በፊርሃ እግዚአብሄር ቦታ ፈሪሃ ኢሕአዴግ ተተክቷል – ተመስገ ደሳለኝ (ክፍል 1)
« የሃይለማሪያም ደሳለኝ ቁልቁለቶች» በሚል በተመስገን ደሳለኝ ከጻፈው የተወሰደ ((ክፍል 1) )
በ2005 ዓ.ም መጀመሪያ አቶ ኃይለማርያም “ጠቅላይ ሚኒስትር” ተደርጎ በኢህአዴግ ሲሾም፤ በፓርቲው ውስጥ አክራሪ ብሔርተኛ የአመራር አባላት ከመኖራቸው አኳያ፤ መቼም ቢሆን “ራሱን ችሎ ይቆማል” ብሎ መጠበቁ ተምኔት እንደሆነ በርካታ የፖለቲካ ተንታኞች መናገራቸው ይታወሳል፡፡ ይህ ኃይል እንኳን እንደ ኃይለማርያም ላለ የድል አጥቢያ መሪ ቀርቶ፣ ከድርጅቱ ምስረታ ጀምሮ እስከ ምኒሊክ ቤተ-መንግስትም ድረስ ታላቅ የተጋድሎ ታሪክ ለነበረው አቶ መለስም ቢሆን ክፍተት ካገኘ አለመመለሱን የ93ቱ ሣልሳዊ ህንፍሽፍሽ በግልፅ አሳይቶ ማለፉ አይዘነጋም፡፡ በተጨማሪም ራሱ መለስ ዜናዊ በድህረ ምርጫ 97 የተፈጠረውን አለመግባባት ተከትሎ ዘብጥያ ወርደው የነበሩትን የቅንጅት አመራሮች “ከእስር እንዲፈቱ ብፈልግም አክራሪው ኃይል ተቃወመኝ” ማለቱን ዊክሊክስ የተሰኘው የመረጃ መረብ የአሜሪካ አምባሳደርን ጠቅሶ ይፋ ማድረጉ ይህንኑ ያስረግጣል፡፡ የአምባሳደሩ መረጃ የተጋነነ፤ አሊያም “ተጋግሮ የቀረበለት ነው” ሊባል ቢችል እንኳ “ጭስ በሌለበት…” እንዲሉ፤ በግንባሩ ውስጥ አክራሪ ኃይል ለመኖሩ በጠቋሚነት ሊወሰድ ይችላል፡፡
ኃይለማርያም ደሳለኝ፣ መለስን ከተካበት ዕለት አንስቶ፣ ያደረጋቸው ዲስኩሮችም ሆኑ ለቀረቡለት ጥያቄ የሰጣቸው ምላሾች በአክራሪው ኃይል ተጽእኖ ሥር ማደሩን ያሳያል፡፡ የድርጅቱ የታሪክ ንባብም ቢሆን፣ በአቅመ ደካማ የመጠቀም የፖለቲካ ጨዋታው የሰነበተ መሆኑን ያመላክታል፡፡ ኃይለማርያም ከሹመቱ በኋላ ከባሕሪው አፈንግጦ፣ ዝነኛዋን የመለስ ዜናዊን ሕዝባዊ ሽብር መፍጠሪያ ‹‹ቀይ መስመር››ን፤ ‹‹እሳት መጨበጥ›› በሚል ተክቶ የተቃውሞ እንቅስቃሴን በሙሉ እስከማስፈራራት መገፋቱም የዚሁ ውጤት ይመስለኛል።
በተቀረ እርሱ ወደ ሥልጣን በመጣበት መጀመሪያ አካባቢ፣ ‹‹ኃይማኖተኛ››ነቱን ብቻ በመጥቀስ ‹‹ቤቴን የወንበዴዎች ዋሻ አደረጋችሁት›› በሚል ሥርዓታዊ ማፍያነትን ባደራጁ ጓደኞቹ ላይ ጅራፍ እስከማወናጨፍ ይደርሳል ተብሎ መገመቱ፣ በግንባሩ ውስጥ የተንሰራፋውን አክራሪ ኃይል በቅጡ ካለመረዳት የመነጨ ነው ብዬ አስባለሁ፡፡
እዚህ ጋ ሳይጠቅስ የማይታለፈው ጥቅምት 10 ቀን 2005 ዓ.ም የወጣው ‹‹ሪፖርተር ጋዜጣ›› በልዩ እትሙ፣ ኃይለማርያም ‹‹ቄስ›› ተብሎ ሊቀባ አንድ ወር ሲቀረው በትምህርት ምክንያት ከሀገር እንደወጣ ካስነበበበት ጋር የሚያያዘው ነው፡፡ ወደ ፖለቲካው ከመቀላቀሉ በፊት የሚያመልክበትን ‹‹የኢትዮጵያ ሐዋርያት ቤተክርስቲያን›› ቄስ ህዝቅኤል ጎዴቦን ‹‹ፖለቲካ ውስጥ መግባት ሀጢአት አይሆንብኝምን?›› ሲል መጠየቁን ጋዜጣው አትቷል፡፡ ግና፣ ምን ዋጋ አለው? ባልተጠበቀ ፍጥነት ከተራ ፖለቲከኝነት አልፎ የሀገሪቱ መሪ ለመሆን በመብቃቱ፣ ‹‹ቅስና››ው በመንገድ ሊቀር ተገደደ እንጂ፡፡ እርሱም ቢሆን ዛሬ እንዲህ አይነት ጥያቄ አያነሳም፤ በፈሪሃ እግዚአብሔሩም ቦታ፣ ፈሪሃ ኢህአዴግ ተተክቷል፡፡ እናም ከእስልምና መንፈሳዊ መሪዎች እስከ ጋዜጠኞችና የተቃዋሚ ፓርቲ አባላት ያሉ ንፁሀን፣ በራሱ አነጋገር ‹‹እሳት በመጨበጣቸው›› ወደ ‹‹ቃሊቲ›› ተላልፈው ምድራዊውን ገሀነም ይቀበሉ ዘንድ ቡራኬ ሰጥቷል፡፡