በተጠርጣሪ የፕሮቴስታንታዊ ኑፋቄ ኅቡእ አራማጆች ላይ ዛሬ ምስክሮች መሰማት ይጀምራሉ
- ከሓላፊነታቸው ውጭ የሚንቀሳቀሱ ፕሮቴስታንትና ጉዳዩን ፖሊቲካዊ ያደረጉ የደኅንነት አባላት ነን ባዮች የኮሌጁን ሓላፊዎች በመጫን ተጠርጣሪዎቹን ከተጠያቂነት ለማዳን እየሠሩ ነው፤ ተጠርጣሪዎቹ በኮሌጁ አስተዳደር የተከለከለ ስብሰባ በግቢው እንዲያካሒዱ ረድተዋቸዋል፡፡
- በ‹ደኅንነት አባላቱ› የሚደገፉትና ‹‹የኢሕአዴግ ተወካዮች ነን›› የሚሉት ተጠርጣሪዎቹ፣ ለሃይማኖታቸው የቆሙትን ብዙኃኑን የኮሌጁን ደቀ መዛሙርት በስለትና በፌሮ ብረት የታገዘ ዛቻና ማስፈራራት እያደረሱባቸው ነው፤ ደቀ መዛሙርቱና የኮሌጁ አስተዳደር ጉዳዩን ለጸጥታ አካላት አስታውቀዋል፡፡
- ተጠርጣሪዎቹ÷ ‹‹ጽንፈኝነትን ታስፋፋለች›› በማለት ቤተ ክርስቲያንን የከሰሱ ሲኾን ዋና ዲኑን ጨምሮ አንዳንድ የኮሌጁን ሓላፊዎች ደግሞ ‹‹ማኅበረ ቅዱሳንና ፖሊቲከኞች ናችኹ›› በሚል ወንጀላ በምርመራው ሒደት እንዳይሳተፉና ከቦታቸው ለማስነሣት እየተንቀሳቀሱ ነው፡፡፡
- ኅቡእ የኑፋቄ አንቀሳቃሾችን በመመልመልና በማደራጀት የሚታወቁ ግለሰቦች (አሳምነው ዓብዩ፣ ደረጀ አጥናፌ እና ታምርኣየሁ አጥናፌ) ተጠርጣሪዎቹ ጥፋታቸውን እንዳያምኑ ከመገፋፋት ጀምሮ ደቀ መዛሙርቱን በጎጠኝነት በመከፋፈል አንድነታቸውን ለማሳጣት እየተንቀሳቀሱ ነው፡፡፡
