የሕዳሴ አብዮት!
ተመስገን ደሳለኝ (አዲስ አበባ)
የዛሬይቱ ኢትዮጵያችን ‹‹አብዮታዊ ሁኔታ›› ላይ ለመድረሷ በብዙሃን ዜጐች ዕይታም ሆነ፤ ሂደቱን በተከታተሉ ዓለም አቀፍ ተቋማትና ምሁራን ምልከታ የማይታበል ሐቅ ሊሆን መቃረቡ በዚህ ተጠየቅ ለማነሳው አጀንዳ ገፊ-ምክንያት ነው፡፡ በአናቱም ባለፈው ሳምንት ‹‹የ‹ቀለም› አብዮት ናፍቆት›› በሚለው መጣጥፍ ላይ ለማሳያነት የጠቀስኳቸው ፖለቲካዊ፣ ማሕበራዊ እና ነገረ-ንዋያዊ ችግሮች ተደማምረው፣ ሀገሪቷን በርቀት እንደታዘብናት ሶቪየት ሕብረት፣ አሊያም በቅርበት እንዳስተዋልናት ሶማሊያ በመጪዎቹ ጥቂት ጊዜያት የመፈራረሷን አይቀሬነት ማስረገጣቸውን ልብ እንላለን፡፡ ከዚህ ክፉ የታሪክ ዕጣ ለመታደግም ከሁለት አስርታት በላይ ያስቆጠረውን ይሄን አሮጌ ሥርዓት መቀየር ብቻውን ዘላቂ መፍትሔ ሊያመጣ እንደማይችል ዛሬ ግልፅ እውነታ ሆኗል፤ ምክንያቱ ደግሞ ለዘመናት በገዥነት የተንሰራፋው የፖለቲካ ባሕልም አብሮ ካልታደሰ ነገሩ-ሁሉ ‹‹ታጥቦ ጭቃ…›› ከመሆን አለመዝለሉ ነው።