አቡጉዳ – በጋራ እንሰራለን ካሉ (ሰማያዊች) ጥሩ ነው – የአንድነት አመራር(ሰንደቅ)
የአንድነት ፓርቲ፣ ለሚያዚያ 26 ቀን በአዲስ አበባ ሰልፍ እንደጠራ፣ ከአዲስ አበባ አስተዳደሩ አስፈላጊዉን እውቅና እንዳገኘ መዘገቡ ይታወቃል። አንድነት ሰልፉን መጋቢት 28 ቀን ጠርቶ የነበረ ሲሆን፣ የአዲስ አበባ አስተዳደር በተባለው ቀን እውቅና ባለመስጠቱ፣ የተለያዩ ዝግጅቶ በመኖራቸውና የአመት በዓላትም ጊዜ በመሆኑ፣ ወደ ሚያዚይ 26 መሸጋገሩን የአመራር አባልቱ ይገልጻሉ። በዚህ ሂደት ከአስተዳደሩ ጋር በርካታ የደብዳቤ ልዉዉጦች የተደረጉ ሲሆን፣ በዓንድነት አመራር አባላትና በአስተዳደር ባለስልጣአንት መካከል ዉይይቶች ተደርገዋል።
ከአስተዳደሩ ጋር የነበሩ በርካታ የደብዳቤ ልዉዉጦችን መደረጋቸው፣ መብትን ለማግኘት እንደ መለማመጥ ይቆጠር እንደሆነ በመግለጽ ሰንደ አግዜጣ ላቀረበላቸው ጥያቄ መልስ የሰጡት የአንድነት የሕዝብ ግንኙነት ክፍላ ሃላፊ አቶ ሃብታሙ አያሌው «መደራደር ማለት የዘመናዊ ፖለቲካ ማሳያ እንጂ የአንበርካኪና የተንበርካኪነት ስሜት አይደለም» ሲሉ አንድነት የሰለጠነ እንጂ የጀብደንኘት ፖለቲካን እንደማይራምድ ገልጸዋል።
ሰማያዊ ፓርቲ በተናጥል የጠራዉን ሰልፍ በተመለከተ የተጠየቁት አቶ ሃብታሙ «ከመንግስት ጋር ውይይት እያደረግን ባለንበት ወቅት በመሐል መጥቶ ሰልፍ ጠርቼአለሁ ከማለት ይልቅ አንድነት የጠራውን ሰልፍ ደግፎ መውጣት በተገባ ነበር። በአንፃሩ የዚህችን ሀገር ትልቅ ችግር ፈጣሪ ትቶ አንድነት መታገል ትክክል ነው ብለው ካመኑና አዋጪም ነው ብለው ካሰቡ ይቀጥሉ» ሲሉ ያላቸው ቅሬታ ገልጸዋል። ሰማያዊ ፓርቲ ከአንድነት ጋር ለመስራት ፍቅደኛ ከሆነ አንድነት በሩ ሁልጎዜ ክፍልት እንደሆነ የገለጹት አቶ ሃባትሙ «በጋራ እንሰራለን ብለው ከመጡ ጥሩ ነው» ሲሉ በጋራ አብሮ የመስራትን ጥቅም አስምረዉበታል።
ሰንደቅ ከአቶ ሃብታሙ ጋር ያደረገዉን ቃለ ምልልስ የተወሰነዉን እንደሚከተለው አቅርበናል።
ሰንደቅ፡- ሰላማዊ ሰልፍ ሕገ-መንግስታዊ መብት ከመሆኑ አንፃር ከመንግስት ጋር ተደጋጋሚ የደብዳቤ ልውውጥ በማድረጋችሁ መብታችሁን ተለማምጣችሁ እየጠየቃችሁ እንደሆነ የሚገልፁ ወገኖች አሉና ስለዚህ ጉዳይ ያለዎት አስተያየት ምንድነው?
አቶ ሀብታሙ፡- እኔ እንደማስበው ይሄንን እያሉ ያሉ ወገኖች ፖለቲካን በአግባቡ ያልተረዱ ይመስለኛል። በአጉል ጀብደኝነት አገር አይመራም። ጀብደኝነት ፖለቲከኝነት አይደለም። ፖለቲከኛነት ብስለት ይጠይቃል። ፖለቲከኝነት መግባባትና ድርድር ማድረግ ያስፈልጋል። ተወደደም ተጠላም ይሄ ስርዓት በመላ ሀገሪቱ ቢያንስ ደመወዝ ከፍሎ የሚያስተዳድረው ከአንድ ሚሊዮን በላይ ሰራተኛ ወይም አባላት አሉት። ይሄ ስርዓት የሚያንቀሳቅሳቸውን እነዚህን ወገኖች ኢትዮጵያዊ አይደላችሁም ብለህ ፖለቲከኛ ልትሆን አትችልም። ስለሆነም በመነጋገርና ዴሞክራሲያዊ በሆነ መንገድና በሰለጠነ መንገድ ለመፍታት መሞከር ሀገሪቷን ዘመናዊ ፖለቲካ እንድትላበስ ያደርጋል።
መንግስት ከሕግ ውጪ ሲሆን አንድነት አይታገስም። አንድነት ተንበርካኪ ቢሆን ደሴ ወላይታ፣ አርባ ምንጭ፣ ጎንደር ሰላማዊ ሰልፍ አያደርግም ነበር። መደራደር ማለት የዘመናዊ ፖለቲካ ማሳያ እንጂ የአንበርካኪና የተንበርካኪነት ስሜት አይደለም። ይሄንን ሰልፍ ለማካሄድ የአዲስ አበባ አስተዳደር በአንድ ሳምንት ውስጥ አራት ደብዳቤ ነው የፃፈልን።
ይህ አስተዳደር በተቋም ደረጃ ወደ መነጋገር ሲመጣ እናበረታታለን እንጂ ወደ ሌላ ጫፍ ገፍተን “አሰርን ፈታን” እያልን በጭቅጭቅ ፖለቲካ የሚዲያውን አየር ለመቆጣጠር መሞከር መሠረት የሌለው ፖለቲካ የሚያሳይ ነው። አንድነት ግን መሠረት ያለው የፖለቲካ ፓርቲ እንደመሆኑ መጠን ሀገር በጀብደኝነት ይመራል ብሎም አያምንም። ከማንኛውም አካል ጋር ይነጋገራል።
ሰንደቅ፡- ቀደም ሲል በጃንሜዳ ሰልፍ ማድረግ ሕገ-ወጥ መሆኑን ስትጠቅሱ ነበር አሁን ደግሞ ሰልፉን ጃንሜዳ ለማድረግ ወስናችኋልና ለምን?
አቶ ሀብታሙ፡- በእኛ በኩል ግልፅ አቅጣጫ ይዘን ነው እየተንቀሳቀስን ያለነው። ለአስተዳደሩም ይህንኑ ጉዳይ አቅርበናል። በጃንሜዳው ጉዳይ ክስ መስርተን አለአግባብ የጦር ካምፕ ወዳለበት ቦታ ሂዱ ብሎ ገፍቶናል ብለን የቃል ክርክር ተደርጓል። በቃል ክርክሩም አስተዳደሩ ላይ ክሱን ሲከላከል የነበረው ጃንሜዳ አካባቢ ምንም አይነት የጦር ካምፕ የለንም ቀደም ሲል ነበር አሁን ግን የለም ብሎ ክዶ ተከራክሯል። በእኛ በኩል የጦር ካምፕ አለ ብለን ተከራክረናል። ጉዳዩም በፍርድ ቤት እንደተያዘ ነው። ዋናው ነገር የአዲስ አበባ አስተዳደር አካባቢው በጦር ካምፕነት አያገለግልም። በቦታውም ሰላማዊ ሰልፍ ማድረግ አለባችሁ ብሎ ደብዳቤ እስከፃፈና ጉዳዩም በፍርድ ሂደት ላይ እስካለ ድረስ በጃንሜዳ ሰልፍ አናደርግም የምንልበት ምክንያት የለም። ከዚህ አንፃር ኃላፊነትም የሚወስደውም ሕግ በመጣስ የሚጠየቀውም አስተዳደሩ ነው። በእኛ እምነት ቦታው የትም ይሁን የትም ዋናው ጉዳያችን በዚህ ስርዓት ተቸግሬአለሁ ያለ፣ የአስተዳደሩን በደል የተረዳ ከሚደረገው የደህንነትና የካድሬ አፈና ተላቆ አንድ ሚሊዮን ሕዝብ ጽ/ቤት ቢመጣ በቀላሉ ሰልፉ አራት ኪሎ ደርሷል ማለት ነው። ስለሆነም በእኛ በኩል የሕዝቡን የትግል ስሜት የምንለካበት ነው። ሕዝቡ ይውጣ እንጂ የትም ቦታ ይሁን ችግራችን አይደለም። ነገር ግን ኢህአዴግ መስቀል አደባባይ እየተሰለፈ አንድነትን ወደሌላ የሚገፋ ከሆነ ግን አንቀበለውም፤ አንታገሰውም።
ሰንደቅ፡- ሰማያዊ ፓርቲ ከሞላ ጎደል እናንተ ያነሳችሁትን የሚመስል ጥያቄ በማንገብ ለሚያዝያ 19 ሰላማዊ ሰልፍ ጠርተዋል። ጥያቄአችሁ ከመቀራረቡ አንፃር የአንድን ከተማ ሕዝብ በየሳምንቱ ሰልፍ ውጣ ማለት ምን ያህል ተገቢ ነው?
አቶ ሀብታሙ፡- እንደማስበው የኢትዮጵያ ፖለቲካ ታሟል የሚባለው ከዚህ በመነሳት ነው። በተመሳሳይ ጉዳይ ላይ ለምን ትጠራላችሁ አንልም። ነገር ግን የፖለቲካ ጠቀሜታውን መገምገም የፖለቲከኞቹ ብቃትና ቅንነት ጉዳይ ይመስለኛል። ግልፅ የሆነ የትግል አላማ ማስቀመጥና ያለማስቀመጥ ጉዳይ ይመስለኛል። እውነት ነው ጥያቄአችን ላይ የጎላ ልዩነት የለም። የሕዝብ መፈናቀልን በተመለከተ በደሴው ሰልፍ ላይ ተነስቷል። ከዚህ በፊትም አንስተነዋል፤ ዛሬም እናነሳዋለን። ነገር ግን አንድነት ሁልጊዜ በአንድ ጉዳይ ማላዘን የለበትም ብለን እናስባለን። ስለዚህ በእኛ በኩል ተራማጅ የሆነ የተጠና ትግል ነው የምናደርገው። በአንድ ጊዜ ሁለት ሦስት ከተማ ሰልፎች መጥራት ጀምረናል። በመላ ሀገሪቱ በአንድ ቀንና በተመሳሳይ ሰዓት ሰልፍ ማድረግ እንችላለን። በእርግጥም እኛ አደባባይ ባንናፍቅም ስርዓቱ እየገፋን ነው። በዚያው ጎን ለጎን ወደ በመነጋገር ፖለቲካ እየለመንን ሳይሆን ሕዝባዊ አቅማችንን ከፍ በማድረግ ኢህአዴግን ለመለወጥ እየሰራን ነው። ከመንግስት ጋር ውይይት እያደረግን ባለንበት ወቅት በመሐል መጥቶ ሰልፍ ጠርቼአለሁ ከማለት ይልቅ አንድነት የጠራውን ሰልፍ ደግፎ መውጣት በተገባ ነበር። በአንፃሩ የዚህችን ሀገር ትልቅ ችግር ፈጣሪ ትቶ አንድነት መታገል ትክክል ነው ብለው ካመኑና አዋጪም ነው ብለው ካሰቡ ይቀጥሉ።