“ጅብ ቲበላህ በልተኸው ተቀደስ”
ከጸጋዬ ገብረመድኅን አርአያ
ወያኔዎች አዲስ አበባን ከተቆጣጠሩ በኋላ የነበሩትን ዕለታት ክንውኖች በሥርዓት የመመዝገብ ልምድ ያለው ሰው የሚያሰፍራቸው ልዩ ልዩ ሁኔታዎች ይኖሩታል። ከመጀመሪያው ዕለት አንስቶ። የእኔን የመጀመሪያ ዕለት አጭር ማስታወሻ ልንገራችሁ። በማለዳ ተነስቼ ጋቢዬን አጣፍቼ ከበሬ ላይ ቆሜ ሥፍር ቁጥር የሌላቸው አህዮች ወደ መሐል ከተማው (አዲስ አበባ) ሲጓዙ አያለሁ። ያንኑ ያህል ባራባሶ ጫማ የተጫሙ፣ የአካል ዝለት የሚታይባቸውና ከእህል ጋር ከተለያዩ አያል ቀን የሆናቸው የሚመስሉ “ሰብአዊ ፍጥረቶች” አብረዋቸው ይሮጣሉ። ሲያሳዝኑ! ቆይ ቆይ…ከፓስተር ኢንስቲቱት በር ላይ አንድ ጥይት ተተኰሰ። ሌላ ጥይት- ሌላ ጥይት! ሰዎቹ ካለፉ በኋላ ወጣ ብለን ያየነው ሟች በሰፈሩ እንደ ሕሊና ሕመምተኛ የሚታወቅ ነበር።