት ላይ እስካልጠፋ ድረስ ይኖራሉ፡፡ መካከለኛ መጠን እና ይዘት ያለው ጽሑፍ ለመጻፍ ምን ያሀል ጊዜ ይወስድብኛል? ልትደነቁ ትችላላችሁ አውነት መናገር ጊዜ አይፈጅም፡፡ የእኔ ትችት የሚወክለው አንድ በጣም ትልቅ ዋጋ ያለው ዋና የሆነ መርህ ምንድነው? ሀሳብን በነጻ የመግለጽ መብት፡፡ ከዚህ አስተያየት ጋር በሙሉ ልብ እስማማለሁ፡፡ “አንተ ከምትለው ነገር ጋር አልስማማም የመናገር መብትህን ግን አስቀ ሞት ደረስ እከላከላለሁ፡፡“

ለእኔ ትችት መጻፍ እንዴት ያለ አስቸጋሪ ነገር ነው? ከረሜ ላ መብላት ምን ያህል ያስቸግራል? የእኔ ትችቶች ምን ያህል ለውጥ ማምጣት ይችላሉ? ባለፈው ሳምንት በሞት በተለየው እና ከታላቁ ቻርሊ ቻፕሊን ጀምሮ ታላቅ አስቂኝ አርቲስት በነበረው በሮቢን ዊሊያም ቃላት መዋስ አፈለጋለሁ፡፡ “የቱም ዓይነት ሰው ቢነግርህ ቃላት እና ሀሳቦች ዓለምን ይለውጣሉ፡፡” ለእኔ ትችቶች እውነታነትን የሚመራመሩ ካድሬዎች አሉኝን? ካድሬዎችን አልወዳቸውም፡፡

የሰኞ ትችትን መጻፍ ላቆም እችላለሁን? አዎ፡፡ በኢትዮጵያ ያለው ገዥ አካል በእየቀኑ ውሸት መናገሩን የሚያቆም ከሆነ፡፡ ስለገዥው አካል ጥሩ ነገር ልናገር እችላለሁን? አዎ፡፡ አምባገነኖች ስልጣናቸውን ከህግ አግባብ ውጭ መጠቀሙን ሲያቆሙ እና ኃላፊነትን መቀበል እና መሸከም ሲጀምሩ፡፡

ትችቶቼን በምጽፍበት ጊዜ የሚያጋጥመኝ የግል ቅሬታ ምንድን ነው? ዋናው እና ትልቁ እውነታ በኢትዮጵያ ስለሰብአዊ መብት ያለምንም ፍርኃት የሚጽፉ እና ለህዝቦች ሰብአዊ መብት መከበር የሚሟገቱ ለህዝብ ፍቅር እና ጠንካራ ተነሳሽነት ያላቸው በቂ የኢትዮጵያ ምሁራን እና ልሂቃን አለመኖራቸው ነው፡፡ ትችቶችን ለመጻፍ ልዩ ተሰጥኦ ወይም ክህሎት አለኝን? በፍጹም፡፡ ማንም ሰው እኔ እያደረግሁ ያለሁትን ነገር ማድረግ ይችላል፡፡ ሆኖም ግን ሁሉን ነገር የሚይዝ መሆን ያስፈልጋል፡፡ ማንም ቢሆን ወደ ኋላ በማይመለስ እና ድፍረት በተቀላቀከበት መልኩ ስልጣናቸውን ከህግ አግባብ ውጭ በሚጠቀሙ እና የንጹሀን ዜጎችን መብት ለሚደፈጥጡ አምባገነኖች እውነታውን እስካፍንጫቸው ድረስ መንገር መቻል አለበት/ባት፡፡ በዚህ ዓይነት መልኩ እራሳቸውን ያዘጋጁ ሰዎች ሀሳቦች ከአዕምሯቸው እና የህዝብ አፍቅሮታቸው ከልቦቻቸው በማያቋርጥ መልኩ እንደ ጅረት ውኃ ይፈስሳሉ፡፡

ከእኔ አንባቢ ደንበኞቼ መልስ እና ትችቶችን አገኛለሁን? አዎ፡፡ ሁሉችሁንም ከልብ አመሰግናችኋለሁ፡፡ ለእያንዳንዳችሁ በተናጠል ምላሽ መስጠት ባለመቻሌ ይቅርታ እንድታደርጉልኝ እጠይቃለሁ፡፡ ምንም ዓይነት ፋይዳ ለሌላቸው እርባናየለሽ ትችቶች እና ስሜታዊነትን ለሚጋብዙ ክብረቢስ ለሆኑ ጭፍን አስተያየቶች ምላሽ መስጠት ይኖርብኛልን? እንዴት ተደርጎ? በፍጹም፡፡ ለእርባናየለሽ ትችቶች ምላሽ መስጠት ምላሽ ሰጭው እራሱ እርባናየለሽ መሆን ማለት ነው፡፡ የጆርጅ በርናንድ ሻውን አባባል በመዋስ “ከብዙ ጊዜ በፊት ጀምሮ ትምህርት ቀስሜበታለሁ፣ ከአሳማ ጋር በፍጹም ትግል አትግጠም ቆሻሻ ትሆናለህና፣ ከዚህም በተጨማሪ አሳማው ጭቃ ዉስጥ መላወሱን ይወደዋለና፡፡ “የእኔን ትችቶች ወደ አማርኛ የሚተረጉማቸው ማን ነው? ራሳቸውን ያውቃሉ:፡ የእኔ ትችቶች በመጽሐፍ መልክ ሊወጡ ይችላሉን? አይቀርም በቀርብ ጊዜ።

ለደንበኞቼ የሚስጥር ተስፋ ላካፍላቸው እችላለሁን? አዎ በሚገባ እንጅ፡፡ የእኔ ትችቶች ወጣት ኢትዮጵያውያንን/ትን እና አፍሪካውያንን/ትን ለተለያዩ ጉዳዮች እና በሃሳብ ኃይላቸው የርዕዮት ዓለም ትግል በማካሄድ ማን አሸናፊ እንደሆነ ያውጃሉ ይህንን የሚያደርጉበት ምክንያት AK-47ን ስለያዙ አይደለም፣ ሆኖም ግን ህዝቦች የያዟቸው ሀሳቦች ትክክል ለመሆናቸው እና ለማሳመን 47 ምክንያቶችን መደርደር ስለሚችሉ ነው፡፡ የእኔ ትችቶች እያንዳንዳቸው የኢትዮጵያ ባለእራይዎች፣ አዲስ ሀሳብ አመንጭዎች እና አሳቢዎች ለእራሳቸው፣ ለእርስ በእርሳቸው አገሪቱ በምን ዓይነት መልክ እንደምትለወጥ ለሀገራቸው እና ለጋራ የወደፊት እጣፈንታቸው በመተሳሰብ  የሚያድርጓቸው ተግሎች እና ጥረቶች ሁሉ አዲሱን ትውልድ ለፋናወጊ ለውጥ ይቀሰቅሳሉ የሚል ሚስጥራዊ ተስፋ አለኝ፡፡

በማንኛውም ሀገር ላይ ለውጥ ለማምጣት ማንም ቢሆን ወጣቱ ትውልድ ስለእራሳቸው፣ ስለሀገራቸው እና ስለወደፊት ዕጣፈንታቸው እንዴት ባለ ሁኔታ ማሰብ እና ለለውጥ መዘጋጀት እንዳለባቸው ማስተማር አስፋላጊ እንደሆነ እምነት አለኝ፡፡ የእኔ  ትችቶች በአንድ ቀን ወጣት ኢትዮጵያንን/ትን በማነሳሳት በጎሳ ክፍፍል ላይ፣ በጭቆና እና በግፍ አገዛዝ ላይ በማመጽ ፍቅርን እና አንድነትን በማወጅ ሃሳብን በነጻ በመግለጽ በሀገሪቱ ላይ ነጻነቱን እንደሚጎናጸፍ ሚስጥራዊ ተስፋ አለኝ፡፡ በኢትዮጵያ በአንድ ወቅት በጎሳ ማንነታቸው ወይም ብሄራቸው ላይ ኩራትን የማይሹ ሆኖም ግን ደስታን እና ፍቅርን የሚያመጡ ወጣት ኢትዮጵያውያን/ት ትውልዶች ሊመጡ እንደሚችሉ አውቃለሁ፡፡

ለኢትዮጵያ የፖለቲካ እና ማሃበራዊ ቀውስ ምስቅቅል ችግሮች መፍትሄ ምንጮች ምንድን ናቸው ብዬ አምናለሁ? እውነት፣ ይቅርታ አድራጊነት እና እርቀ ሰላም ማውረድ፡፡ በኢትዮጵያ የሰብአዊ መብትን በማስከበር ትግል ውስጥ እነዚህ መርሆዎች የመሰረት ድንጋይ ናቸው፡፡ እኔ ከማንኛውም ቡድን ጋር ድብቅ የፖለቲካ ወይም ከማናኛውም ተመሳሳይ ቡድን ውስጥ የሚሳሳብ ድብቅ አጀንዳ የለኝም፡፡ በማንኛውም እረገድ ፖለቲካዊ ፍላጎት የለኝም፡፡ ከብዙ ጊዜ ጥናት ጀምሮ እንደተማርኩት ስልጣን የማታለያ መሳሪያ ነው እናም ፍጹም የሆነ ስልጣን ፍጹም የሆነ ማታለልን ያመጣል፡፡ ምን ዓይነት የፖለቲካ ስልጣን እንዳለ እና ለህዝቦች መልካም ምኞት እና ነጻነት መደረግ እንዳለበት እምነት አለኝ፡፡ የእኔ ብቸኛው ትልቁ ጉዳዬ የኢትዮጵያ ህዝብ ደህንነት እና የነጻነት ሁኔታ ነው፡፡ በመሬት ላይ እንዳለ እንደ ማንኛውም ነጻ ህዝቡ ሊቀበለው እና በሰላም ሊኖር ያገባል፡፡ ለዚያም ነው እኔ እንደ ሰብአዊ መብት ተጋሟጋች ፍቅር፣ ዘላቂ እና ከፍተኛ ጥረት ማድረግ ለሚሉት ከፍተኛ ዋጋ የምሰጠው፡፡

ውሱን የሆኑ እኔ የምወዳቸው ኃይሎች አሉ፡፡ እኔ ይኸ የሞራል ስብዕና ግዴታን መወጣት ነው ብዬ አምናለሁ፡፡ በእያንዳንዱ ዜጋ ያለው ኃይል ስልጣንን ከህግ አግባብ ውጭ ለሚጠቀሙ እና የሰብአዊ መብትን ለሚደፈጥጡ እውነትን እስከአፍንጫው መንገር መቻል ነው፡፡ እያንዳንዱ ሰው አምላክ የሰጠውን/የሰጣትን ኃይል በመጠቀም ህዝቦች ወደ ሰላም እና አንድነት እንዲመጡ ዜጎች እንዲበታተኑ እና በጥላቻ ፖለቲካ እንዲታመሱ ሌት ከቀን አበርትተው የሚሰሩትን የዕኩይ ምግባር አራማጅ አምባገነኖች መቃወም አስፈላጊ ነው፡፡ በቀልን የሚኮለኩል እና አይን ያጠፋን ዓይኑን ለሚለው ማንንም እውር ለሚያደርግ ፍልስፍና ወይም ርዕዮት ዓለም በህሊናዬ ወይም በልቤ ውስጥ ምንም ዓይነት ቦታ የለም፡፡

ትችቶቼን በምጽፍበት ጊዜ የሚገጥሙኝ ልዩ ተግዳሮቶች አሉን? ጥቂት፡፡ ከእነዚህ መካከል ምን ለማለት እንደምፈልግ በትክክለኛው መንገድ የሚገልጹትን ትክክለኛ የሆኑ ቃላትን፣ አዲስ ሀሳቦችን እና ሀረጎችን ፈልጎ ከማግኘት ላይ ነው፡፡ በርካታ ከሆኑ ስያሜዎች (አዲስ ቃላትን መፍጠር) ጋር እፋጠጣለሁ እናም ትችቶቼን ለማቅረብ ጥረት አደርጋለሁ፡፡

የአንድን ሰው  የፖለቲካ ቀንቋ አጠቃቀምን በመግለጽ ለማስደንገጥ እና ለማስፈራራት እና ለማሸማቀቅ፣ ለማበሳጨት እና ቃላትን በማዥጎድጎድ ለመመበጥበጥ፣ ለመረበሽ እና የበላይነትን ለማሳየት፣ ለማሸነፍ እና ለማስፈራራት፣ ቀልብን ለማሳጣት እና በድን ለማድረግ፣ ወኔቢስ ለማድረግለ እና ጥላሽት ለመቀባት፣ ድፍረትን ለማሳት እና ንዴትን ለመቆስቆስ እና የጠላትነት ስሜት አቅጣጫን ለማሳጣት ዘራፊነት የሚለውን ያልተሞረደ ቋንቋ እና የአዋራጆች ላይ አንዳንድ አዲስ ቃላቶች ዘይቤ አነጋገሮች ለማምረት ሞክሪያለሁ፡፡ መለስ በእነዚህ ዓይነት መረን የወጣ የቋንቋ አጠቃቀም የተካነ ነበር፡፡ የአፍሪካን አምባገነኖች የመጨረሻው ደረጃ ለመገለግጽ ዘራፊነት የሚለውን ቃል እጠቀማለሁ፡፡ በኢትዮጵያ የሰለጠኑ ሙሰኞችን ለመገለጽ ሙስና ሰሪዎች በሚል እገልጸዋለሁ፡፡ በኢትዮጵያ ያለውን ገዥ አካል ሚስጥራዊነት እና ሙሰኝነት ለመግለጽ ሚስጥሮሙሰኛ በሚል ሀረግ አያይዘዋለሁ፡፡ ሁሉንም ኢትዮጵያውያን/ት በአንድነት እንዲነሳሱ ለመጠየቅ ህብረት እና አንድነት የሚሉ ቃላትን እጠቀማለሁ፡፡ “ሰብትብብር” እና “ወጣት ትብብር” እያልኩ የምጠራውን ልዩ የሆነ ትብብር ለማጠናከር ሁሉም ኢትዮጵያውያን/ት ጥረት እንዲያደርጉ እጠይቃለሁ፡፡ “ሰብትብብር” በጎሳ ላይ ወይም ደግሞ በብሄር ላይ ያልተመሰረተ ሆኖም ግን ለሰው ልጅ ክብር እና ለአፍሪካ “ትብብር” ለቆሙት ለዋናዎቹ ዓለምአቀፋዊ የሰብአዊ መብት እሴቶች መከበር እንደገና በድጋሜ እጠይቃለሁ፡፡ ወጣት ትብብር በእኔ አስተሳሰብ ቀላል የሆነ ሀሳብ ነው፡፡ ነገር ግን እንደ እኔ እና እንደእናንተ ማለትም በአምባገነንነት ጸንተው ለቆሙት፣ በሙስና ለተዘፈቁት እና ስልጣናቸውን ከህግ አግባብ ውጭ ለሚጠቀሙት ይህ ቃል ባይተዋር ነው፡፡ “ዲፕሎማሲያዊ ክስረት” ማለትም የዩናይትድ ሰቴትስ የሰብአዊ መብት አስመሳይነት ለሚለው ቃል ያያዝኩት ነው፡፡ በእርግጥ “የጡመራማሳጣት” አለ፡፡ ሌሎች ጥቂቶች አሉ ሆኖም ግን በዌብስተር ዲክሽነሪ ላይ የአርትኦ ስራ ለሚሰሩ ማናቸውንም በማንኛውም ጊዜ ለሚይዙ መርሆዎችን ያሰርጻሉ ብዬ አልጠብቅም፡፡

ትችቶችን መጻፍ አስደሳች ነገር ነውን? አይደለም፣ ይልቁንም ሌሎች ሰዎች እንዲደሰቱ ማድረግ ነው፡፡ እዚህ ላይ ባቆም የተሻለ ነው፡፡ በእኔ ሳምንታዊ የቃላት ውሱንነት ምክንያት ሀሳቤን እገታለሁ፡፡ የእኔን አንባቢዎች ጊዜ ወይም ትዕግስት ለማባከን አልፈልግም፡፡ በየሳምንቱ ለምን እንደምጽ የሚከተለው ለአንባቢዎቸቼን አመሰግናለሁ፡፡   በኢትዮጵያ ለሰብአዊ መብቶች መከበር የሚደረገው ተጋድሎ ይቀጥላል፡፡ የኦማር ክሀያምን አባባል በመዋስ ተንቀሳቃሿ ጣት ሁልጊዜ ሰኞ ትጽፋለች፡፡ እናም ከተጻፈ በኋላ ወደሚቀጥለው ሰኞ እና ከዚያም በመቀጠል ታልፋለች፡፡

የመጀመሪያው ምስጋናየ በየሳምንቱ ለበርካታ ዓመታት ትችቶቼን ሲያወጡ ለነበሩ ለኢትዮጵያ ድረ ገጸ አርታይዎች ነው፡፡ ልዩ ናቸው፡፡ ያለእነርሱ ድጋፍ እና ማበረታታት ብዛት ካለው አንባቢየ ጋር መገናኘት አልችልም ነበር፡፡ ለእኔ እነዚህ የድረ ገጽ አርታዒዎች ያልተዘመረላቸው ጀግኖቸ ናቸው፡፡ በማንኛውም በቻልነው ነገር ሁሉ ልናግዛቸው እና ልንረዳቸው ይገባል፡፡

በእርግጥም ልባዊ የሆነው ምስጋናየ በትዕግስት ሲሰሩ ለብዙ ጊዜ ሲሰቃዩ ለቆዩት አንባቢዎቼ፣ ረዥሞቸቹን ትችቶች ለበርካታ ዓመታት  በድረ ገጾቻቸው ሲያትሙልኝ ለቆዩት ሁሉ ምስጋናየ ይድረሳቸው አሜን!

ኢትዮጵያ በክብር ለዘላለም ትኑር!

ነሐሴ 29 ቀን 2006 ዓ.ም