ኤርትራ ሆይ! ብረሳሽ… – ተመስገን ደሳለኝ

«የሃይለማሪያም ደሳለኝ ቁልቁለቶች» በሚል በተመስገን ደሳለኝ ከጻፈው የተወሰደ (ክፍል 4)

ጠቅላይ ሚንስትሩ ሪፖርቱን ባቀረበበት ወቅት፣ አቶ ግርማ ሰይፉ መንግስት የኤርትራንና የኢትዮጵያን ሕዝብ ለማቀራረብ የሚያደርገውን ጥረት አስመልክቶ ያለውን አቋም በተመለከተ ላነሳው ጥያቄ፣ የሰውየው ምላሽ ከእውነታው ፍፁም ያፈነገጠ ሆኖ አግኝቸዋለሁ፡፡

የኃይለማርያም ማብራሪያ ሁለቱ ሕዝቦች የቀድሞ ግንኙነታቸውን መልሰው እንዲያጠናክሩ ‹‹ኢትዮጵያውያን የኃይማኖት አባቶች እና ምሁራኖች ለሚያደርጉት ጥረት መንግስት ድጋፍ እያደረገ ነው›› የሚል ሲሆን፤ ኤርትራን በተመለከተ ደግሞ ዓለም አቀፉ ማሕበረሰብ በአሸባሪነት ፈርጆ ማዕቀብ ጥሎ እያሰቃያት ከመሆኑም በላይ በአካባቢው ከኢትዮጵያ በስተቀር ተሰሚነት ያለው ሀገር ያለመኖሩን የሚያመላክት አንድምታ አለው፡፡

ይህ ግን ምን ያህል እውነት ነው? ብለን ስንጠይቅ፤ በኤርትራ መገንጠልም ሆነ በለንደኑ ኮንፈረንስ የህወሓትን የበላይነት ያስረገጡትና በአሜሪካን አስተዳደር ተሰሚነት ያላቸው አምባሳደር ኸርማን ኮኽን ኤርትራን ከ‹‹ብርዱ›› ለማውጣት አሜሪካም ሆነች የተባበሩት መንግስታት የጣሉትን ማዕቀብ እንዲያነሱ እና ድንበሩ እንዲሰመር በአደባባይ መጮኽ ከጀመሩ መሰንበታቸውን እንረዳለን፡፡ እንዲሁም ሌላኛው አምባሳደር ዴቪድ ሺንም ኢትዮጵያ ባድመን እስከመስጠት ከሄደች በሁለቱ ሀገራት ሰላም ማምጣት እንደሚቻል ደጋግመው ሲናገሩ ተደምጠዋል፡፡

እናም እነዚህን ሰዎች ጨምሮ ጥቂት የማይባሉ አሜሪካውያን ፖለቲከኞች ኤርትራ እ.ኤ.አ. ከ2009 ዓ.ም ወዲህ ሽብርተኝነትን ከመደገፍ መቆጠቧን ጠቅሰው በመከራከር ላይ መገኘታቸው እውነታውን ፍንትው አድርጎ ሳያል፡፡

የጠቅላይ ሚኒስትሩ ‹‹ኢትዮጵያውያን የኃይማኖት አባቶችና ምሁራኖች…›› ንግግርም በሬ ወለደ ይመስለኛል፡፡ ከዚህ ባለፈ የሀገሬ መንግስት ለተከታታይ አስራ ስድስት አመታት ‹ኤርትራ ሆይ! ብረሳሽ ቀኜ ይርሳኝ›ን የሚዘምረው ሀገር-በቀል ተቀናቃኞቹን በስመ-ሻዕቢያ መጨፍለቅ ሲፈልግ ብቻ መሆኑ ግልፅ ነው፡፡