ጠቅላይ ሚኒስትሩ ለመጨረሻቸው እንዲዘጋጁ ንገሩልኝ

በፍቃዱ ዘ ኃይሉ

ዋሆች ኢትዮጵያ ‹‹ግብርና መር ኢንዱስትሪ›› የተባለ ስትራቴጂ ትከተላለች ብለው ያምናሉ፣ እውነታው ግን ኢትዮጵያ የምትከተለው ‹‹መለስ መር ፖለቲካ›› መሆኑ ነው፡፡ ሁሉም ነገር ‘መለስ’ እና ‘መለስ’ ብቻ ነው፡፡ የሕወሓት፣ የኢሕአዴግ፣ የኢትዮጵያ

መሪ መለስ ናቸው፡፡ ተነቦ፣ ተነቦ ቀለሙ የለቀቀው ‘Agricultural Development Led Industrialization’ም ሆነ አሁን በወረት እየተነበበ ያለው ‘African Development: Dead Ends and New Beginnings’፣ ሁለቱም የተደረሱት በእርሳቸው ነው፡፡

አንድ ሰው በግል ቤተ ሙከራው የፈለገውን ያህል ጊዜ የተለያዩ አማራጮችን ቢሞክር፣ የተለያየ ጊዜ ቢወድቅ ችግር ላይኖረው ይችላል፡፡ ቤተ ሙከራው ሃገር፣ መሞከሪያዎቹ ደግሞ ሕዝቦች ከሆኑ ግን የሚፈጠረው ስህተት አስቀያሚ መሆኑ አይቀሬ ነው፡፡ ጉዳዩ መራር የሚሆነው ደግሞ መሳሳቱ ሳይሆን ሕዝቡን ደግሞ፣ ደግሞ መሞከሪያ የማድረግ ምኞቱ ካሻቀበ ነው፡፡ የኢትዮጵያው ጠቅላይ ሚኒስትር ከዚህ የተለየ ምንም ሲያደርጉ አላየሁዋቸውም፡፡ ደግነቱ ቤተሙከራይቱ ሕገ-መንግስት አንድ ተመራማሪ ለስንት ዓመታት ደጋግሞ መሞከር እንደሚችል ያስቀመጠው ቀነ ገደብ የለም፡፡

አንዳንዴ እኛስ አንዴ ስማችን ተቃዋሚ ነው፤ ነገር ግን የኢሕአዴግ ሰዎች ራሳቸው እንዴት ሰውየውን ‘በቃህ’ አይሏቸውም? አይሰለቻቸውም እንዴ! ‘እስኪ ደግሞ በትረ መንግስቱን እኛም እንጨብጠው እና ያቅማችንን እንሞክር’፣ ሳይሏቸው ለምን ቀሩ? እውን የመለስ አመራር ላይ ጠንካራ እምነት ስላላቸው ነው? እውን መሪውና ተመሪዎቹ በሐሳብ አንድ መሆን ችለው ነው? አይመስለኝም፡፡ ራሴን እየጠየቅኩ፣ ራሴ እየመለስኩ በተቀመጥኩበት የመጣልኝን ሐሳብ ‘እንደወረደ’ ከዚህ በታች አሰፈርኩት፡፡

የተተኪ እጦት?
የኢሕአዴግ ሰዎች አቶ መለስ ‹‹ስልጣኔን የመልቀቅ ፍላጎት›› አለኝ ብለው ሲናገሩ ይደነግጣሉ፡፡ ‹‹እባክዎ አይውረዱብን›› እያሉ በየራሳቸው ልሳኖች ይማፀናሉ፡፡ ደጋፊዎቻቸውን የጠቅላይ ሚኒስትሩ መውረድ የሚያስደነግጣቸው ከሆነ ሰውየው መተኪያ የላቸውም ማለት ነው፡፡ አራት ሚሊዮን አባል አለኝ የሚለው ኢሕአዴግ ውስጥ አንድ እሳቸውን የሚተካ ሰው ከሌለ ፓርቲው ሃገሪቷን ለመምራት አይበቃም ማለት ነው፡፡ አራት ነጥብ፡፡ ስለዚህ ኢሕአዴግ መንበረ ስልጣኑን በገዛ ፈቃዱ ለሚችሉ መስጠት አለበት እንጂ፣ እንዴት በአንድ ሰው ጫንቃ ላይ አገሪቷን ይጥላታል? ለምንስ ሰውየውን ‹‹ያለግል ፍላጎታቸው›› የማይሆን ኃላፊነት ያሸክማቸዋል?

እኔ ግን ለትህትና ብሎ ራሱን ዝቅ አድርጎ ካልሆነ በቀር፣ በፓርታቸው ውስጥ አንድ እሳቸውን የሚተካ ይጠፋል ብዬ አላምንም፡፡ ታዲያ ምንድነው ምክንያቱ?

እነእከሌን ያየህ ተቀጣ?
ስዬ፣ ታምራት ላይኔ . . . እውን የታሰሩት በተነገረን ‹‹ሙስና›› [ብቻ] ነው? ታዲያ የፖለቲካ ልዩነታቸው ከአቃቢ ሕጉ ክስ ለምን ቀደመ? በመለስ መንበረ ስልጣን ላይ ድንጋይ የሚወረውሩ የገዢው ፓርቲ ሁነኛ ሰዎች፣ ሁነኛ ቅጣት ተቀጥተዋል፡፡ ቀጣዩ ደፋር ማነው?

የዘንድሮውን ሹም ሽረት ስንመለከት፡ ስም እና ልምድ ያላቸው የኢሕአዴግ ባለስልጣናት ቦታቸውን በመልቀቅ፣ መለስን ሊተኩ ቀርተው ቀና ብለው ለማየት እንኳን የሚሽቆጠቆጡ አዳዲስ ፖለቲከኞች ተሹመዋል፡፡ አብዛኞቹ ከአቶ መለስ አመራር ጋር የተሰጣቸውን ከባድ ኃላፊነት ለመወጣት እንደሚጥሩ መናገር ጀምረዋል፡፡ ‹‹ሁሉንም በአንድ ሰው መተካት›› የሚል ቅፅል ስም የተሰጠው የኢሕአዴግ ባለስልጣናት የመተካካት ሥራ ጥሩ የሰሩ የሚመስሉ፣ በሕዝብ ዘንድ አንፃራዊ ተቀባይነት ያገኙትን ባለሥልጣናት ያሽቀነጠረ ነበር፡፡

ታዲያ ተተኪዎቹ መለስን ለመተካት ጠንክረው ይሰራሉ፣ ወይስ የታላላቆቻቸው የመሽቀንጠር ዕጣ ፈንታ እንዳይደርስባቸው ሕዝብ ይበድላሉ? እንደኔ፣ እንደኔ ሕዝብ ቢያበሳጩ የሚያዋጣቸው ይመስለኛል፡፡

ሃብትና ንብረት፡ ቁልፉ በሰውየው እጅ ነው?
‹‹እላይ ቤት›› ያሉ ሰዎች የፓርላማ አባላት ደሞዝ አነሰ ብለው ለምን አይሟገቱም? ደሞዛቸው ስለሚበቃቸው አይደለም፡፡ የነሱ ደሞዝ እንኳን ለነሱ ዓይነቱ ውስኪ አውራጅ፣ መኪና አማራጭ ቀርቶ ለኔ ዓይነቱ ምስኪን ራሱ ለወር የሚበቃ ሊባል አይችልም – በዛሬ የኑሮ ውድነት፡፡ የቤት እና የመኪና ጥቅማጥቅሙ አንጀታቸውን አርሷቸውም አይደለም – ዘላቂ እንዳልሆነ ያውቃሉና፡፡ የፓርላማ ደሞዛቸው ትዝ ብሏቸው ስለማያውቅ ነው፡፡ ተቃዋሚዎች እንኳን ጉዳዩ አሳሳቢ ነውና እንዳያነሱት ‹‹ለሕዝብ ሳይሆን፣ ለደሞዛቸው›› ብለው መሳለቂያ እንደሚያደርጉዋቸው ስለሚያውቁ እንደማይቻል ቻሉት፡፡ ለነገሩ አሁን በፓርላማ አንድ ተቃዋሚ ብቻ ስለሆነ ያለው፣ የአንድ ሰው ችግር የሃገር ችግር አይደለም፡፡

አንዳንዴ ምናለ እኒህ ባለስልጣናት፣ የሰውየው መጠቀሚያ ከሚሆኑ ወደ አውሮፓ ወይም አሜሪካ ተሰደው ከቅኝ ግዛት ነፃ ቢወጡ ልትሉ ትችላላችሁ፡፡ ይሄን ማድረግ ግን አይችሉም፡፡ አብዛኛዎቹ እዚህ አገር ከፍተኛ ሃብት አካብተዋል፤ የዚያ ሃብት ደህንነት በኢሕአዴግ የበላይነት ነው የሚረጋገጠው፡፡ ኢሕአዴግ ውስጥ መፍረክረክ ከተከሰተ አጋጣሚውን ተከትሎ ተቃዋሚዎች ስልጣን ቢይዙ ‘ሃብቱ ከየት መጣ?’ ልንባል እንችላለን የሚል ስጋት እንዳላቸው መጠርጠር አያቅተንም፡፡ ሌላኛው ስጋታቸውም በአቶ መለስ ላይ ቢያምፁ ሃብት ንብረታቸው አንድም የነሱ አይሆንም አሊያም በሙስና የተገኘ በሚል ተከርቸም ያስወረውራቸዋል፡፡ ይህንን ሲያስቡት ሰውየው ‹‹ሺ ዓመት ቢገዙስ›› የሚሉ አይመስላችሁም፡፡ እኔን ይመስለኛል፡፡

የሚተባበር የለም?
የመለስን በትረ ስልጣን ለሚመኙ የኢሕአዴግ ሰዎች ሌላኛው ትልቁ ችግር፣ የሚተባበር ሰው መጥፋቱ ነው፡፡ ሁሉም ድንጉጥ ነው፡፡ ድንገት መለስ ላይ የምሰነዝረው ተቃውሞ በፓርቲው ውስጥ ደጋፊ ቢያጣ እና ባይሳካ የኔ መጨረሻ ምን ይሆናል ብሎ ማሰቡ፣ ሐሳቡ ራሱ ያስደነግጠዋል፡፡ በሕወሓት መሰንጠቆች ውስጥ ‹‹ተገንጥለው›› የባከኑት ታጋዮች የሚተባበራቸው አጥተው ነው፡፡ ምክንያቱም ደግሞ በሳቸው ወንበር ላይ የተቃጣ ማናቸውም ቁጣ መጨረሻው መቀሰፍ መሆኑ ነው፡፡ አንድ ሰው ያልሆኑትን ሰው፣ በአንድ ሰው ደግሞ አይሞከርም፡፡ ‹‹ጎመን በጤና›› ይሏችኋል ይሄኔ ነው፡፡ ለነገሩ ከዚህ አገባብ አንፃር ቬጂቴሪያን ካልሆኑ በቀር ‹‹ጮማ በጤና›› ቢባል ይሻላል፡፡

ለክፉም ለደጉም፡ መለስ ይተማመኑ ወይስ ይዘጋጁ?
እንደኔ፣ እንደኔ ጠቅላይ ሚነስትሩ ከላይ ባነሳኋቸው ምክንያቶች ብቻ መንበረ ስልጣኔን ማንም አይደፍርብኝም ብለው ማሰብ የለባቸውም ብዬ አስባለሁ፡፡ ድንገት ተተኪ ሊገኝላቸው፣ ድንገት ሌሎች ላይ በደረሰው የማይቀጣ/የማይማር፣ ድንገት ሃብት ንብረት የሌለው ወይም ሃብት ንብረቱን የከዳ፣ ድንገት የማስተባበር አቅሙ የበረታ ተቀናቃኝ ሊመጣባቸው ይችላል፡፡ ስለዚህ ከወዲሁ መዘጋጀት አለባቸው፡፡

የሃገራችን መሪዎች፡- የቀዳማዊ ኃይለሥላሴም ሆነ የኮሎኔል መንግስቱ መጨረሻ የሚነግረን አንድ ነገር አለ፤ የመለስን መጨረሻ፡፡ ጠቅላይ ሚኒስትሩ ለመጨረሻቸው እንዲዘጋጁ ንገሩልኝ!!!