ወቅታዊ ተግዳሮቶቼን የምፈታው በምክክርና በጸሎት ነው – ማኅበረ ቅዱሳን
- ማኅበሩ ትውልዳዊ ተልእኮውን ለአባቶች በመታዘዝና በሥርዓተ ቤተ ክርስቲያን በመወሰን የመፈጸም አሠራሩና ፍላጎቱ እንደጸና መኾኑንና ከዚኽ ውጭ በሌላ መንገድ የሚመጣ መፍትሔ ይኖራል ብሎ እንደማያምን የሥራ አመራር ጉባኤው አስታውቋል፡፡
- መንግሥት አካሒዳለኹ ከሚለው የፀረ አክራሪነት ትግልና ቤተ ክርስቲያኒቱ በቅዱስ ሲኖዶስ ወስና የአፈጻጸም አቅጣጫ ከሰጠችበት የአደረጃጀትና አሠራር ለውጥ አፈጻጸም ጋራ በተያያዘ በተለያዩ አካላት የሚሰነዘሩበትን የስም ማጥፋት ዘመቻዎችና መሠረተ ቢስ ክሦች ከአባቶች፣ ከአስተዳደር ሓላፊዎች፣ ከሰንበት ት/ቤቶች፣ ከመንፈሳውያን ማኅበራትና ከመላው ምእመናን ጋራ ተቀራርቦ በመረዳዳትና በጸሎት ፍትሐ እግዚአብሔርን በመጠየቅ የመፍታት የወትሮ ጥረቱ ተጠናክሮ ይቀጥላል፡፡
(አዲስ አድማስ፤ ቅጽ ፲፫ ቁጥር ፯፻፵፫፤ ቅዳሜ ሚያዝያ ፬ ቀን ፳፻፮ ዓ.ም.)
በከፍተኛ የትምህርት ተቋማት የሚማሩ የኦርቶዶክስ ተዋሕዶ እምነት ተከታይ ወጣቶችን አደራጅቶ የቤተ ክርስቲያኒቱን እምነት፣ ሥርዓትና ትውፊት እንዲማሩና የአበው ተተኪ እንዲኾኑ በቅ/ሲኖዶስ ጸድቆ በተሰጠው መተዳደርያ ደንብ መሠረት የሚያገልግለው ማኅበረ ቅዱሳን÷ በየመድረኩ ከሚሰማው የአክራሪነት ፍረጃና ከቤተ ክርስቲያኒቱ የአደረጃጀትና አሠራር ለውጥ እንቅስቃሴ ጋራ በተያያዘ የገጠሙትን የስም ማጥፋትና የማኅበሩን አገልግሎት የማሰናከል ወቅታዊ ተግዳሮቶች ተቀራርቦ በግልጽ በመመካከርና በጸሎት መፍትሔ ለማስገኘት ሲያደርግ የቆየውን ጥረት አጠናክሮ እንደሚቀጥልበት ገለጸ፡፡
የማኅበሩ የሥራ አመራር ጉባኤ ከመጋቢት 27 – 28 ቀን 2006 ዓ.ም በአቡነ ጎርጎሬዎስ የትምህርትና ሥልጠና ማእከል አዳራሽ ባካሔደውና ከ45 የሀገር ውስጥና የውጭ ማእከላት የተውጣጡ 160 ያህል አመራሮች በተሳተፉበት የመጀመሪያ መንፈቅ ዓመት መደበኛ ስብሰባ፣ በቤተ ክርስቲያኒቱ ተቋማዊ ህልውናና በማኅበሩ አገልግሎት ቀጣይነት ላይ ተጋርጧል ያላቸውን ወቅታዊ ተግዳሮቶች በዝርዝር በመገምገም ቀጣይ የመፍትሔ አቅጣጫ ማስቀመጡ ተጠቁሟል፡፡
የሥራ አመራር ጉባኤው ያለፉትን ስድስት ወራት የአገልግሎት ዕቅድ ክንውን ሪፖርት በማዳመጥና በስፋት ቀርቧል በተባለው የወቅታዊ ኹኔታዎች ግምገማ ላይ በጥልቀት በመምከር ባስቀመጠው የመፍትሔ አቅጣጫ÷ ማኅበሩ በቅዱስ ሲኖዶስ ጸድቆ በተሰጠው መተዳደርያ ደንብ መሠረት ትውልዳዊ ተልእኮውን ለአባቶች በመታዘዝና በሥርዓተ ቤተ ክርስቲያን በመወሰን የመፈጸም አሠራሩና ፍላጎቱ እንደጸና መኾኑንና ከዚኽ ውጭ በሌላ መንገድ የሚመጣ መፍትሔ ይኖራል ብሎ እንደማያምን አስታውቋል፡፡
በተዛባ አመለካከትና በሐሰተኛ ክሥ የቤተ ክርስቲያኒቱን አባቶችና የመንግሥት አካላትን ግራ በማጋባትና በማሳሳት የማኅበሩን አገልግሎት ማስተጓጎል ዋነኛ አጀንዳ አድርገዋል ባላቸው ግለሰባዊና ቡድናዊ ቅስቀሳዎች ላይ የሥራ አመራር ጉባኤው በትኩረት መወያየቱ ተነግሯል፡፡
መንግሥት አካሒዳለኹ ከሚለው የፀረ አክራሪነት ትግልና ቤተ ክርስቲያኒቱ በቅ/ሲኖዶስ ወስና የአፈጻጸም አቅጣጫ ከሰጠችበት የአደረጃጀትና አሠራር ለውጥ አፈጻጸም ጋራ በተያያዘ በተለያዩ አካላት የሚሰነዘሩበትን የስም ማጥፋት ዘመቻዎችና መሠረተ ቢስ ክሦች ከአባቶች፣ ከአስተዳደር ሓላፊዎች፣ ከሰንበት ት/ቤቶች፣ ከመንፈሳውያን ማኅበራትና ከመላው ምእመናን ጋራ ተቀራርቦ በመረዳዳትና በጸሎት ፍትሐ እግዚአብሔርን በመጠየቅ የመፍታት የወትሮ ጥረቱ ተጠናክሮ የሚቀጥልበትን አቅጣጫ ማስቀመጡን ምንጮች ገልጸዋል፡፡
የማኅበሩ ዓላማና ፍላጎት ከቤተ ክርስቲያኒቱ ሐዋርያዊ ተልእኮ የሚነሣና ጥቅሙም ለቤተ ክርስቲያኒቱ በመኾኑ ከቤተ ክርስቲያኒቱና ከሀገሪቱ ህልውና የሚቀድም የተለየ የማኅበር (ቡድናዊ) ዓላማና ጥቅም እንደሌለም የሥራ አመራር ጉባኤው ውሳኔ ገልጦአል፡፡
የማኅበሩ አባላት በመተዳደርያ ደንቡ በሰፈረው የአባላት መብትና ግዴታ መሠረት በቤተ ክርስቲያኒቱ የአገልግሎት መዋቅሮች ውስጥ ታቅፈው ቤተ ክርስቲያኒቱ በምታዛቸው ማንኛውም መንፈሳዊና ማኅበራዊ ግዳጆች በመሳተፍ ሐዋርያዊ ተልእኮዎቿን የማጠናከር፣ መብቶቿንና ጥቅሞቿን ለማስጠበቅ ከሚመለከታቸው የቤተ ክርስቲያኒቱ አካላትና አገልጋዮች ጋራ በመደጋገፍ የመቆም ድርሻቸውን በላቀ መንፈሳዊና ሞያዊ ብቃት መወጣታቸውን እንዲቀጥሉ በአጽንዖት አሳስቧል፡፡
ኢትዮጵያ የተለያዩ እምነቶችና ባህሎች ሀገር መኾኗን በቅጡ እንደሚገነዘብ የገለጸው ውሳኔው፣ የማኅበሩ አባላት እያንዳንዳቸው ሕጋቸውና መመሪያቸው ያደረጉትን የቤተ ክርስቲያኒቱን ትምህርተ ሃይማኖት፣ ወራሽና ተቀባይ የኾኑለትን ሥርዓትዋንና ክርስቲያናዊ ይትበሃሏን በመንፈሳዊና አእምሯዊ መንገድ ከመጠበቅና ከማስከበር በቀር ሌላው አይኑር በሚል በአመለካከትና በአስተሳሰብ የተለዩ ወገኖችን አጥርና ቤት በኃይልና በጫና የመነቅነቅና የመጋፋት ባሕርያዊ መገለጫ ይኹን ድርጊታዊ ተሞክሮ እንደሌላቸውና እንደማይኖራቸው ጠቅሷል፡፡
አባላቱንና ተቋማዊ አሠራሩን በተመለከተ በማስረጃ ተደግፈው የሚቀርቡለትን ችግሮች ከመተዳደርያ ደንቡና ከውስጣዊ አሠራሩ አኳያ ያለማመንታት ለማረም ምንጊዜም ዝግጁ እንደኾነ የመከረው የሥራ አመራር ጉባኤው፣ እንደ ምእመንነታቸው ቤተ ክርስቲያናቸውን ከመከባከብ ባሻገር እንደ ዜግነታቸው ለሀገራቸው ልማታዊ ዕድገት ከፍተኛ አስተዋፅኦ ለማበርከት የሚበቃ ሞያዊ አቅምና ሥነ ምግባር ያላቸውን ከ30ሺሕ መደበኛና ከግማሽ ሚልዮን በላይ ደጋፊ አባላት ያቀፈውን ማኅበር በማበረታታት የድርሻውን እንዲወጣ ከማድረግ ይልቅ፣ በተለያዩ ክሦችና ውንጀላዎች ለማሸማቀቅ ያለዕረፍት የሚደረገው ሐሰተኛ ቅስቀሳና የክሥ ዘመቻ አግባብነት እንደሌለውና ውጤትም እንደማያመጣ አስገንዝቧል፡፡
