አቡጊዳ – እነ ሃብታሙ ፍርድ ቤት አልቀረቡም – አብርሃ ደስታ የት እንዳለ አይታወቅም

አቡጊዳ – እነ ሃብታሙ ፍርድ ቤት አልቀረቡም – አብርሃ ደስታ የት እንዳለ አይታወቅም

« ከትላንት በስቲያ የተያዙት የተቃዋሚ ፓርቲ አመራሮች በዛሬው እለት አራዳ ፍርድ ቤት ሊቀርቡ እንደሚችሉ የፍኖተ ነፃነት የፖሊስ ምንጮች የፍኖተ ነፃነት የፖሊስ ምንጮች እንደጠቆሙት የአንድነት ለዴሞክራሲና ለፍትህ ፓርቲ የህዝብ ግንኙነት ኃላፊ ወጣት ሀብታሙ አያሌው፣ የፓርቲው የድርጅት ጉዳይ ም/ኃላፊ የሆነው አቶ ዳንኤል ሺበሺ እንዲሁም የሰማያዊ ፓርቲ ብሔራዊ ምክር ቤት ም/ሰባሳቢ አቶ የሺዋስ አሰፋ ዛሬ ከሰዓት በኋላ አራዳ ፍርድ ቤት ለጊዜ ቀጠሮ እንደሚቀርቡ ይጠበቃል፡፡ የተቃዋሚ ፓርቲ አመራሮቹ ጠበቆቻቸውን ጨምሮ ማንም ሰው እንዳይጎበኛቸው ክልከላ መደረጉ የሚታወቅ ሲሆን መንግስት ፖለቲከኞቹን ያሰረበትን ምክንያት እስካሁን ይፋ አላደረገም፡» ሲል የኖት ነጻነት ጋዜጣ ዘግቦ ነበር።

በርካታ የአንድነት ፣ ሰማይዊ አመራር አባላት፣ የእስረኞቹ ጠበቃዎች፣ ቤተሰብና ወዳጆች፣ እስረኞቹን ለማየትን እና ደህንነታቸው ለመከታተል በፍርድ ቤት ተገኝተው ለሰዓታት ቢጠብቁም ፣ ኢሕአዴግ እስረኞቹ ወደ ፍርድ ቤት ሳይቀርቡ ቀርተዋል።

በዚህ ጉዳይ ላይ አስተያየት የሰጡት፣ በቅርቡ የአንድነት ፓርቲን የተቀላቀሉት፣ ደራሲና የፖለቲካ አክቲቪስት አቶ አስራት አብርሃም «ህገ መንግስቱ ላይ 48 ሰአት በምን አቆጣጠር ነው? ወታደራዊ የሚስጥር ኮድ ነው እንዴ ? የትግል ጉዋዶችን ዛሬ ፍርድ ቤት ያቀርቡቸው ይሆናል ብለን ቀኑን ሙሉ በብርድና በዝናብ እየተደበደብን ብንውልም ሊያቀርቧቸው አልቻሉም አሁንስ ማስመሰሉም ተውት መሰለኝ» ሲሉ የዛሬዉን ዉሉ በሃዘኔት ገልጸዋል።

የአንድነት ምክር በት አባል እንዲሁም ብቸኛ የፓርላም አባል አቶ ግርማ ሰይፉ በበኩላቸው « መረጃ መደበቅ የአፈና አገዛዝ አንዱ መገለጫ ነው፡፡ በስምንት ሰዓት ጀምሮ ፍርድ ቤት ይቀርባሉ ተብለው ሲጠበቁ የነበሩት እነ ሀብታሙ ሳይቀርቡ ቀርተዋል፡፡ ብዙ ሰው ስራ ፈቶ ውሎዋል፡፡ ይህ ለልማታችን አጋዥ ነው ብለን ልንወስደው እንችላለን፡፡ መረጃ በትከክል ስለማይገኝ እንዲሁም በትክክል የምናስተላልፍበት ስናጣ የምንጠቀምባቸው አማራጮች ለክስ እንደሚያበቁንም አውቀናል፡፡ ለማንኛውም ለመታሰር የተዘጋጀን ማሰር ብዙ የሚያመጣው ፋይዳ አይታየኝም፡፡ አሁንም አሰሮ ከመጨነቅ ነፃነትን መፍቀድ የተሻለ ሳይሆን አይቀርም፡፡ በ48 ሰዓት ፍርድ ቤት መቅረብ ያለባቸው ሰዎች ሳይቀርቡ ቢቀር ህገ መንግሰትን ያለማክበር መሆኑን በዚህም መነሻ ማን ተጠያቂ እንደሚሆን አይታወቅም፡፡ ዳኞች ስልጠና ላይ ስለሆኑ ነው የሚል መልስ ልናገኝ እንችላለን፡፡ ህገ መንግሰቱ ግን ይህን እንደ ምክንያት አይቀበልም፡፡ ለማኝኛውም ትዕግሰቱን እንዲሰጠን መለመን ነው፡፡ ፈጣሪን፡፡ የተሳሪ ቤተሰቦች እንዲበረቱ ማበረታት ይኖርብናል እባካችሁ ከጎናቸው መሆናቸንን እናሰመስክር፡፡ የነፃነት ጉዞ ረጅም ቢሆንም መድረሳችን ግን አይቀርም፡፡» ሲሉ እስረኞቹ ለፍርድ አቅርቦ ፍርድ ቤት አለማቅረብ ጸረ-ሕገ መንግስታዊ መሆኑን ለማሳየት ሞከረአል።

ከአረና አካባቢ በደረሰን ዜና መሰረት ወጣት ፖለቲከኛዉን ብሎገሩ አብርሃ ደስታ እንኳን ፍርድ ቤት ሊቀርብ እስከአሁን የት እንዳለ እንኳን ማወቅ የተቻለበት ሁኔታ የሌለ ሲሆን፣ በአካሉ ላይ ከፍተኛ ጉዳት ሊደርስነት እንደሚችል ግምት እንዳላቸው ይናገራሉ።