ሰበር ዜና – ባልተጠናቀቀው የቅ/ሲኖዶስ ምልዓተ ጉባኤ ስብሰባ መግለጫ ተሰጠ፤ ጋዜጠኞችን አደናግሯል
ከግንቦት ፭ – ፲፱ ቀን ፳፻፮ ዓ.ም. ለ16 ቀናት የተካሔደውን የምልዓተ ስብሰባ ውሳኔዎች በ17 ነጥቦች የዘረዘረውና ዛሬ ከቀኑ 10፡00 ላይ የተሰጠው ጋዜጣዊ መግለጫ፣ በፓትርያርኩ ቢነበብም የቅዱስ ሲኖዶሱ ዋና ጸሐፊ ብፁዕ አቡነ ሉቃስ በማኅበረ ቅዱሳን መተዳደርያ ደንብ ላይ የተጀመረው ውይይት ቀጥሎ ውሳኔ እንደሚያሳልፉ ተናግረዋል፡፡
በመግለጫው ተ.ቁ.(12) ላይ የማኅበረ ቅዱሳን መተዳደርያ ደንብ ማሻሻያ ረቂቅ በተመለከተ በ፲፱፻፺፬ ዓ.ም. ወጥቶ የነበረው ደንብ እንዲሻሻል በአጥኚ ኮሚቴው የተዘጋጀው 34 ገጽ ረቂቅ መቅረቡ ተጠቅሷል፤ አያይዞም ‹‹ምልዓተ ጉባኤው ከተመለከተ በኋላ በስፋት ውይይት ተደርጎበታል›› ከማለት በቀር ስለውሳኔ ያመለከተው ነገር የለም፡፡
የማኅበሩ መተዳደርያ ደንብ ማሻሻያ ረቂቅ ለምልዓተ ጉባኤው ቀርቦ በንባብ የተሰማው ትላንት ጥዋት ሲኾን ውይይቱ ግን ከቀትር በኋላ 9፡00 ላይ ተጀምሮ በፓትርያርኩ ተቀባይነት የሌላቸው አቋሞች ሳቢያ ወደ ዝርዝር ጉዳይ ሳይገባ ለዛሬ በይደር ቆይቶ እንደነበር የስብሰባው ምንጮች ተናግረዋል፡፡
ዛሬ ከቀኑ 10፡00 ላይ መግለጫው በፓትርያርኩ ንባብ ከተሰማ በኋላ ጥያቄ ለማቅረብ ባለመፈቀዱ ጋዜጠኞች እንዲወጡ ቢደረግም፣ የቤቶችና ሕንፃዎች አስመላሽ ኮሚቴ ሰብሳቢ መጋቤ ካህናት ኃይለ ሥላሴ ዘማርያም ባልተመለሱ ቤቶችና ሕንፃዎች ጉዳይ አሟልተው እንዲያቀርቡ የታዘዙትን ሪፖርት ለማቅረብ ተጠርተው ሲገቡ ታይተዋል፡፡
ይኹንና ምልዓተ ጉባኤው በመግለጫው፡-
- የቤተ ክርስቲያኒቱ ቋሚ ንብረቶች ኾነው በመንበረ ፓትርያርክ አካባቢ የሚገኙት እስከ አኹን ድረስ ያልተመለሱ አራት ሕንፃዎች በሚመለሱበት ኹኔታ አስፈላጊው ክትትል እንዲደረግ ከስምምነት ላይ መድረሱን ጠቅሷል፡፡
- በአዲስ አበባ ሀ/ስብከት የፓትርያርኩ ረዳት ሊቀ ጳጳስ በመኾን ለመላው አህጉረ ስብከት በአርኣያነት የሚጠቀሰውን የመዋቅር የአደረጃጀትና የአሠራር ለውጥ ጥናት በቅድመ ግንባር የመሩት ብፁዕ አቡነ እስጢፋኖስ በጥያቄአቸው መሠረት ከሓላፊነታቸው ለቀዋል፡፡
- በስብከተ ወንጌልና ሐዋርያዊ ተልእኮ መምሪያ የተዘጋጀው የሚዲያዎች ስርጭት ደንብ ጸድቋል፡፡ በደንቡ መሠረት የብዙኃን መገናኛ ቦርድ በቋሚ ሲኖዶሱ ተቋቁሞ ሥራውን ይጀምራል፡፡
- ገዳማትን መልሶ ማቋቋምና ማጠናከር እንዲቻል የገቢ ምንጭ ለመፍጠር ሰፋ ያለ ጥናት ተጠንቶ እንዲቀርብ በጥቅምቱ ምልዓተ ጉባኤ ብፁዓን አበው ያሉበት አንድ ኮሚቴ በሠየመው መሠረት ተዘጋጅቶ በቀረበው ጥናት ላይ ጉባኤው ተነጋግሮ፣ በ40 ገዳማት ላይ የተለያዩ የልማት ሥራዎችን ለማከናወን የቀረበውን ጥናት ጉባኤው አጽድቆ ሥራ ላይ እንዲውል ወስኗል፡፡
- ቤተ ክርስቲያናችን ሥራዋን በመሪ ዕቅድ እንድታከናውን የተዘጋጀው የመሪ ዕቅድ ዘገባ ለምልዓተ ጉባኤው ቀርቦ በስፋት የተገለጸ ሲኾን የመጨረሻው መሪ ዕቅድ በጥራዝ ተዘጋጅቶ እንዲቀርብና በቋሚ ሲኖዶስ ታይቶ አስፈላጊው እንዲፈጸም ጉባኤው ተስማምቷል፡፡
- የሕገ ቤተ ክርስቲያኑን ረቂቅ ምልዓተ ጉባኤው በንባብ አዳምጦ በአብዛኛው ነጥቦች ላይ ማሻሻያ በማድረግና በማረም ለተጨማሪ እርማት ብፁዓን አባቶች፣ ሊቃውንተ ቤተ ክርስቲያንና የሕግ ባለሞያዎች ያሉበት ኮሚቴ ቅ/ሲኖዶሱ ሠይሟል፤ ለጥምቅምቱ ምልዓተ ጉባኤ እንዲያቀርቡ ተወስኗል፡፡
- ወደፊት ለኤጲስ ቆጶስነት ስለሚመረጡ ቆሞሳት እንዲዘጋጅ ተደርገቶ የነበረውን መመዘኛ ጉባኤው በንባብ ካዳመጠ በኋላ በሕገ ቤተ ክርስቲያኑ ረቂቅ ከተዘረዘረው መመዘኛ ጋራ ተገናዝቦ ለወደፊቱ እንዲቀርብ መመሪያ ሰጥቷል፡፡
- የቅድስት ሥላሴ መንፈሳዊ ኮሌጅ ቦርድ ደንብ በተመለከተ አንዳንድ መሻሻል የሚገባቸው ነጥቦች በመኖራቸው ይህንኑ ደንብ ተመልክተውና መሻሻል የሚገባውን አሻሽለው ለጥቅምት ፳፻፯ ዓ.ም. የቅ/ሲኖዶስ ምልዓተ ጉባኤ የሚያቀርቡ ከሊቃነ ጳጳሳትና ከሕግ ባለሞያዎች ኮሚቴ ተቋቁሟል፡፡
- በቤተ ክርስቲያናችን በቅዱስ ሲኖዶስ ማእከላዊነት የሚደረገው የሜሮን አወጣጥ ዝግጅት ቀጣይነት እንዲኖረው ለማድረግ ሥራውን የሚከታተሉ ሦስት ብፁዓን ሊቃነ ጳጳሳት የተመደቡ ሲኾን በጀትም እንዲያዝ ተወስኗል፡፡
- በእንግሊዝ ለሚኖሩ አገልጋዮችና ምእመናን ሕንፃ ቤተ ክርስቲያን ለመሥራት ለብድር ያቀረቡትን የገንዘብ ጥያቄ ጉባኤው ተነጋግሮ ከጠየቁት 4‚800‚000.00 (ዐራት ሚልዮን ስምንት መቶ ሺሕ ብር) ውስጥ 2‚400‚000.00 (ኹለት ሚልዮን አራት መቶ ሺሕ ብር) በስጦታ እንዲሰጣቸው ኾኖ የገንዘብ አሰባሰቡም በቋሚ ሲኖዶስ ታይቶ ውሳኔ እንዲያገኝ ምልዓተ ጉባኤው መመሪያ ሰጥቷል፡፡
- ፓትርያርኩ በሀገር ውስጥና በውጭው ዓለም ባሉ አህጉረ ስብከት የሚያደርጉት ሐዋርያዊ ጉዞ ለቤተ ክርስቲያን መንፈሳዊና ማኅበራዊ አገልግሎት በእጅጉ ጠቃሚ በመኾኑ ለሐዋርያዊ ጉዞው በሚያስፈልገው በጀት ላይ የማሻሻያ ጥናት ተደርጎ ለቀጣዩ በጀት ዓመት እንዲቀርብ ተወስኗል፡፡
- በመንበረ ፓትርያርክ ቅጥር ግቢ ለብፁዓን አበው ወደ ሕክምና ቦታ ማመላለሻ፣ በውጭ አህጉረ ስብከት የሚኖሩ ብፁዓን አበው ከውጭ ሲመጡና ሲመለሱ መቀበያና መሸኛ የሚኾን መኪና በማስፈለጉ ለቀጣዩ በጀት ዓመት በጀት እንዲያዝ፣ ከበጎ አድራጊዎች ርዳታ እንዲፈለግ ተወስኗል፡፡
- ለሕዳሴ ግድብ ቤተ ክርስቲያናችን ቀደም ሲል ካደረገችው የገንዘብ አስተዋፅኦ በተጨማሪ ብፁዓን አበው የቅዱስ ሲኖዶስ አባላት፣ የመንበረ ፓትርያርክ ጠቅላይ ጽ/ቤት፣ የየወረዳውና የየአጥቢያ አብያተ ክርስቲያናት፣ መንፈሳዊ ኮሌጆች፣ ገዳማትና መንፈሳውያን ት/ቤቶች፣ ሠራተኞች በበጎ ፈቃደኛነት የአንድ ወር ደመወዛቸውን ለቦንድ ግዥ እንዲያውሉ ተወስኗል፡፡

