የአቶ ኤርሚያስ ለገሰ “ባለቤት አልባ ከተማ”
በሶፍት ኮፒ ተሰርቶ በኢንተርኔት የተሰራጨውን መጽሐፍ አሁን አንብቤ ጨረስኩት (ነሐሴ 27፡ ከምሽቱ ሶስት ሰዓት ላይ ማለቴ ነው)፡፡ መጽሐፉ በስውር አልደረሰኝም፡፡ እዚሁ ፌስቡክ ላይ Book for All ከሚባለው ግሩፕ ነው ያገኘሁት፡፡ እርግጥ የደረሰኝ ኮፒ ለህትመት የተዘጋጀው ሳይሆን የመጽሐፉ የመጀመሪያ ረቂቅ ይመስለኛል፡፡
ያም ሆነ ይህ መፅሐፉን አነበብኩት፡፡ ሆኖም በመጽሐፉ ያነበብኩት ነገር ብዙም አላስደነቀኝም፡፡ የቀድሞው ም/ሚኒስትር ስናየው፣ ስንሰማውና በግሉ ፕሬስ ስናነበው የነበረውን ነው መልሰው የጻፉት፡፡ ያ ማለት ግን ዋሽተውናል ማለት አይደለም፡፡ አቶ ኤርሚያስ ለጊዜው ያልተናገሯቸው በርካታ ነገሮች ሊኖሩ እንደሚችሉ ብረዳም አሁን የጻፉት ነገር በኢህአዴግ አባላት ሲነገረን ከነበረው በምንም መልኩ የሚለይ አይደለም፡፡ አቶ መለስ ዜናዊን ጨምሮ ሌሎች አንጋፋ የኢህአዴግ መሪዎች በልዩ ልዩ የግምገማ መድረኮች ሲያወጧቸው የነበሩት ሪፖርቶች ከዚህ ቢብሱ እንጂ ከዚህ የሚያንሱ አይደሉም፡፡ ለአብነትም አቶ መለስ “ቦናፓርቲስታዊ የመበስበስ አደጋዎች” እና “ድርጅታችን ከእንጥሏና ከጭንቅላቷ መግማት ጀምራለች” በሚሉ ርዕሶች የጻፏቸውን ሪፖርቶች መጥቀስ ይቻላል፡፡
የአቶ ኤርሚያስ መጽሐፍ መልዕክቱ ለኢህአዴግ ተቃዋሚዎች አልመሰለኝም፡፡ ከዚህ ይልቅ አቶ ኤርሚያስ ለኢህአዴግና ለአባላቱ ማስጠንቀቂያ ያስተላለፉበት የተቆርቋሪነት ድርሳን ሆኖ ነው ያገኘሁት፡፡ አቶ ኤርሚያስ በጥቅሉ “ድርጅቱ የተመሰረተበትን ዓላማ እየሳተ በስህተት ላይ ስህተት እየጨመረ ሄዷል፤ ለወደፊቱ በዚሁ መንገድ ከቀጠለ የህልውናው ነገር አጠያያቂ ይሆናል፤ ሀገሪቷም አደጋ ላይ ተወድቃለች፤ ስለዚህ አመራሩና አባላቱ የድርጅቱን ህልውና ማስቀጠል ከፈለጉ ተገቢ የማስተካከያ እርምጃዎችን በጊዜ መውሰድ አለባቸው” የሚል መልዕክት ነው ያስተላለፉት፡፡
ይህ የአቶ ኤርሚያስ ስጋት በአቶ መለስ ዜናዊ በተለያዩ ጊዜያት ተንጸባርቋል፡፡ አቶ መለስ “የቆሰለው ጅብ ታሪክ”ን እያነሱ “ኢህአዴግ ራሱን እያረመና እያስተካከለ ካልሄደ እንደቆሰለው ጅብ ራሱን በልቶ ይጨርሳል” በማለት ጽፈዋል፡፡ በሌላ ጊዜም “የኢህአዴግ ዋነኛ ጠላቱ ተቃዋሚው ሳይሆን ኢህአዴግ ራሱ ነው፤ ኢህአዴግ ራሱን ካልጠበቀ ህልውናው ለአደጋ ይጋለጣል” በማለት በአደባባይ ተናግረዋል፡፡ ስለዚህ የኢህአዴግ አባላትና ደጋፊዎች ሰውየውንና መጽሐፉን ከማጥላላት ይልቅ የአቶ ኤርሚያስን ምክር በአዎንታዊነት ተመልክተው ለተግባራዊነቱ ሊንቀሳቀሱ ይገባል እላለሁ፡፡
—–
በአንጻሩ ግን አንድ ጥያቄ አለኝ፡፡ “እነኝህ በስልጣን ማማ ላይ ከቆዩ በኋላ ወደ ውጪ እየኮበለሉ የኢህአዴግን እኩይነት የሚያወጉን ባለስልጣናት ራሳቸው ምን ያህል ንጹህ ናቸው?” የሚል፡፡ እንዲህ የምለው ከኢህአዴግ አፈንግጠው ወደ ወጪ ከሚጠፉት ባለስልጣናት መካከል የብዙዎቹ ግለ-ታሪክ የተበላሸ መሆኑን ስለማውቅ ነው፡፡ ለምሳሌ የኦህዴድና የኢህአዴግ ፖሊት ቢሮ አባልና የኦሮሚያ ክልል የአስተዳደርና ጸጥታ ሃላፊ የነበሩት አቶ ዮናታን ዲቢሳን እንውሰድ፡፡ እኝህ ግለሰብ በየካቲት 1993 ከተሰደዱ በኋላ ኢህአዴግ የሰራቸው ወንጀሎች በማለት ብዙ ነገር ለፍልፈዋል፡፡ ነገር ግን በወቅቱ ስልጣን ላይ ከነበሩት የኦህዴድ (ኦፒዲኦ) መሪዎች መካከል የርሳቸውን ያህል በወንጀል የተነከረ ግለሰብ ያለ አይመስለኝም፡፡ በታችኛው እርከን (ዞን፣ ወረዳ፣ ቀበሌ) የነበሩት የኦሮሚያ ክልል አስተዳደር አካላት ተጠሪነታቸው ለርሳቸው ነበር፡፡ በመሆኑም በኦሮሚያ ክልል የሚካሄዱ እንቅስቃሴዎችን በቅርበት ይቆጣጠሩ ነበር፡፡ በዚህ ስልጣናቸው ተጠቅመው የከወኗቸው ብዙ ጉዶች አሉ፡፡
እኝህ ግለሰብ በሺህ የሚቆጠሩ የኦሮሞ ልጆች በኦነግ ደጋፊነት ተከስሰው እንዲታሰሩ፣ እንዲገደሉ፣ እንዲሰደዱና ደብዛቸው እንዲጠፋ የተደረገበትን ኦፕሬሽን ካቀናበሩትና ካስፈጸሙት አንዱ ናቸው፡፡ የኦሮሚያ መሬቶችን አላግባብ እየቆረሱ ለጎረቤት ክልሎች ሰጥተው ካበቁ በኋላ በሌሎች ክልሎች የተከለሉ ኦሮሞዎች “ወደ ኦሮሚያ ክልል መጠቃለል እንፈልጋለን” የሚል ጥያቄ ሲያነሱ አይቀጡ ቅጣት እንዲቀጡ አድርገዋል፡፡ በኦሮሚያ ክልል በሚኖሩ የአማራ ተወላጆች ላይ በተካሄዱ የመግደል፣ የማስደንበርና የማፈናቀል ዘመቻዎችም አውራ ተሳታፊ እንደነበሩ በሰፊው ይታወቃል (ወደ ውጪ ከኮበለሉ በኋላ በወለጋ ክፍለ ሀገር ከሆሮ ገድሩ አውራጃ ለተናፈቀሉ የአማራ ተወላጆች ተቆርቋሪ ሆነው የአዞ እምባ ማንባታቸው በጣም አስደምሞኛል)፡፡
አቶ ዮናታን በተለይም ለሃያ ዓመታት የግጭት ቀጣና በሆነው የአዋሽ-ቦርዶዴ-ሚኤሶ-አፍደም መስመር ላይ (የባቡር ሐዲድን ተክትሎ ባሉት ከተሞች) በኦሮሞና በሶማሌ ወንድማማች ህዝቦች መካከል በየሶስት ወሩ ለሚቀጣጠለው ግጭት ኢ-ፍትሐዊ ሽፋን በመስጠት ግጭቱ እንዳይረግብ ከሚያደርጉ ግለሰቦች ዋነኛው ነበሩ፡፡ ግጭቱን በሰላማዊ መንገድ ለመፍታት የሚንቀሳቀሱ የዞንና የወረዳ ስራ አስፈጻሚዎችን አስረዋል፤ ከስራ አባረዋል፡፡ በግጭቱ የምንጊዜም ተጠቂ የሆኑት የአሰቦትና የሚኤሶ አርብቶ አደሮች ራሳቸውን የሚከላከሉባቸውን የጦር መሳሪያዎች በመንጠቅ ከሩቅ አካባቢ በሚመጡ ቆለኛ የከብት ዘራፊዎች በተደጋጋሚ እንዲገደሉና እንዲዘረፉ አድርገዋል፡፡ በዚህ ጥቃት የተንገበገቡት የሀረርጌ ሽማግሌዎች ለአቤቱታ ወደ ጨፌ ኦሮሚያና የፌዴራል መንግሥት ሲሄዱ ሰድበው በማዋረድ መልሰዋቸዋል፡፡
እኝህ ነውረኛና ወንጀለኛ ግለሰብ ናቸው እንግዲህ ወደ ውጭ ሄደው የኢህአዴግን አውሬነት የሚያረዱን፡፡ በልዩ ልዩ ሚዲያዎች ቀርቦ ሲጠየቅ “ለኦሮሞ ህዝብ ስለተቆረቆርኩና ኢሕአዴጎች በነጻነት ስላላሰሩኝ ሀገር ጥዬ ወጣሁ” ብሎናል፡፡ የሚገርመው ደግሞ ለኦሮሞ ህዝብ እታገላለሁ የሚለው ኦነግ “የኦነግ ደጋፊዎች ናችሁ” በሚል ስም የኦሮሞ ወጣቶችን ቁምስቅላቸውን ሲያሳይ የነበረውን ነውረኛ ግለሰብ በሁለት እጆቹ መቀበሉ!! አይ ፖለቲካ!! ውቢቷ እመቤት!!
አቶ ዮናታን ከሀገር የጠፉት በወቅቱ ኦሮሚያን በስውር ይመራ ከነበረው ሰለሞን ተስፋይ (ጢሞ) ጋር በመጣላታቸው ነው እንጂ ለኦሮሞ ህዝብ በመቆርቆራቸው አይደለም፡፡ ከሰለሞን ጋር በጥቅም ተጋጩ፤ ከርሱ የሚሰጣቸውንም ትእዛዝ አልቀበልም እያሉ ማስቸገር ጀመሩ፡፡ በመሆኑም “ቆይ! የሚል ዛቻ ደረሳቸው፡፡ በዚህም ቀን ከሌሊት እንቅልፍ አጡ፡፡ በመሀሉ እርሳቸውን የሚወዱ ሰዎች ለአጭር ጊዜ ስልጠና ወደ አውሮጳ ላኳቸው፡፡ ዮናታንም በዚያው ኮበለሉ፡፡ ታሪካቸው ይኸው ነው፡፡ (በነገራችን ላይ በመጋቢት 1993 ህወሐት ለሁለት ሲከፈል አቶ ሰለሞን ተስፋይ ከነ ስዬ አብረሃ ጋር ከድርጅቱ ተባረዋል፤ አቶ ዮናታን የሰለሞንን ዛቻ ችሎ ለአንድ ወር ቢቆይ ኖሮ ከሀገር ባልኮበለለም ነበር)፡፡
—–
የመጽሐፉ ፀሐፊ የሆኑት አቶ ኤርሚያስ ወንጀለኛ እንዳልሆኑ አምናለሁ፡፡ እኔም ወንጀለኛ ናቸው ከሚል አይደለም ይህንን የጻፍኩት፡፡ ነገር ግን ወደ ውጭ የኮበለሉት ባለስልጣናት ጠቅላላ ታሪካቸው መጠናት አለበት ባይ ነኝ፡፡ ሰውዬው እንደ ዶ/ር ነጋሶ ጊዳዳ ከፖለቲካ ተሳትፎው ውጪ በግል የሰራው ወንጀል ከሌለ እሰየው! አሰላለፉን መቀየር ይችላል፡፡ ሰውየው እንደ ዮናታን ዲቢሳ በደም የጨቀየ ዶሴ በእጁ ላይ እያለ የኢህአዴግን እኩይነት የሚዘበዝብልን ከሆነ ግን በጭራሽ አንቀበለውም፡፡ ወንጀለኛ ምንጊዜም ቢሆን ወንጀለኛ ነው፡፡ የፖለቲካ አሰላለፍ ለውጥ ወንጀለኛነትን አይፍቀውም፡፡ አንድ ሺህ አንድ ነጥብ!!!