ቅድስት ቤተ ክርስቲያን የቅዱሳን አሠያየም ቀኖና ከአፈጻጸም መመሪያው ጋራ ልትደነግግ ነው

  • የመንበረ ፕትርክናው ነጻነት በተገኘበትና ብሔራዊ ቅዱስ ሲኖዶስ በተቋቋመበት ባለፈው ግማሽ ምእት በተነሡ ቅዱሳን ጥናትና አሠያየም ላይ ትኩረት ይሰጣል፡፡
  • ቀኖናው ተደጋጋሚ ራእይና ተኣምራት በማሳየት የተመሠረተውን የቤተ ክርስቲያናችንን የቅዱሳን አሠያየም ትውፊት ሲኖዶሳዊ በማድረግ የሚያጠናክር ነው ተብሏል፡፡
  • የኮፕት ኦርቶዶክስ ቤተ ክርስቲያን ብፁዕ ወቅዱስ ፖፕ አቡነ ቄርሎስ ስድሰተኛንና ሊቀ ዲያቆን ሐቢብ ጊዮርጊስን በቅድስና ለመሠየም በምታደርገው ዝግጅት ቅድስናቸውን ዐውቃላቸዋለች፡፡
  • ኹለተኛው ፓትርያርክ ብፁዕ ወቅዱስ አቡነ ቴዎፍሎስ ሐምሌ ፬ ቀን ፲፱፻፹፬ ዓ.ም. ‹‹ቴዎፍሎስ ቅዱስ ሰማዕት››፤ ብፁዕ አቡነ ጴጥሮስ ሊቀ ጳጳስ በ፲፱፻፺፯ ዓ.ም. ‹‹ሰማዕተ ጽድቅ›› ተብለው እንዲጠሩ ከቅዱስ ሲኖዶስ ዐዋጅ ወጥቷል፡፡
  • ወላዲተ አእላፍ ቅዱሳን – ቅድስት ኢትዮጵያ፡- በሰማይ በዐጸደ ነፍስ ተጋድሏቸውን ፈጽመው የጽድቅና የድል አክሊል ተቀዳጅተው የሚኖሩ ማኅበረ ቅዱሳን ብቻ ሳይኾን በምድር በሕይወተ ሥጋ ከከሐድያን፣ ከመናፍቃን፣ ከፍትወታት እኩያትና ከኃጣውእ የሚጋደሉ የቃል ኪዳን ቅዱሳን አገርም ናት!

(አዲስ ጉዳይ፤ ቅጽ ፰ ቁጥር ፪፻፳፩፤ ሰኔ ፳፻፮ ዓ.ም.)

patriarchate officeየኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን ቅዱስ ሲኖዶስ የቅድስና አሠያየምን የተመለከተ ቀኖና (ደንብ) እንደሚያወጣ ተገለጸ፡፡ በርክበ ካህናት ቅዱስ ሲኖዶስ ምልዓተ ጉባኤ መደበኛ ስብሰባ ላይ ለውይይት የቀረበው የ፲፱፻፺፩ ዓ.ም. ሕገ ቤተ ክርስቲያን ማሻሻያ ረቂቅ እንዳመለከተው፣ በመንፈስ ቅዱስ የሚመራው ቅዱስ ሲኖዶሱ ስለ ቅድስና አሠያየም ጉዳይ ዝርዝር ደንብና መመሪያ ያወጣል፤ በቤተ ክርስቲያኒቱ ስለሚሠየሙ ቅዱሳን ውሳኔ የመስጠት ተግባርና ሓላፊነትም የመንበረ ሐዋርያት ወራሽ በኾነው በቅዱስ ሲኖዶሱ ሥልጣን እንደሚፈጸም በማሻሻያ ረቂቁ ላይ ተመልክቷል፡፡

አዲስ ጉዳይ ያነጋገራቸው አንድ የቅዱስ ሲኖዶሱ አባል፣ የቅድስና አሠያየም ቀኖናው(ደንብ) እና የአፈጻጸም መምሪያውን የማዘጋጀት አስፈላጊነት አስመልክተው ሲያስረዱ፡- ‹‹እስከ አኹን ተወስነን ያለነው ቤተ ክርስቲያናችን በግብጽ ኮፕት ኦርቶዶክስ ቤተ ክርስቲያን ቅዱስ ሲኖዶስ ሥር በነበረችባቸው ዓመታት ከውጭ ወደ ኢትዮጵያ መጥተው በተቀበልናቸውና ከኻያው መቶ ክፍለ ዘመን በፊት በነባር ትውፊታችን ባወቅናቸው ብሔራውያን ቅዱሳን ነው፤ በመንበረ ፕትርክና መንፈሳዊ ነጻነት ከተቀዳጀንና ብሔራዊ ሲኖዶስ ከተቋቋመ ከኃምሳ ዓመት በላይ ስለተቆጠረ ከዚያ ወዲኽ የተነሡ ቅዱሳን ታውቀውና ተጠንተው ልናውቃቸው/ዕውቅና ሊሰጣቸው ይገባል፤›› ብለዋል፡፡

የቅድስና አሠያየም ቀኖናውና የአፈጻጸም መምሪያው ከመሠረቱ ሲታሰብ፣ ከቤተ ክርስቲያናችን ጋራ የትምህርተ ሃይማኖት አንድነት ያላቸው አኃት አብያተ ክርስቲያናትና የሌሎች ጥንታውያን አብያተ ክርስቲያናት ቀኖናትና ተሞክሮ በዝርዝር መታየቱንና ለተግባራዊ ዝግጅቱም ከፍተኛ እገዛ እንደሚኖረው የቅዱስ ሲኖዶሱ አባል ጠቅሰዋል፡፡ በቅዱሱ ሥያሜ ላይ የመጨረሻ ውሳኔ የመስጠቱ ሥልጣን የቅዱስ ሲኖዶሱ ቢኾንም፣ የአሠያየሙ መነሻ ከምእመናኑ በሚቀርብበትና ‹‹ይሾም ይገባዋል፤ የለም ይቆይ›› በሚለው ጉዳይ የምእመናነ ክርስቶስ ተሳትፎ ስለሚኖርበት አግባብ ደንቡ የሚያካትታቸው ድንጋጌዎች እንደሚኖሩም የቅ/ሲኖዶስ አባሉ ለአዲስ ጉዳይ ተናግረዋል፡፡

Ethiopian Monk reading Manuscripts

ስንክሳር ከገድል ይለያል፡፡ ዲያቆን ያረጋል አበጋዝ ‹‹ፍኖተ ቅዱሳን›› በሚል ርእስ ፲፱፻፺፫ ዓ.ም. ባሳተሙት መጽሐፍ የስንክሳርንና የገድልን ልዩነት ያስረዳሉ፡፡ ገድል÷ ትግል፣ ፈተና፣ ውጊያ፣ ሰልፍ፣ ድልና አክሊል እስኪገኝ ድረስ የሚደክሙት ድካም፣ የሚሠሩት ሥራ፣ የሚቀበሉት መከራ ነው፡፡ ስለኾነም ገድል(በላቲኑ አክታ በግሪኩ ሃግዮስ)፡- የአንዱን ጻድቅ ወይም ሰማዕት ታሪክና የተቀበለውን ጸዋትወ መከራ በዝርዝር፣ ከጌታ የተቀበለውን ጸጋና ቃል ኪዳን፣ በምድር ወይም በዐጸደ ነፍስ የፈጸማቸውን ተኣምራት፣ ስለክብሩ የተደረሰለትን መልክእ የሚይዝ ነው፡፡ ስንክሳር(Synaxarium) ማለት ስብስብ(እስትግቡእ) ማለት ነው፡፡ ስብስብ የተባለበትም ምክንያት የብዙ ቅዱሳንን ገድልና ዜና ሕይወት በአንድ ላይ የያዘ መጽሐፍ ስለኾነ ነው፡፡ ስንክሳር በእያንዳንዱ ቀን የሚዘከረውን ቅዱስ ታሪክ ጠቅለል ባለ መልኩ የያዘ ነው፡፡ ከታሪኩም መጨረሻ ታሪኩን ጠቅለል አድርጎ የሚያስረዳ በግጥም መልክ የተዘጋጀ ድርሰት አለ፡፡ ይኸውም አርኬ ይባላል፡፡ ስንክሳር ደግሞ የኹሉንም ቅዱሳን ሥራ ጠቅለል ባለ መልኩ በዕለት የያዘ ነው፡፡ ስንክሳር ቅዱሳኑን የሚያነሣው ያ ዕለት የተወለዱበት፣ ያረፉበት፣ ቃል ኪዳን የተቀበሉበት ወይም በዚያ ዕለት እንዲዘከሩ የሚያደርጋቸው ሥራ የሠሩበት ዕለት ከኾነ ነው፡፡ ስለኾነም በአንድ ቀን ብዙ ቅዱሳን ይዘከራሉ፤ እንዲኹም ስንክሳር አንዱን ቅዱስ በተለያዩ ቀናት ሊያዘክረው ይችላል፡፡ ዲያቆን ኤፍሬም እሸቴ ‹‹የገድላት አዝማናዊ አከፋፈል›› በሚል ርእስ በ፲፱፻፺፪ ዓ.ም. ባቀረቡት ጥናት÷ የቤተ ክርስቲያናችን ገድላት ክርስትና መንግሥታዊ ሃይማኖት ኾኖ ከታወጀበት ከአራተኛው መ/ክ/ዘ ጀምሮ የመጨረሻዎቹ ገድሎች ተጽፈውባቸዋል እስከሚባልበት እስከ ፲፰ኛው መ/ክ/ዘ ድረስ ያሉትን ዓመታት ድረስ የተጻፉትን ያጠቃልላሉ፤ በይዘቶቻቸውም ገድላቱ በሚያተኩሩባቸው የታሪክ ክሥተቶች፣ የታሪክ ለውጦች እና የአጻጻፍ ዘዴዎቻቸው በአራት አዝማናት ተከፍለው ሊጠኑ ይችላሉ – የዘመነ አኵስም፣ የዘመነ ዛጔዌ፣ የዘመነ ዘርዓ ያዕቆብ(ወርቃማው የግእዝ ሥነ ጽሑፍ ዘመን) እና ሀገራችን በጦርነት የታመሰችበት ፲፮ኛው መ/ክ/ዘ፡፡ አጥኚው በርካታ አብነቶችን በመጥቀስ እንዳመለከቱት፣ በኢትዮጵያ የቅዱሳን አሠያየም በመጨረሻ የተነሡና ገድላት የተጻፉላቸው ኢትዮጵያውያን ቅዱሳን የኤርትራው ዘርዓ ቡሩክ እና ጻድቁ ዮሐንስ ሲኾኑ ከእነርሱ በኋላ የተነሣ ገድል የተጻፈለት ቅዱስ አልተገኘም፤ ምናልባት ገድለ ቅዱሳን መጻፉ ሞቶ የተቀበረው በዚህ ዘመን ሳይኾን አይቀርም፡፡ የቅዱሳንን ዜናቸውንና ሥራቸውን በየዕለቱ መስማት እነርሱን ወደ መምሰል የሚያነሣሣ፣ ረድኤታቸውን የሚያስገኝ በበረከታቸውም የሚያስጎበኝ ነውና ቤተ ክርስቲያን ሳይሳለሙ፣ ዜና ቅዱሳን ሳይሰሙ መዋል እንደማይገባ አበው ተናግረዋል፡፡

ራሱን ችሎ በሚወጣው የአሠያየም ቀኖናና ዝርዝር የአፈጻጸም መመሪያው መሠረት ተለይተውና ተጠንተው የቅዱስ ሲኖዶሱን ዕውቅና ያገኙ ቅዱሳን÷ ዜና ሕይወታቸው፣ ብሂላቸው፣ ምክራቸውና ትሩፋታቸው እንዲጻፍ ይደረጋል፤ ይህም ለቅዱሳኑ መታሰቢያነት ብቻ ሳይኾን በቤተ ክርስቲያናችን የነገረ ቅዱሳን አስተምህሮ መሠረት፣ ትውልዱ ፈለጋቸውን እንዲከተል እንዲመስላቸውም መንገዳቸውን የሚያውቅበትና የሚማርበት፣ በረከትም የሚያገኝበት ኾኖ እንደሚያገለግል ብፁዕ ሊቀ ጳጳሱ ገልጸዋል፤ የቅዱሳኑ ታሪክ የሚመዘገበው የብዙ ቅዱሳንን ዜና ሕይወት በአንድነት እንደያዘው የስንክሳር ዓይነት አጻጻፍ እንደሚኾንና ይኸውም ከገድላት አጻጻፍ እንደሚለይ ብፁዕነታቸው አስረድተዋል፡፡

የነገረ ቤተ ክርስቲያን ተመራማሪና ጸሐፊ ዲያቆን ዳንኤል ክብረት፣ የቤተ ክርስቲያኒቱ መዓዛ ስለኾኑት ቅዱሳን አሠያየም ቀኖና ማውጣትና በመሳሰሉት ጉዳዮች ላይ ቅዱስ ሲኖዶሱ መነጋገሩ አጀንዳዎቹን ታላቅ ያደርጋቸዋል ይላሉ፡፡ የቅዱሳን አሠያየም፡- በሲኖዶሳዊ (formal/official canonization) እና በሕዝብ ዕውቅናና አጽድቆት(popular acclaim) እንደሚፈጸም የሚያስረዱት ጸሐፊው፣ በኢትዮጵያ ቤተ ክርስቲያን ትውፊት እስከ ሕይወታቸው ፍጻሜ በገድል ተቀጥቅጠው ላረፉና ከዕረፍታቸውም በኋላ ምትሐት ያይደለ እውነተኛና ተደጋጋሚ ተኣምራትን በማድረግ ለሚታወቁ ቅዱሳን ዕውቅናና አጽድቆት ሲሰጥ የቆየው ሕዝበ ክርስቲያኑ እንደነበር አውስተዋል፤ የቀኖና ዝግጅቱ ምእመኑ ትውፊቱን እንዲያስታውስና ለዘመናት የተወበትን ምክንያት እንዲመረመር የሚያደርግ በመኾኑ የሌሎች አብያተ ክርስቲያናትን አሠራር ብቻ ሳይኾን የምእመኑ የቀድሞ ትውፊትም በአግባቡ ተጠንቶ መያዝ እንዳለበት ይመክራሉ፡፡

‹‹አራቱ ኃያላን›› በሚለውና የመካከለኛው መቶ ክፍለ ዘመን ቅዱሳንን ታሪክ በጥልቀት ባስነበቡት መጽሐፋቸው፣ በቤተ ክርስቲያኒቱ ኹለት ዓይነት ዕውቅና እንዳለ የሚያብራሩት ተመራማሪው፣ አንድ ሰው ለቤተ ክርስቲያን ላበረከተው በጎ ነገር የሚሰጠው የአስተዋፅኦ ዕውቅና እና ለቅድስና ኑሮ የሚሰጠው ዕውቅና እንዳለ ጠቅሰዋል፡፡ የአስተዋፅኦ ዕውቅና በታላላቅ አድባራት ላይ በነገሥታት በሚሾሙት የሚሰጥ ሲኾን በመጻሕፍት ኅዳጎችና በሥዕሎች ግርጌ አስተዋፅኦዋቸውን በማሣልና በመጻፍ የሚገለጽ ነው፡፡ ዋነኛው የማዕርገ ቅድስና ዕውቅና ግን የቅዱሱ ዕረፍት/ኅልፈት ቢያንስ ኃምሳ ዓመት ከሞላው በኋላ በሚገለጥ ራእይ፣ በሚደረጉ ተኣምራትና መንክራት የሚሰጥ ሲኾን የሚወሰነውም የመላእክትን አኗኗር በሚመስሉ፣ ከዊነ ምንኵስናን ሥርዓተ ገዳምን ባጸኑ ገዳማውያን አባቶች ነው፡፡

The Four Saints of Zagwe Dynast

ቅዱስ ይምርሐነ ክርስቶስ፣ ቅዱስ ሐርቤ(ገብረ ማርያም)፣ ቅዱስ ላሊበላ፣ ቅዱስ ነአኵቶ ለአብ – እነዚህ ቅዱሳን የነበሩበት ዘመን ከ፲፩ኛው – ፲፪ኛው መ/ክ/ዘ ሲኾን ምስፍናን ከክህነት፣ ክህነትን ከምስፍና ጋራ አስተባብረው በመያዝ ለክርስትና መስፋፋት፣ ለቤተ ክርስቲያን ዕድገት፣ ለአገር አንድነት የከፈሉት መሥዋዕትነት፣ ያቆዩት መንፈሳዊ ቅርስ፣ በዐይን የማታይ፣ በእጅ የሚዳሰስ ከመኾኑም በላይ ለሀገር ኢኮኖሚ የደም ሥርና የጀርባ አጥንት ኾነው የሚታዩት ውቅር አብያተ ክርስቲያናት ሕያው ምስክሮች ናቸው፡፡ በመኾኑም እናት ቤተ ክርስቲያን ለአራቱ መንፈሳውያን ነገሥታት፡- የቅድስና ማዕርግ ሰጥታ፣ ገድላቸውን ጽፋ ለትውልደ ትውልድ አቀቆይታለች፡፡ (የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን ታሪክ ከልደተ ክርስቶስ እስከ ፳፻ ዓ.ም.)

የቤተ ክርስቲያኒቱ የቅድስና ቀኖና በሥርዓተ ምንኩስና ወይም በሥርዓተ ጋብቻ መጽናትን እንደ ዋነኛ መስፈርት ይቆጥራል የሚሉት ዲ/ን ዳንኤል፣ ለቤተ ክርስቲያን ብዙ ከደከሙት ነገሥታት እንደ ዐፄ ዘርዐ ያዕቆብ ያሉት በአንድ ሚስት ባለመጽናታቸው ከመታሰቢያ ያላለፈ የአስተዋፅኦ ዕውቅና እንዳትሰጥ ሲያደርጋት፣ በ፫፻፴፫ ዓመታት ውስጥ ከተነሡት የዛጔዌ ነገሥታት ውስጥ በአንዲት ሚስት በመጽናት ክህነትን ከንግሥና ያስተባበሩትን ካህናት ወነገሥታት ሐርቤ፣ ይምርሐነ ክርስቶስ፣ ነአኵቶ ለአብና ላሊበላን በቅድስና መሠየሟን አስረድተዋል፡፡

St-Takla-org_Coptic-Pope-Kyrillos-Cyril-VI-031

ጸሎተኛና ገባሬ ተኣምር ብፁዕ ወቅዱስ ፓትርያርክ አቡነ ቄርሎስ ፮ኛ (እ.አ.አ ከ፲፱፻፶፱ – ፲፱፻፸፩)

ገዳማዊና ብሕትውናዊ ሕይወትን ለዓለም እንዳበረከተች የምትታመነው የግብፅ ኦርቶዶክስ ቤተ ክርስቲያን በቅዱሳን አሠያየም ቀኖናዋ÷ የጥናትና ምርመራ (Investigation)፣ የዕውቅና(Recognition) እና የቀኖና (Canonization) ደረጃዎች እንዳሏት ዲ/ን ዳንኤል ይዘረዝራሉ፡፡ እንደ ዲያቆን ዳንኤል ገለጻ፣ የቤተ ክርስቲያኒቱ የሥያሜ ቅዱሳን ሒደት አኹንም ያላቋረጠ ሲኾን÷ እ.አ.አ ከ፲፱፻፶፱ – ፲፱፻፸፩ የመንበረ ማርቆስ ፻፲፮ኛ ፖፕ የነበሩት ጸሎተኛና ገባሬ ተኣምር ብፁዕ ወቅዱስ ፓትርያርክ አቡነ ቄርሎስን ፮ኛ እና በ፲፱ኛው መ/ክ/ዘ መጨረሻና በ፳ኛው መ/ክ/ዘ መጀመሪያ ካህናትና ምእመናን በትምህርተ ሃይማኖታቸውና በመንፈሳዊ ሕይወታቸው ተጠናክረው ቤተ ክርስቲያኒቱን ከጥፋት እንዲታደጉ ያደረገውን ሊቀ ዲያቆን ሐቢብ ጊዮርጊስን(፲፰፻፸፮ – ፲፱፻፶፩) ባለፈው ዓመት ሰኔ ወር ለተጋድሏቸው የዕውቅና(Recognition) የቅድስና ደረጃ በቅዱስ ሲኖዶሱ እንደተሰጣቸው አውስተዋል፡፡

 

 

ኢትዮጵያ ባፈራቻቸው ቅዱሳንና በመሠረተቻቸው ገዳማት ብዛት ከግብፃውያን የማያንስ ታሪክ እንዳላትwww-St-Takla-org--St-Takla-Haymanot-The-Ethopian-03-05 የሚያምኑት ዲ/ን ዳንኤል÷ በግብፅ ቤተ ክርስቲያን ዘንድ በተጋድሏቸው የሚከበሩ እንደ ሙሴ ፀሊም፣ በሲኖዶሳቸውም ሳይቀር ቅድስናቸው የታወቀላቸው፣ ሕንፃ ቤተ ክርስቲያን የታነፀላቸው እንደ ጻድቁ አቡነ ተክለ ሃይማኖት የመሳሰሉ ቅዱሳን መኖራቸውን ጠቅሰዋል፡፡ የግብፅ ሲኖዶስ ለጻድቁ አቡነ ተክለ ሃይማኖት ቅድስና ዕውቅና የሰጠው ከዕረፍታቸው ኹለት መቶ ዓመታት በኋላ መኾኑን የሚጠቅሱት ተመራማሪው፣ መሠረቱ ግን ጻድቁን በተጋድሏቸው የሚያውቃቸው ሕዝብና በእግራቸው ተተክተው ገዳማዊ ሕይወትንና ስብከተ ወንጌልን ያስፋፉት አርድእቶቻቸውን እንደነበሩና ይህም በየወሩ በ24 ለሚታሰበው በዓለ ዕረፍታቸውና በየዓመቱ ግንቦት 12 ለሚከበረው ፍልሰተ ዓፅማቸው መነሻ እንደኾነም ገልጸዋል፡፡

የአሠያየም ድንጋጌው የሕዝበ ክርስቲያኑን መነሻና ሒደታዊ ተሳትፎ ታሳቢ ማድረጉ የሚገባ ነው የሚሉት የነገረ ቤተ ክርስቲያን ጸሐፊና ተመራማሪው÷ ‹‹ቅዱሱን በቅድሚያ ማክበር የሚጀምረው ሕይወቱን በተጋድሎ ባሳለፈበት፣ በስሙ ጠበል በፈለቀበት፣ ተደጋጋሚ ተኣምራት በሚፈጸሙበት፣ አንድ ዓይነት ራእይ ለተለያዩ ሰዎች በሚታይበት ሥፍራ የሚኖረው የአካባቢው ሰው ነው፤ ሕዝቡም የቅዱሱን ገድል ይጽፋል፤ ዝናውን የሰሙ ምእመናን ወደ አካባቢው ይጓዛሉ፤ ዜና ሕይወቱና ገድሉ የሰፈረበትን መዝገብ እየገለበጡ ወደየአካባቢያቸው በመውሰድ ስሙን እያዘከሩበትና እየጸለዩበት በቃል ኪዳኑ ይማፀናሉ፤ የቅዱሱ ስምና ሥራም በዚኽ መልኩ እየተወረሰና እየተስፋፋ ይቀጥላል፤›› በማለት ልምዱ ለሚዘጋጀው ቀኖናና ዝርዝር የአፈጻጸም መምሪያ መነሻ መደረግ እንዳለበት ሐሳባቸውን ያካፍላሉ፡፡

 

 

 

 

ቤተ ክርስቲያን በቅድስና የምታውቃቸውና የምታሳውቃቸው

ቤተ ክርስቲያን ለዕሥራ ምእት(ሚሌኒየም) በዓል አከባበር ባሳተመችው ‹‹የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን ታሪክ ከልደተ ክርስቶስ እስከ ፳፻ ዓ.ም.›› መጽሐፍ ‹‹የኢትዮጵያ ቤተ ክርስቲያን ቅዱሳን›› የምንላቸው÷ (1)ብሔራውያን ቅዱሳንን፣ (2)ከውጭ ወደ ኢትዮጵያ መጥተው በፈጸሙት ሐዋርያዊ አገልግሎታቸውን ፈጽመው ዘላለማዊ ዕረፍታቸውን በኢትዮጵያ ምድር በማድረጋቸው ቅድስና ሰጥታ፣ በየስማቸው ቤተ ክርስቲያን አንፃ፣ ጽላት ቀርፃ፣ ገዳም ገድማ ያከበረቻቸውንና ያስከበረቻቸውን ቅዱሳን ያጠቃልላል፡፡

የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን መሠረታዊ አለኝታ የኾኑትን ከፍተኛ የጥምህርት ተቋማትና ዐበይት መምህራንን፣ በቤተ ክርስቲያናችን ስም በየአረፍተ ዘመናቱ መላ ሕይወታቸውን የሰው ዘር የኾነውን ኹሉ በሥራና በጸሎት በማገልገል፣ እግዚአብሔርን በማመስገን ሕይወታቸውን መሥዋዕት አድርገው ያቀረቡትንና እጅግ በጣም ከፍተኛ ገድል የፈጸሙትን ኹሉ ቤተ ክርስቲያኛችን የጾታ ልዩነት ሳታደርግ በገድላቸው ጽናትና በትሩፋታቸው ብዛት ‹‹ብፁዕ እና ብፅዕት፣ ቅዱስና ቅድስት›› ሊያሰኝ ከሚችል የብፅዕናና የቅድስና ማዕርግ የደረሱ መኾናቸውን በማረጋገጥ፡- በስማቸው ቤተ ክርስቲያን እንዲታነፅ፣ ገዳም እንዲገደም፣ ደብር እንዲደበር፣ ገድልና ድርሳን እንዲጻፍላቸው፣ ወርኃዊና ዓመታዊ በዓላቸው እንዲታሰብና እንዲዘከር በማድረግ በቅድስና ታውቃቸዋለች፤ ታሳውቃቸዋለች፡፡

ማኅበረ ቅዱሳን ለከፍተኛ ትምህርት ተቋማት ግቢ ጉባኤያት ማስተማርያ ባሳተመውና መልአከ ሰላም ቀሲስ ደጀኔ ሺፈራው ባዘጋጁት ‹‹ነገረ ቅዱሳን – ፩›› መጽሐፍ የቅዱሳን ሰዎች አሠያየም (Canonization of Saints) አስመልክተው፣ ‹‹በኦርቶዶክሳዊት ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን የቅዱሳን አሠያየም በድምፅ ብልጫ አይደለም፤›› ይላሉ፡፡ ቅዱሳንን ቅዱስ የሚያሰኛቸው ሕይወታቸው ነው፡፡ በውስጥም በአፍኣም በቅድስና ወርቅ የተለበጡ በመኾናቸው እንደ ካህኑ ዘካርያስና እንደ ቅድስት ኤልሳቤጥ ‹‹በጌታ ትእዛዛትና ሕግጋት ኹሉ ያለነቀፋ እየሔዱ በእግዚአብሔር ፊት ጻድቃን ነበሩ፡፡›› ተብሎ ይመሰከርላቸዋል፡፡ (ሉቃ.፩÷፮) ከኹሉ በላይ የሚሰክርላቸው ደግሞ እግዚአብሔር ነው፡፡ (ኤር.፩÷፬-፭፤ ማቴ.፲፩÷፲፩፤ ፪ኛነገ. ፬÷፱፤ መጽ.ሶስና ፩÷፵፬፤ ዘኊ.፲፪÷፩-፰)

Saint Aba Samuel ZeWaldiba

ጻድቅ አባ ሳሙኤል ዘገዳመ ዋሊ፣ መነኰስ ፍጹም፣ ምዑዝ ምንኵስናኹ፣ ንጹሕ ድንግልናኹ፣ አካለ አንበሳ ግሩመ ይሜጥን በእዴኹ

በመኾኑም ኦርቶዶክሳዊት ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን ቅዱሳንን የምትሠይባቸውን መሠረቶች መልአከ ሰላም ቀሲስ ደጀኔ ሺፈራው እንደሚከተለው ይዘረዝራሉ፡-

  1. ‹‹እስከ ሞት ድረስ የታመንክ ኹን፤››(ራእይ ፪÷፲) እንደተባለ እስከ ሕይወታቸው ፍጻሜ ድረስ በጾም በጸሎት ተወስነው፣ በገድል ተቀጥቅጠው በአምልኮተ እግዚአብሔር የጸኑትን፤
  2. በጌታችን በአምላካችንና በመድኃኒታችን በኢየሱስ ክርስቶስ ደም ላይ የተመሠረተችውን ቤተ ክርስቲያን እምነትና ሥርዓት ጠብቀው በማስጠበቅ በአገልግሎት የተጉትንና የተጋደሉትን፤፤
  3. የእግዚአብሔርን ቃል ንባብ ትርጓሜና ምሥጢር ሳያፋልሱ በማስተማር በሃይማኖት ያጸኑትን፣ ምእመናንንም ያበዙትን፤፤
  4. በሕይወታቸው ነውር በሃይማኖታቸው ነቀፌታ ያልተገኘባቸውን፤፤
  5. ከዓለም ተለይተው፣ በርሓ ወድቀው፣ ደንጊያ ተንተርሰው፣ ጤዛ ልሰው፣ ዋሻ ዘግተው፣ ጸብኣ አጋንንትን ድምፀ አራዊትንና ግርማ ሌሊትን ሳይሠቀቁ የኖሩትን፣ ስለ ሃይማኖታቸው በመመስከር በሰማዕትነት ያረፉትን፤፤
  6. ምትሐት ያይደለ እውነተኛ ተኣምራት በማድረግ የሚታወቁትን፤
  7. በአጠቃላይ ከፍጹምነት ማዕርግ የደረሱትን ቅዱሳን እግዚአብሔር እንዳከበራቸው ታከብራቸዋለች፤ ቅዱሳን ብላ በቅድስና ስም ትጠራቸዋለች፡፡

ከእነርሱ አስቀድሞ የቅድስና ማዕርግ በተሰጣቸው ሰዎች መዝገብ ስማቸውን በክብር ትጽፋለች፤ ሕዝቡም እንዲያውቀው ታደርጋለች፡፡ ዐፅማቸው ያለበት ቦታ የሚታወቅ እንደኾነ ሰብስባ በክብር ታስቀምጣለች፡፡ ተኣምራቸውን ወይም ገድላቸውን ትጽፍላቸዋለች፡፡ ለጸሎት፣ ለልመናና ለምስጋና የሚኾን መልክእ ትደርስላቸዋለች፡፡ የሚታሰቡበት ዕለት ትሰጣቸዋለች፡፡ የመታሰቢያ ሥዕል ትሥልላቸዋለች፡፡ ጽላት ትቀርፅላቸዋለች፤ ሕንፃ ቤተ ክርስቲያን ታንፃላቸዋለች፡፡ ስማቸውንም እየጠራች ትማፀንባቸዋለች፡፡ ምእመናንም በስመ ክርስትና ኃይለ ጊዮርጊስ፣ ወለተ ጊዮርጊስ፣ ገብረ ተክለ ሃይማኖት፣ ወለተ ተክለ ሃይማኖት. . . እየተባሉ እንዲጠሩ ታደርጋለች፡፡

ቅዱሳን እንደ ግብራቸውና ሥምሪታቸው ይለያሉ

ቅዱሳን ሰዎች ለተለያየ ተግባር ነገር ግን ለአንድ ዓላማ በእግዚአብሔር የተጠሩ ሰዎች ናቸው፡፡ መጠራት ብቻ ሳይኾን ከተጠሩት መካከል ተለይተው የተመረጡ ናቸው፡፡ ‹‹የተጠሩ ብዙዎች የተመረጡ ጥቂቶች ናቸውና፡፡›› (ማቴ.፳፪÷፲፬) የተባለው ለዚኽ ነው፡፡ ስለኾነም ‹‹እኔ እግዚአብሔር አምላካችኹ ቅዱስ ነኝና እናንተም ቅዱሳን ኹኑ›› (ዘሌ.፲፬÷፪) ብሎ በቀጥታ የተናገረ ቅድስና የባሕርይው የኾነ እግዚአብሔር ከብዙዎች መካከል ለይቶ የመረጣቸውን ቅዱሳንን መልሶ ከብዙኃኑ መቀላቀል አይገባም፡፡

ቅዱሳን በግእዝ ርትእት አንድ ቢኾኑም በግብራቸውና ስምሪታቸው የተለያዩ ናቸውና እግዚአብሔር የልጁን መልክ እንዲመስሉ ወስኖ የጠራቸው፣ የመረጣቸው፣ ያጸደቃቸውና ያከበራቸው ነቢያት፣ ሐዋርያት፣ ጻድቃን፣ ሰማዕታት፣ ነገሥታት፣ ካህናት፣ አበው፣ አርድእት፣ ጳጳሳት፣ ሊቃውንት፣ ደናግል፣ ምእመናን ቅዱሳን ናቸው፡፡

የቅዱሳን የፍጹምነትና የቅድስና ደረጃዎች

የእግዚአብሔር ወዳጆች የኾኑ ቅዱሳን በአንድ ጊዜ የፍጹምነትና የፍጹምነትና የቅድስና ደረጃ ላይ አይደርሱም፤ ነገር ግን የተወለደ ሕፃን ቀስ በቀስ በመዳኽ ወደ መቆም፣ ከመቆም ወደ መራመድ ከዚያም መሮጥና መዝለል እንደሚጀምር ኹሉ ቅዱሳንም ከወጣኒነት ጀምረው በጸጋ እግዚአብሔር እየተጎበኙ ወደ ፍጹምነት ይደርሳሉ፡፡ ‹‹ለጥቂት ጊዜ መከራን ከተቀበላችኹ በኋላ ራሱ ፍጹማን ያደርጋችኋል፤ ያጸናችኋል፤ ያበረታችኁማል፡፡›› እንዲል፡፡ (፩ኛጴጥ.፩÷፭ – ፲፩)፡፡
በወጣኒነት ጀምረው ፈተናውን እያሸነፉ ሲሔዱ በማዕከላዊነት ደረጃ አድርገው በመጨረሻ ከፍጹም ብቃት ላይ ይደርሳሉ፡፡ እነዚኽ ሦስቱ መንፈሳውያን ደረጃዎች፡- ወጣኒነት፣ ማዕከላዊነት እና ፍጹምነት ሲኾኑ ንጽሐ ሥጋ፣ ንጽሐ ነፍስ እና ንጽሐ ልቡና በመባልም ይታወቃሉ፡፡ በዚኽም መሠረት ቅዱሳን ደረጃ በደረጃ የሚደርሱባቸው መዓርጋት በዝርዝራቸው ዐሥር ናቸው፡፡ እነዚኽም ሦስቱ በንጽሐ ሥጋ፣ አራቱ በንጽሐ ነፍስ፣ ሦስቱ በንጽሐ ልቡና ይገኛሉ፡፡

በንጽሐ ሥጋ የሚገኙት ሦስቱ ማዕርጋት፡-

  1. ጽማዌ
  2. ልባዌ
  3. ጣዕመ ዝማሬ ናቸው፡፡

በንጽሐ ነፍስ የሚገኙት አራቱ ማዕርጋት፡-

  1. አንብዕ
  2. ኵነኔ
  3. ፍቅር
  4. ሑሰት ናቸው፡፡

በንጽሐ ልቡና የሚገኙት ሦስቱ ማዕርጋት፡-

  1. ንጻሬ መላእክት
  2. ተሠጥሞ ብርሃን
  3. ከዊነ እሳት ናቸው፡፡

እኒኽ ማዕርጋት የሚገኙትና የሚደረስባቸው በቅደም ተከተላቸው ነው፡፡ ከላይ ያለውን ማዕርግ የሚይዝ ታችኛውን ማዕርግ እንደያዘ በዚያው ላይ እየተጨመረለት ይሔዳል፡፡ (ዲ/ን ያረጋል አበጋዝ፣ ፍኖተ ቅዱሳን፣ ገጽ 197 – 198)፡፡ የፍጹማን መነኰሳት ሕይወት ይህን ይመስላል፡፡ የአባቶቻችን ማዕርግ እስከዚኽ ነው፤ የሰውን ልቡና ይመረምራሉ፤ ያለፈውንም የሚመጣውንም በእግዚአብሔር ኃይልና ቸርነት ያውቃሉ፡፡