መልካም አስተዳደር ሲባል – ተመስገን ደሳለኝ
«የሃይለማሪያም ደሳለኝ ቁልቁለቶች» በሚል በተመስገን ደሳለኝ ከጻፈው የተወሰደ (ክፍል 3)
አቶ ኃይለማርያም በስድስት ወር (በጥር) ለተወካዮች ም/ቤት ማቅረብ የነበረበትን ሪፖርት በዘጠኝ ወሩ ባለፈው ሳምንት ባቀረበበት ወቅት፣ ከምርጫው በፊት የፖለቲካ ማሻሻያ መጠበቁ የዋህነት እንደሆነ የጠቆመን፣ የም/ቤቱ አባል አቶ ግርማ ሰይፉ የጠበበው ምህዳርን አስመልክቶ ላቀረበለት ጥያቄ ‹‹ዲሞክራሲ በአንድ ሳምንት ተበጥብጦ አይጠጣም (ፓርቲው ሥልጣን ከያዘ በቀጣዩ ወር ሃያ ሁለተኛ አመቱን መድፈኑን ልብ ይሏል)፣ ዲሞክራሲ ህልውናችን ነው፣ ቀይ ምንጣፍ አናነጥፍም…›› ጅኒ ቁልቋል በሚሉ የእብሪት ገለፃዎች ማለፉ ነው፡፡ ከዚህም በላይ ሪፖርቱ በሀሰተኛና በማደናገሪያ ዘገባዎች የታጀለ እንደነበረ መታዘብ ተችሏል፡፡ ለማሳያነትም ያህል ጥቂቶቹን በአዲስ መስመር እጠቅሳለሁ፡-
መልካም አስተዳደር ሲባል…
የኃይለማርያም ደሳለኝ ሪፖርት በደምሳሳው እውነት ለመናገር የሞከረው መልካም አስተዳደር ያለመኖሩን በተመለከተ ብቻ ነው፡፡ ለማሳያነትም የሚከተለውን ልጥቀስ፡-
‹‹በአገራችን ከፌዴራል ተቋማት ጀምሮ በሁሉም ክልሎችና የከተማ አስተዳደሮች ደረጃው የተለያየ ቢሆንም፣ የመልካም አስተዳደር ችግሮች እንደሚታዩ ሕዝቡ በተለያዩ መድረኮችና አገልግሎት በሚያገኝባቸው ሥፍራዎች ቅሬታዎች እያነሳ መሆኑ ግልፅ ነው፡፡››
ከዚህ በተጨማሪም መንግስታዊ ጉድለቱ ከኪራይ ሰብሳቢነት አንስቶ፤ በመሬት አስተዳደር፣ በታክስ አሰባሰብ እና የጉምሩክ ሥነ-ሥርዓት በማስፈፀም ሂደት፣ በአገልግሎት ተቋማት ውስጥ የሚታይ የአመለካከት ችግር፣ የሥራ ተነሳሽነት አለመኖር፣ ግልፅነት እና ተጠያቂነት መጥፋትንም እንደሚጨምር ሪፖርቱ አትቷል፡፡ ይሁንና ሰዎቹ እንዲህ በድፍረት ያነበሩት ሥርዓትን ክሽፈት ቢያውጁም፣ ቅንጣት ታህል ‹የሕዝብ ተቃውሞ ሊነሳ ይችላል› የሚል ስጋት የለባቸውም፡፡ ስለምን? ቢሉ፣ በአንድ በኩል ስለዲሞክራሲ ማበብና የሕግ የበላይነት እየዘመሩ፤ በሌላ በኩል በእነዚህ ሁሉ ችግሮች ተተብትበው ሥልጣንን በገዛ ፍቃድ ካለመልቀቅም አልፎ ቀጣዩን ምርጫ አጭበርብሮ እና ተቀናቃኞችን ጨፍልቆ ለማሸነፍ ዝግጁ መሆን የሚቻለው በእኛይቱ መከረኛ ኢትዮጵያ ብቻ እንደሆነ ገና ድሮ ገብቷቸዋልና፡፡
ሌላው የአገሪቱን ሀብት በጠራራ ፀሀይ የመዝረፍ እውነታውን ለመረዳት ጠቅላይ ሚንስትሩ ሪፖርቱን ካቀረበበት ሁለት ቀን ቀደም ብሎ (በ14/8/06 ዓ.ም) የፌዴራል ዋና ኦዲተር የ2005ቱን የበጀት ዓመት በተመለከተ ያቀረበውን ሪፖርት ማየቱ ብቻ በቂ ነው፡፡ መስሪያ ቤቱ በተለያየ ምክንያት ከመንግስት ተቋማት በአንድ ዓመት ውስጥ ብቻ እንደባከነ የገለፀው የገንዘብ መጠን በድምሩ 3,207,752,247.05 (ሶስት ቢሊዮን ሁለት መቶ ሰባት ሚሊዮን ሰባት መቶ ሀምሳ ሁለት ሺ ሁለት መቶ አርባ ሰባት ብር ከዜሮ አምስት ሳንቲም) መሆኑን በግላጭ አስቀምጧል፡፡ ይህ እንግዲህ በቀጥታ ከጥሬ ገንዘብ ጋር የተያያዘ ውድመት ነው፡፡ ከዚህ ሌላ በርካታ ችግሮችና ዘረፋዎች መኖራቸውን ሪፖርቱ በስፋት ዘርዝሯል፡፡ ለምሳሌ የሽያጭ መመዝገቢያ መሳሪያን የተመለከተውን ማየት ይቻላል፡፡
ይህ መሳሪያ ሥራ ላይ መዋል ከጀመረበት ጊዜ አንስቶ እስከ 2005 በጀት ዓመት መጨረሻ ድረስ ለግብር ከፋዩ ከተሸጠው ውስጥ 89 በመቶው አገልግሎት ላይ ቢውልም፣ የሽያጭ መረጃን ወደ መረጃ ቋት የሚያስተላልፈው 12 በመቶ ብቻ ሲሆን፤ የተቀረው 88 በመቶ ምንም ነገር እንደማያስተላልፍ ተገልጿል፡፡ እናሳ! ይህ ስለምን ሆነ? ለግብር ሰብሳቢ መስሪያ ቤቱ መረጃ የማያስተላልፉት የሽያጭ መመዝገቢያ መሳሪያዎችስ በእነማን ድርጅቶች እጅ ውስጥ የሚገኙት ይሆኑ? …እውን! ጠቅላይ ሚንስትሩ ለዚህ መልስ ይኖረዋልን?
ስኳር ኮርፕሬሽኖችን ሲባል ….
አቶ ኃይለማርያም ደሳለኝ በሪፖርቱ ላይ ‹‹(አዳዲሶቹ) አብዛኛው የስኳር ፋብሪካዎቻችን በቀጣይ ዓመት ወደ ማምረት ተግባር ይገባሉ ተብሎ ይጠበቃል›› በማለት ቢገልፅም፤ የኦዲት ሪፖርቱ ግን ተቃራኒውን ነው የሚያረዳን፡፡ ይገነባሉ የተባሉት ፋብሪካዎች በኮርፕሬሽኑ የአምስት ዓመት ዕቅድ መሰረት ሁለመናቸው ተጠናቅቆ ወደ ማምረት እንደሚገቡ መገለፁ አይካድም፡፡ ነገር ግን የጣና በለስ ቁጥር አንድ እና ቁጥር ሁለት ግንባታ እስከ ጥቅምት 2005 ዓ.ም ያልቃል ቢባልም፤ በዛው ዓመት መጨረሻም ቁጥር አንድ 45 በመቶ፣ ቁጥር ሁለት 39 በመቶ ብቻ ሲጠናቀቅ፤ በኦሞ-ኩራዝ ደግሞ የፋብሪካው ግንባታ መጠናቀቅ በነበረበት ዓመት 42 በመቶ ብቻ የተሰራ መሆኑን ሪፖርቱ አጋልጧል፡፡ እንዲሁም እስከ ጥቅምት 2006 ዓ.ም ይጠናቀቃል የተባለው የወልቃይቱ ፋብሪካ የኦዲት ሪፖርቱ እስከተዘጋጀበት ጊዜ ድረስ ምንም አይነት የግንባታ ሥራው እንዳልተጀመረ ተገልጿል፡፡
በተጨማሪም የተንዳሆ ስኳር ልማት ፋብሪካ በታቀደለት ጊዜ ባለመጠናቀቁ ምክንያት 5146.09 ሄክታር መሬት ላይ የነበረው የሸንኮራ አገዳ ምርት ዕድሜው በመራዘሙ ተበላሽቶ እንዲወገድ በመደረጉ፣ ፋብሪካው ማግኘት የሚገባውን 102,440,145.00 (አንድ መቶ ሁለት ሚሊዮን አራት መቶ አርባ ሺህ አንድ መቶ አርባ አምስት) ብር ተገቢ ባልሆነ መንገድ ያሳጣው እንደሆነ የኦዲት ሪፖርቱ አትቷል፡፡ ታዲያ ጠቅላይ ሚንስትራችን ‹በሚቀጥለው ዓመት ሥራ ይጀምራሉ› የሚለን የትኞቹን የስኳር ፋብሪካዎች ይሆን? እግዜር ያሳያችሁ! እንዲህ አይነት ያፈጠጠ ነጭ ውሸት የሚነግረን፣ ፕሮጀክቶቹን እስከዚህ ዓመት መስከረም ወር መጀመሪያ ድረስ በበላይነት ይመራ የነበረው አባይ ፀሀዬን አማካሪው አድርጎ ነው፡፡
የሆነው ሆኖ ይህ ሁኔታ የሚያመላክተው ሌላ ጉዳይ ቢኖር አቶ ኃይለማርያም ዛሬም ‹‹እመራዋለሁ›› ለሚለው አብዮታዊ ድርጅቱ ሩቅ የመሆኑን ምስጢር ነው፡፡ በጠቅላይ ሚኒስትርነት በተሾመ ማግስት፣ አቶ መለስ ማሌሊትን ቀብሮ ስለልማታዊ መንግስት ከማንችስተር እስከ ኮሎምቢያ ዩንቨርስቲዎችና ዓለም አቀፍ የአደባባይ መድረኮች መከራከሩን ያልሰማ የሚመስለው ኃይለማርያም ደሳለኝ፣ በመጀመሪያው ከውጭ ጋዜጠኛ (ከቪኦኤው ፒተር ላይን) ጋር ባደረገው ቃለ-መጠየቅ ላይ ‹‹እኛ ተራማጅ ግራ-ዘመም ነን›› ሲል የተደመጠበትም መግፍኤ ይኸው ይመስለኛል፡፡