አቡጊዳ – የሚሊዮኖች ድምጽ ቅስቀሳ በደብረ ማርቆስ (ፎቶዎችን ይዘናል)
ዛሬ ሐሙስ ግንቦት 28 ቀን 2006 ዓ.ም፣ በደብረ ማርቆስ የአንድነት አባላትና ደጋፊዎች በስፋት በራሪ ወረቀቶችን ሲያሰራጩ እንደዋሉ የሚሊዮንች ድምጽ ንቅናቄ ግብረ ኃይል ዘገበ። ከበራሪ ወረቀቶች በተጨማሪ በከተማዋ የተለያዩ ቦታዎች ትላልቅ የማስታወቂያ ፖስተሮች የተለጠፉ ሲሆን፣ በመኪና ዉስጥ በመሆንም ፣ በድምጽ ማጉያ ቅስቀሳ ተደርጓል።
ፖሊስ ሕጋዊ ለሆነው ሰልፍ ቅስቀሳ ሲያደርጉ የነበሩ 10 የደብረ ማርቆስ አንድነት አባላትን አስሮ እንደነበረና ለሰዓታት አቆይቶ እንደፈታ የደረሰን ዘገባ ያመለክታል።
የደብረ ማርቆስ ከተማ በቅድመ ኢሕአዴግ ዘመን፣ የጎጃም ክፍል ሃገር ዋና ከተማ የነበረች ሲሆን፣ ላለፉት ሃያ ሶስት አመታት የኢሕአዴግ አገዛዝ በከተማዋ ይሄ ነው የሚባል ለዉጥ እንዳላመጣ ይነገራል። በቴሌቭን እና ራዲዮ የሚነገረዉ ፈጣን እድግት ፣ በከተማቸው እንዳላዩት የሚናገሩት የደብረ ማርቆስ ነዋሪዎች፣ ዉጭ፣ አንድነት ፓርቲ በጠራዉ ሰልፍ ድምጻቸዉን በድፍረትና በነቂስ ያሰማሉ ተብሎ ይጠበቃል።
«በደብር ማርቆስ ኢሕአዴግ ከጠራቸው ሰልፎች ዉጭ በተቃዋሚዎች ሰልፍ ሲደረግ አይተው እንደማያወቁ የተናገሩት ያነጋገርናቸው አንድ ተንታኝ ፣ የአንድነት ፓርቲ አጥሩን ሰብሮ፣ ሕዝቡ ለመብቱና ለነጻነቱ ድምጹኝ እንዲያሰማ ማድረጉ በራሱ ትልቅ ድል እንደሆነ ይናገራሉ።
የአንድነት ፓርቲ በደብረ ማርቆስ ከሚደረገው ሰልፍ በተጨማሪ በአዳማ/ናዝሬትና በደቡብ ክልል በምትገኘዋ ቁጭ ወረዳ የሚሊዮኖች ድምጽ፡ለፍትሃን ለመሬት ባለቤትነት በሚለው መርህ ሥር ሰልፎች ፣ ሰኔ አንድ ቀን ያደርጋል።















