የሰንበት ት/ቤቶች አንድነት ዓመታዊ ሀገር አቀፍ ጠቅላላ ጉባኤ ነገ ይጀመራል

  • ጠቅላላ ጉባኤው በየዓመቱ የሚካሔድበት በዓለ ጰራቅሊጦስ ‹‹የሰንበት ት/ቤቶች ቀን›› ነው
  • ሰንበት ት/ቤቶች ከአማሳኞች ጋራ የገቡበት ግጭትና አፈታቱ የጠቅላላ ጉባኤው ትኩረት ነው
  • ጥያቄያቸው በአግባቡና በወቅቱ ባለመፈታቱ ወጣቶች በየቦታው እየተንገላቱና እየታሰሩ ነው
  • ከ፳ ሚልዮን በላይ ወጣቶች በሰንበት ት/ቤቶች የታቀፉት ከ፬ ሚልዮን አይበልጡም
  • 60 ሺሕ ወጣቶች በ102 ማኅበራት የተደራጁበት የአ/አ ወጣቶች ማኅበራት ኅብረት ፈቃድ ታገደ

(ምንጭ፡- አፍሮ ታይምስ፤ ቅጽ ፩ ቁጥር ፳፤ ዓርብና ቅዳሜ፣ ግንቦት ፳፱ – ፴፣ ፳፻፮ ዓ.ም.)

sunday_schoolየኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን የሰንበት ት/ቤቶች ማደራጃ መምሪያ፣ ሦስተኛውን ሀገር አቀፍ የሰንበት ት/ቤቶች አንድነት ዓመታዊ ጠቅላላ ጉባኤ ከግንቦት ፴ – ሰኔ ፩ ቀን ፳፻፮ ዓ.ም. እንደሚያካሒድ ተገለጸ፡፡

በመንበረ ፓትርያርክ ጠቅላይ ቤተ ክህነት ደረጃ በየዓመቱ በበዓለ ጰራቅሊጦስ ሰንበት የሚካሔደው ጠቅላላ ጉባኤው በመላ ሀገሪቱ የሚገኙት ሰንበት ት/ቤቶች፡-

  • የአገልግሎት ሥርዓታቸውን በወጥነት ለመምራት የሚያስችል መሪ ዕቅድ እንዲያወጡበትና ትግበራውን በአህጉረ ስብከት የአፈጻጸም ሪፖርቶች እንዲከታተሉበት፣
  • በዚኽም በጋራ ችግሮቻቸው ዙሪያ የተሞክሮና ልምድ ልውውጥ በማድረግ እርስ በርሳቸው መልካም ግንኙነትን እንዲያዳብሩበትና እንዲማማሩበት፣
  • በአጠቃላይ ሰንበት ት/ቤቶችን ከላይ እስከ ታች በማደራጀት በማደራጃ መምሪያው ተደራሽ የኾነ ሀገር አቀፍ አገልግሎት እንዲኖር በማድረግ በቤተ ክርስቲያን ያላቸውን ኹለገብ ተሳትፎ እንዲያሳድጉበት፣

ታስቦ ከ፳፻፬ ዓ.ም. ጀምሮ በአጥቢያ አብያተ ክርስቲያናት፣ በወረዳ/ክፍላተ ከተሞች አብያተ ክህነት ጽ/ቤቶች እና በአህጉረ ስብከት ደረጃ በተቋቋሙ የሰንበት ት/ቤቶች አንድነት መሠረትነት የተቋቋመ መኾኑ ተገልጧል፡፡

ለኹሉም ሰንበት ት/ቤቶች በሚበጁ የአገልግሎት ስልቶች፣ መሪ ዕቅዶች፣ መንፈሳዊና ሀገራዊ ፋይዳ በተላበሱ የልማት ሐሳቦችና ወጥ የመፍትሔ አቅጣጫዎች ላይ በማተኮር የሚያገልግለው ሀገር አቀፍ የሰንበት ት/ቤቶች አንድነት ለኹለት ቀናት የሚመክርበትን የጠቅላላ ጉባኤ መርሐ ግብሩን የሚያከናውነው በመንበረ ፓትርያርክ ጠቅላይ ቤተ ክህነት አዳራሽ እንደኾነ ተጠቅሷል፡፡

በጠቅላላ ጉባኤው፣ የአዲስ አበባ 160 አድባራትና ገዳማት ሰንበት ት/ቤቶችን ሊቃነ መናብርትን ጨምሮ ከ36 አህጉረ ስብከት ከእያንዳንዳቸው አምስት አምስት ልኡካን (የአህጉረ ስብከት ሥራ አስኪያጆች፣ የሰንበት ት/ቤት ክፍሎች ሓላፊዎች፣ ሦስት የየአህጉረ ስብከቱ ሰንበት ት/ቤቶች አንድነት አመራሮች) በአጠቃላይ 500 ያህል ተሰብሳቢዎች በተወካይነት እንደሚሳተፉበት ታውቋል፡፡

ሀገር አቀፉ ጠቅላላ ጉባኤ በሥራ ላይ በሚውልባቸው ቀናት÷ ከማደራጃ መምሪያው እስከ አጥቢያ አብያተ ክርስቲያናት ድረስ ለአዳጊ ሕፃናትና ለወጣቶች ወጥና ኹለገብ አገልግሎት ለመስጠትና የሰንበት ት/ቤቶችን ትስስር በማጠናከር ዘመኑን ለመቅደም ያስችላል በተባለውና ጥቅምት ፲፬ ቀን ፳፻፮ ዓ.ም. በቅ/ሲኖዶስ ምልዓተ ጉባኤ ውሳኔ በጸደቀው የሰንበት ት/ቤቶች አንድነት ጠቅላላ ጉባኤ የውስጥ መመሪያ ላይ የግንዛቤ ማስጨበጫ ውይይት እንደሚያካሒድ ተጠቁሟል፡፡

በመምሪያው የአምስት ዓመት ስትራቴጅያዊ ዕቅድ መሠረት የሕፃናት ትምህርት መማሪያና መዝሙር አገልግሎት በወጥነት ለማስፈጸም የአዲስ አበባ ሀ/ስብከት ሰንበት ት/ቤቶች አንድነት ያዘጋጀውና በሞዴልነት የተወሰደው ሰነድም ለውይይት ይቀርባል ተብሏል፡፡

በየአህጉረ ስብከቱ ሰንበት ት/ቤቶች ያጋጠማቸውን ችግር በተመለከተ ጉባኤው የቡድን ውይይት የሚያደርግ ሲኾን ከዚኹ ጋራ በተያያዘ በተለይ በሰንበት ት/ቤቶችና በአማሳኝ የአጥቢያ አስተዳዳሪዎች መካከል የሚፈጠሩ ችግሮች መንሥኤና አፈታታቸው የጉባኤው ቀዳሚ ትኩረት እንደሚኾን ይጠበቃል፡፡

abune-qelemntos2

ብፁዕ አቡነ ቀሌምንጦስ የሰንበት ት/ቤቶች ማደራጃ መምሪያ የበላይ ሓላፊና የከምባታ ሐዲያና ጉራጌ አህጉረ ስብከት ሊቀ ጳጳስ

የሰንበት ት/ቤቶች ማደራጃ መምሪያ ለመንበረ ፓትርያርክ ጠቅላይ ቤተ ክህነት በመጋቢት ወር መጀመሪያ ላይ ያቀረበው የስምንት ወራት የሥራ አፈጻጸም ሪፖርት እንደሚያስረዳው፣ የመልካም አስተዳደርና የፍትሕ ዕጦት የሰንበት ት/ቤቶች ዋነኛ ችግር ነው፡፡

ሪፖርቱ እንደሚያትተው፣ የሰንበት ት/ቤት ወጣቶች በየቦታው እየተንገላቱና እየታሰሩ ናቸው፤ የሰንበት ት/ቤት የሥራ አመራር አባላት መብታቸው በሕግ አግባብ ሲጠይቁ ከአጥቢያ እስከ ሀገረ ስብከት ድረስ ያሉ ሓላፊዎች ችግራቸውን ተረድተው በአግባቡና በወቅቱ አይፈቱላቸውም፤ እንዲያውም በሙስና እና ብልሹ አሠራር የተዘፈቁ የደብር አለቆችና ጸሐፊዎች የላይ ፈሪ የታች ፈሪ እያሉ ‹‹የጽዋ ማኅበራትን በተጓዳኝ እያደራጁባቸው ነው፡፡››

የችግሮቹ መፍትሔ ግልጽ የወጣቶች ርእይና ስትራተጂ በማስቀመጥ የሰንበት ት/ቤቶችን አንድነት አደረጃጀት ከሀገር አቀፍ እስከ አጥቢያ ማጠናከር መኾኑን የሚያስቀምጠው ሪፖርቱ÷ አደረጃጀቱን ለመምራት የሚያስችል የውስጥ መመሪያ በቅ/ሲኖዶስ መጽደቁን፣ ፳፻፮ እና ፳፻፯ ዓ.ም. ዝርዝር የድርጊት መርሐ ግብር ከመንበረ ፓትርያርክ እስከ አጥቢያ በማውረድ እንዲሠራበት መደረጉን፣ የኹሉንም የሰንበት ት/ቤቶች አደረጃጀቶች እንቅስቃሴ በማእከል ቁጥጥርና ክትትል እየተደረገበት መኾኑን ዘርዝሯል፡፡

ሪፖርቱ አክሎም፣ ለማደራጃ መምሪያው የሚፈቀደው የበጀት መጠን መምሪያው በዓመታዊ ዕቅድ ደግፎ ከሚያቀርበው የበጀት ጥያቄ ጋራ አለመመጣጠኑ፣ መመሪያው በሀገር አቀፍ ደረጃ ያወጣውን የሥልጠናና ግንዛቤ ማስጨበጫ መርሐ ግብር ለማጠፍ እንዳስገደደው፣ የሥርዓተ ትምህርትና የመዝሙር መጻሕፍትን በወቅቱ ለማሳተም እንዳገተው አስታውቋል፡፡

ሌሎች የመምሪያው ምንጮች በበኩላቸው፣ የበጀት እጥረት ለተጠቀሱት ችግሮች በመንሥኤነት መጠቀሳቸውን ቢቀበሉትም ከዐሥርት ዓመታት በላይ በማደራጃ መምሪያው በሓላፊነት የቆዩት ዋና ሓላፊ መ/ር ዕንቊ ባሕርይ ተከሥተ የአመራር ብቃት እንዲሁም ክፉኛ የተጠናወታቸው የአግላይነትና ጠቅላይነት አባዜ ተያይዞ ሊታይ እንደሚገባው ያሳስባሉ፡፡

EOTC SSGAssembly

የሰንበት ት/ቤቶች ሀገር አቀፍ አንድነት ጠቅላላ ጉባኤ

ምንጮቹ እንደሚገልጹት፣ ዋና ሓላፊው የኢትዮጵያ ቤተ ክርስቲያን ሰንበት ት/ቤቶችን በማደራጀትና በማስተባበር ለመምራት ያላቸው ብቃት የዘመኑ ኦርቶዶክሳውያን ወጣቶች የደረሱበትን ንቃትና የአገልግሎት ዝግጁነት የሚመጥን አይደለም፤ በጽኑ አቋማቸውና ክሂላቸው የሚታወቁ የሰንበት ት/ቤት አባላትን ‹‹የማኅበረ ቅዱሳን አባላት ናችኹ›› በሚል እየፈረጁ ለማሸማቀቅና ለመከፋፈል ይሞክራሉ፤ ‹‹የማኅበሩ አባላትኮ ወንድሞቻችን ናቸው፤›› የሚል ከሰጧቸውም ውሰጥ በጠቅላላ ጉባኤ እንዳይሳተፉ እስከማገድና እስከማዋከብ ደርሰዋል፡፡

ከነገ ጀምሮ በሚካሔደው ጠቅላላ ጉባኤ ላይ እንኳ አህጉረ ስብከት የሚያቀርቧቸውን ሪፖርቶች ኹሉ እኔ ካላቀረብኹ በሚል ከአዘጋጅ ኮሚቴው ጋራ ግጭት ውስጥ የገቡት ዋና ሓላፊው ለመመሪያውና ለሰንበት ት/ቤቶች መራራቅ መንሥኤ መኾናቸውን በምሬት የሚናገሩት ምንጮቹ፣ ሰንበት ት/ቤቶችና የአንድነት አመራሮች ከዋና ሓላፊው መ/ር ዕንቊ ባሕርይ ስምምነት በማጣታቸው ከመምሪያው የበላይ ሓላፊ ሊቀ ጳጳስ ብፁዕ አቡነ ቀሌምንጦስ ጋራ እጅና ጓንት ኾነው በመሥራት ላይ እንደሚገኙ ገልጸዋል፡፡

በአኹኑ ወቅት ከመምሪያው ብፁዕ ሊቀ ጳጳስ የተጠናከረ መልካም ግንኙነት እንዳለ የሚያስረዱት ምንጮቹ÷ መመሪያው ከፍተኛ የበጀት እጥረት እንዳለበት በተገለጸበት ኹኔታ ለጉባኤ ዝግጅት የተጠቀመበት የሰንበት ት/ቤቶች የገንዘብ አስተዋፅኦ ሒሳብ ሪፖርት በዋና ሓላፊው አለመቅረቡን፣ ፹፩ዱ መጽሐፍ ቅዱስ ለሰንበት ት/ቤቶች ለማሰራጨት ታቅዶ የተሰበሰበው ገንዘብ ስርጭቱ ሳይከናወን በመቅረቱ የደረሰበት እንደማይታወቅ በመጥቀስ በዋና ሓላፊው ላይ ሌላም ብርቱ ጥያቄ እንዳላቸው አልሸሸጉም፡፡

ዘንድሮ የማደራጃ መምሪያው ለኹለት ቀናት ለሚያካሒደው ጠቅላላ ጉባኤ የሚያስፈልገው 106 ሺሕ ብር ወጪ የአዲስ አበባ አድባራትና ገዳማት 160 ሰንበት ት/ቤቶች እያንዳንዳቸው በተጣለባቸው ድርሻ መጠን ባደረጉት አስተዋፅኦ መሸፈኑና እንዲሁም በማኅበረ ቅዱሳን የቁሳቁስ ድጋፍ መደረጉ ታውቋል፡፡

በአኹኑ ወቅት ከጠቅላላው የሀገሪቱ ሕዝብ ከኃምሳ ሚልዮን በላይ መድረሱ በተነገረው የኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ሃይማኖት ተከታይ ምእመን ውስጥ ኻያ ሚልዮን ያህሉ ወጣቶች ናቸው፡፡ በኢትዮጵያ ብቻ 37‚332 አብያተ ክርስቲያናት እንዳሉ የማደራጃ መመሪያው የመጋቢት ወር የዕቅድ ክንውን ሪፖርት የሚጠቅስ ሲኾን ሰንበት ት/ቤቶች የተቋቋሙባቸው አጥቢያዎች ብዛት 8610 ብቻ መኾኑን ይጠቅሳል፡፡ በሰንበት ት/ቤቶቹ የታቀፉት ወጣቶች ቁጥር በሪፖርቱ ኹለት ሚልዮን(2‚710‚253) እንደኾኑ ቢጠቀስም ሌሎች መረጃዎች እስከ ከአራት ሚልዮን ሊደርሱ እንደሚችሉ ያመለክታሉ፡፡

በተያያዘ ዜና፣ ከ60 ሺሕ በላይ የአዲስ አበባ ኦርቶዶክሳውያን ወጣቶች በ102 ማኅበራት በመታቀፍ በአንድነት የተደራጁበት የአዲስ አበባ ወጣቶች ማኅበራት ኅብረት የአገልግሎት ፈቃድ በቋሚ ሲኖዶሱ ውሳኔና ውሳኔውን መሠረት አድርጎ ከመንበረ ፓትርያርክ ጠቅላይ ቤተ ክህነት ጽ/ቤት በተጻፈ ደብዳቤ መታገዱ ተገለጸ፡፡

በአዲስ አበባ ሀ/ስብከት የፓትርያርኩ ረዳት ሊቀ ጳጳስ ብፁዕ አቡነ እስጢፋኖስ በኩል በየካቲት ወር የአገልግሎት ደንብ ጸድቆለትና ዕውቅና ተሰጥቶት መንቀሳቀስ የጀመረው የኅብረቱ ፈቃድ የታገደው፣ ‹‹ለማኅበራት ደንብ አልተዘጋጀም፤ ለማኅበራት ኹሉ ወጥ ደንብ ባልተዘጋጀበትና ባልጸደቀበት ኹኔታ የተሰጠ ነው፤›› በሚል እንደኾነ ተዘግቧል፡፡

መንፈሳውያን ማኅበራት በገንዘባቸው፣ በዕውቀታቸውና በጉልበታቸው ለቤተ ክርስቲያን የሚያበረክቱት ትውፊታዊ የበጎ ፈቃድ አገልግሎት የሚታመንበትና አስፈላጊነቱ የማያጠያይቅ ነው፡፡ ይህም በተገቢው ሕግና የቁጥጥር መንገድ ተጠብቆ ሊቀጥል እንደሚችል ቢታወቅም ‹‹በቁጥር ይህን ያህል ደርሰዋል፤ ከአጥቢያ እስከ ላዕላይ መዋቅር፣ ከወጣቱ እስከ መድረኩ ያለውን አገልግሎት ለመቆጣጠር እየሠሩ ናቸው፤›› የሚለው ክሥና ‹‹የፖሊቲካ መድረክና የፖሊቲካ ዓላማዎች ማስፈጸሚያ ሊኾኑ ይችላሉ፤›› በሚል የሚቀርብባቸው ውጫዊ ስጋት በኅብረቱ ላይ ለተላለፈው እግድ በምክንያት ተጠቅሷል፡፡