ወዮ ዓለማያ – ወርቁ ለገሠ
የሃረር ጠባይ ሚስጥር የፍቅር ሁሉ ፍጻሜ
አለማያ የወዳጅነት ልክ ማሳያ የመስዋዕትነት ጣሪያ
ወዙ ነጥፎ እስኪረታ
ዝም ነው የሱስ ውለታ
ሃረርጌ አለቀሰ እንባውም ፈሰሰ
የክፉ ቀን ጓዱን ሰርክ እያስታወሰ
ወዮ ዓለማያ የሃረር ሲሳይ
ባህርም እንደሰው ሞት ይሞታል ወይ
ማነው የገደለው ብዬ አልጠይቅ እኔ
በማን ዕጅ አለፈ ብየ አልልም እኔ
የደሙን አባላ በሃርርጌ ወዝ ላይ እያየሁኝ ባይኔ
የየዋህነቱን የታዳጊነቱን የአፍቃሪነቱን ልክ መቁጠር ቢታክትም
ርግማን ሆኖብን ባበሻ ምድር ላይ ደግ አይበረክትም
ይናገር እያሱ ከሞት ተመላሹ
ይናገር ተፈሪ በባህር ደጋሹ
በአለማያ ነገር የማይወሻሹ
ያ ሃረሩ ልቤ ያ ሃሩሩ ልቤ የተንሰፈሰፈው
ያን ኩሩ ዓለማያ የዛን ጀግና ባህር መቃብሩን ሲያየው
ከጨው ልክ ያለፈ ከሬት የመረረ እንባውን የረጨው
የዓልማያን ነገር ማትረፍ እየቻለ ቸልታው ቢቆጨው
እስከመጨረሻይቱ ጠብታ እስከ ህይወቱ ህቅታ
ወዙ ነጥፎ እስኪረታ
ዝም ነው የሱስ ውለታ
አረሱት ይሉኛል የሚያርስ ይረሳቸው
ህይወቱን ሰውቶ ህይዎት በሰጣቸው
ደረቱን በብረት ቀረደዱት አሉ
ለእፍኝ ማሽላ ማተብ በጣሽ ሁሉ
አይ የሰው ውለታ አይ የሰው ሰውነት
ምኑን ለማረሻ ምኑንስ ለብረት
እስከመጨረሻይቱ ጠብታ
እስከህይወቱ ህቅታ
ወዙ ነጥፎ እስኪረታ
መቼ እንድህ የሱስ ውለታ
አበሻ ምን ሆኗል አበሻ ታክቶታል?
ለባህር መሞቱን ዘንድሮስ ትቶታል?
ወየውልሽ ጣና ወየው አባያታ ወየውልህ ጫሞ
ፊት ሰው ሞቶለታል ባህር ይሙት ደግሞ
ብለው ዶለቱ አሉ ብለው መከሩ አሉ
እንግዲህ ዘራፍ በል የባህር ልጅ ሁሉ
ቀረርቶን ተላመድ ሰይፎችህ ይሳሉ
በአለማያ ይብቃ ከሰው መዋዋሉ
ወየው አለማያ የሃረር ሲሳይ
ባህርም የሰውን ሞት ይሞታል ወይ
የሱን ሞት ማን ቻለው የቱ ጎበዝ ከቶ
300 ሽ ነፍሳት ከሞት አፍ አውጥቶ ደሙን አጠጥቶ
የሱን ህይዎቱን ሰውቶ
አወይ ዓለማያ አቤት ያንተስ ነገር
አሉላ ቢሰማ ዮሃንስ ቢሰማ ቴዎድሮስ ቢሰማ
ምን ይውጠው ነበር ምን ይውጠን ነበር
ያ ለባህር ሟቹ ለውሃ ሰሳቹ
ባህር አሥራት ሲሆን ለሚያየው ልጆቹ
ምን ይሰመው ነበር የፈረሱ ጌታ ለደም ተሟጋቹ
መጥኔ ለሁላችን የአገር ልማድ ሻሪ የአባት ወግን ሻሪ
ስንት ባህር ገሎ ስንት ወንዝ አጉድሎ ሽህ ዓመት አክባሪ
የየዋህነቱን የታዳጊነቱን የአፍቃሪነቱን ልክ መቁጠር ቢታክትም
ርግማን ሆኖብን ባበሻ ምድር ላይ ደግ አይበረክትም።
Source: Anonymous
Transcribed from audio file (ወርቁ ለገሠ)
(10/27/10)
