አቡጊዳ – የሰማያዊ ፓርቲ ከአስተዳደሩ ለሚያዚያ 19 ቀን ሰልፍ እውቅና ተሰጠዉ ( ሰነድ ይዘናል)

የሰማያዊ ፓርቲ ሚያዚያ 19 ቀን 2006 ዓ.ም፣ በአዲስ አበባ ለጠራው ሰላማዊ ሰልፍ፣ የአዲስ አበባ አስተዳደር እውቅና ሰጠ። አስተዳደሩ፣ ሰማያዊ ፓርቲ፣ አስፈላጊዉን የእውቅና ፎርም በመሙላት ወደ ሰልፍ ተግባራቱ መሰማራት እንደሚችል ትላንት ለፓርቲዉ በላከው ደብዳቤ ማሳወቁ ይታወቃል። በዚያ መስረት የሰማያዊ ከፍተኛ አመራር አባላት፣ በአስተዳደሩ የተጠየቀዉን የሰላማዊ ሰልፍና ስብሰባ ማሳወቂያ ቅጽ ፎርም በመሙላት፣ ዛሬ ሚያዚያ 16 ቀን አስፈላጊዉን የእውቅና ሰነድ ተቀብለዋል።BLue-22

የሰማያዊ ፓርቲ ሕጉ በሚፈቅደው መሰረት ለአስተዳደር አሳውቆ፣ አስተዳደሩም ለሰልፉ እውቅና ሰጦ ባለበት ሁኔታ ፣ ፖሊሲ ሕግ ወጥ በሆነ መንገድ ከአሥር በላይ የሰማያዊ ፓርቲ አባላትን፣ ለሰልፉ ቅስቀሳ በማድረጋቸው ያሰረ ሲሆን፣ እስከአሁን በደረሰን መረጃ፣ ታሳሪዎች አሁንም በወህኒ እየማቀቁ ናቸው።

የአንድነት ለዲሞክራሲና ለፍትህ ፓርቲ መጋቢት 28፣ ሚያዚያ 5 እና ለሰማያዊ ፓርቲ እውቅና በተሰጠበት ቀን ሚያዚያ 19፣ ሰልፍ ለማድረግ ቢያሳውቅም እውቅና እንዳላገኘ ይታወቃል። « በሚያዚያ 19 ሌሎች ዝግጅቶች አሉ፡፡ በቂ ጥበቃ ማሰማራት አይቻልም። ለሚያዚያ 26 አድርጉት» የሚል ምላሽ እንደተሰጣቸውና ለሚያዚያ 26 ዝግጅት እያደረጉ እንዳለ የገለጹት ያነጋገርናቸው ከፍተኛ የአንድነት አመራር አባል፣ ለአንድነት ሌላ ምክንያት ተሰጥቶ ለሰማያዊ መፈቀዱ እንዳስገረማቸውና አገዛዙ ሆን ብሎ በተቃዋሚዎች መካከል ልዩነት ለመፍጠር አስቦ እንደሆነ ይናገራሉ።

«ማንም ሰልፉን ይጥራዉ ማንም ፣ ሰማያዊ በጠራዉ ሰልፍ፣ ሚያዚያ 19 ቀን ሕዝቡ ድምጹን በነቂስ ያሰማል የሚል ተስፋ አለኝ። እኛም በሳምንቱ፣ ሚያዚያ 26 ቀን፣ አስተዳደሩ እውቅና ሰጠም አልሰጠም ሰልፍ እንወጣለን። ለሰማያዊ ፓርቲ አክብሮት ስላለን፣ የሚያዚያ 19 ሰልፍ ከተጠናቀቀ በኋላ ነዉ፣ ሰኞ ሚያዚያ 20 ቀን በስፋት በ24ቱም የአዲስ አበባ ወረዳዎች ቅስቀሳ የምንጀምረዉ» ያሉ የአንድነት አመራር አባል፣ ፓርቲዉ አስፈላጊዉን የማቴሪያል፣ የጽሑፍና የሰው ኃይል ዝግጅት አጠናቆ እንደጨረሰ አክለው ገልጸዋል።