ሰማያዊ ፓርቲ ታዋቂውን ምሁር ዶ/ር ኃይሉ አርአያን አሰደበ – ዳንኤል ተፈራ
ሰማያዊ በመባል የሚታወቀውና የወጣቶች ፓርቲ እንደሆነ አዘወትሮ የሚናገረው ሰማያዊ ፓርቲ ባለፈው ሳምንት በወጣ ልሳኑ ‹‹ነገረ ኢትዮጵያ›› ላይ ታዋቂውን ኢትዮጵያዊ ምሁርና በተቃውሞ ጎራ እድሜ ሳይገድባቸው ትግል እያደረጉ ያሉትን ምሁር ዶ/ር ኃይሉ አርአያን አሰደበ፡፡
የፓርቲው ልሳን ዶ/ር ሃይሉን ለመሳደብ የተገደደው <<የፖለቲካ ፓርቲዎች መሰባሰብ አለባቸው>> የሚል ጠንካራ አቋም ስላላቸው ሲሆን ሳሙኤል አወቀ በተባለ ጎረምሳ ፀኃፊ በኩል <<የማይረቡና ለሀገር የማይጠቅሙ እንዲሁም አጥፊ>> ተብለው መገለፃቸው ብዙዎችን ያሳዘነ ሲሆን ከኢትዮጵያዊ ጨዋነት ያፈነገጠና ለአባቶች ክብር የማይሰጥ ዘመቻ በፓርቲው ልሳን መጀመሩ በህዝቡ ዘንድ ብዙ ጥያቄ አስነስቷል፡፡
ዶ/ር ኃይሉ በኢትዮጵያ ውስጥ ስመጥር ከሆኑ ምሁራን አንዱ ሲሆን መንግስቱ ሃይለማሪያምን ፊትለፊት ‹‹ስልጣን ልቀቅ!›› ብለው የተጋፈጡ፤ ለኢህአዴግ ስርዓት ተቃዋሚ በመሆናቸው ከዩኒቨርስቲ ከተባረሩ ምሁራን አንዱ የሆኑና ተቃውሟቸውን በመግፋት እስካሁን ደከመኝ ሳይሉ እየታገሉ ያሉ አንጋፋ አባት መሆናቸው ይታወቃል፡፡
ምሁሩ ‹‹ተባበሩ ወይ ተሰባበሩ›› የሚለውን ታሪካዊ ጥቅስ ለመጀመሪያ ጊዜ በመናገራቸው የሚታወቁና አሁንም በፓርቲዎች መሰባሰብ ላይ የሚሰሩ ናቸው፡፡ ታዲያ ሰማያዊ ፓርቲ ልሳኑ ላይ ሀሳብን በሀሳብ መመከት ባልቻለ ፀሃፊ ዶክተሩን ርካሽ ፖለቲካ ትርፍ ፈላጊ ተብለው ተገልፀዋል፡፡
በጋዜጣው የተቆጡ ኢትዮጵያዊያን ፓርቲው ምሁሩን በአስቸኳይ ይቅርታ እንዲጠይቅ አሳስበዋል፡፡ ሰማያዊ ፓርቲ በኢትዮጵያ ተቃዋሚ አለ ብለን አንዋሃድም ማለቱ ይታወሳል፡፡