የአንድነት ሰልፍ በአዳማ ለግንቦት 10 ወይስ….???? – ፍኖተ ነጻነት
የአንድነት ለዲሞክራሲና ፍትህ በአዳማ ሊያደርግ ያሰበው ሰልፍ በትላንትናው ዕለት የማሳወቁ ስራ መከናወኑ ይታወቃል፡፡ይህ በእንዲህ እንዳለ ሰልፉን ለማካሄድ ትችሉ ዘንድ ከአለቆቼ ጋር መምከር አለብኝ ያሉት አቶ ጸጋዬ አበራ የከንቲባ ጽ/ቤት ሐላፊ ሲሆኑ በዛሬው ዕለት ረፋድ ላይ ሰልፉን ከግንቦት 20 በፊት ማድረግ አትችሉም ቢሉም ይህንን የሚገልጽ ደብዳቤ ስላልሰጡን ሰልፉን ለማድረግ ማሳወቅ ብቻ የሚጠበቅብን መሆኑና ከ48ሰዓት በኋላም ሰልፉን ባሳወቅነው ቀን ማለትም ግንቦት 10/2006 ዓ/ም ማድረግ እንደምንችል የተረዳነው መሆናችንን ገልጸን ዛሬ ከሰዓት በኋላ ሙሉ ስንጠብቃቸው ከቆየንበት ቢሯቸው 12፡00ላይ ወጥተናል፡፡
አቶ ፀጋዬ ሰልፉን ከግንቦት 20 በፊት ማድረግ የማይቻለው በከተማው ከፍተኛ የፀጥታ ችግር መኖሩንና እንደሳቸው አገላለፅ ያላቸውን የጸጥታ ሰራተኛ በጠቅላላ በአዳማ ዩኒቨርሲቲው ክልል እየተጠቀሙ በመሆኑ መሆኑንና አሁንም በዚሁ ጉዳይ ስብሰባ ላይ ቆይተው መምጣታቸውን ገልጸውልናል፡፡በተለይም በትላንትናው ዕለት አገርሽቶበት የነበረው የአዳማ ዩኒቨርሲቲ ተማሪዎች ረብሻ ምናልባት እስከመቼ እንደሚረጋጋ እነደማያውቁ ምክንያት በማቅረብ ሰልፉ በ10ም ሆነ በ17 ሊካሄድ እነደማይችልና ምናልባት ከግንቦት 25 በኋላ ማድረግ ትችላላችሁ ስል ደብዳቤ ልሰጣችሁ እችላለሁ ብለዋል፡፡
ይህንን ደብዳቤም በትክከል ቀን ጠቅሼ በዚህ ቀን ማድረግ ትችላላችሁ ብዬ ለመስጠት አልችልም፤ አሁንም ለነገ 4፡00ሰዓት ጊዜ ስጡኝ በማለት ከአለቆቼ ጋር ልመካካር ማለት ጠይቀዋል፡፡ከዚህ አንጻር አዳማው ሰብሳቢ አቶምርቱ እኛ የሚጠበቅብን ማሳወቅ ነውና አሳውቀናል ከዚያም በላይ 48፡00ሰዓት አልፎናልና ህጋዊነታችን ይታወቅ በማለት ገልጾ ከቢሯቸው ልንወጣ ችለናል፡፡በመጨረሻም የአዳማው የህዝብ ግንኙነት ኃላፊ አቶ ተስፋዬ ዋቅቶላ “በከተማውየሰላማዊሰልፍ ፈቃድ ማሳወቂየያ ዴስክ የለም ወይ ?”,ሲል ላቀረበው ጥያቄ አቶ ጸጋዬ “የለም” ሲሉ መልስ ሰጥተዋል፡፡
ለማንኛውም ሰልፋችን በግንቦት 10 እንደተጠበቀ ሆኖ ነገ አራት ሰዓት ከአቶ ጸጋዬ ጀርባ ያለው “ወሳኝ አካል” የሚሰጠንን መልስ ለህዝባችን እናሳውቃለን፡፡የራሷ ኤፍ .ኤም ራዲዮ ወይ ጋዜጣ ወይ መፅሄት የሌላት በስም ብቻ የኦሮሚያ ዋና ከተማ ስትባል የኖረችው አዳማ ከፍተኛ የመልካም አስተዳደር ችግሮችና በተለይም ሙስና የተንሰራፋባት መሆኗን የሚያወቀው ህዝብ ሰልፉን በታላቅ ጉጉት እየጠበቀው መሆኑን በብዙ መንገድ ለማወቅ ችለናል፡፡