አቡጊዳ – የአዲስ አበባ አስተዳደር በአዲስ አበባ ስልፍ ማድረግ እንደማይቻል ገለጸ ፣ አንድነት ግን «አልቀበለም» ይላል !
የአንድነት ለዲሞክርሲና ለፍትህ ፓርቲ መጋቢት 28 ቀን በአዲስ አበባ ሰላማዊ ሰልፍ እንደሚያደርግ ለአዲስ አበባ አስተዳደር ቢያሳዉቅም፣ አስተዳደሩ ሰልፉ እንዲደረግ የታሰበበት ቦታ፣ ትምህርት ቤቶች ፣ ዩኒቨርሲቲና የመንግስት መስሪያ ቤቶች ያሉበት በመሆኑ እዉቅና እንደማይሰጥ የሚገልጽ፣ ከሕገ መንግስቱ የተጻረረ ደብዳቤ መላኩ ይታወቃል።
የአንድነት ፓርቲ ፣ ምንም እንኳን ቀበና ከሚገኘው ጽ/ቤታቸው እስከ ጠቅላይ ሚኒስተሩ ጽ/ቤት ድረስ ሊደረግ የታሰበው ሰልፍ በምን መስፈርትና ሚዛን ሕጉን የጣሰ ባይሆንም፣ ለአስተዳደሩ ጽ/ቤት አክብሮትን ለማሳየት፣ ሌሎች ሶስት አማራጮች ቢያቀርብ፣ አስተዳደሩ ለሶስቱም አማራጮች እዉቅና አልሰጥም ብሏል።
ከቀረቡት አማራጮ መካከል አንዱ ከቀበና ተነስቶ ፣ በአራት ኪሎ፣ ከዚያ ፒያሳ አድርጎ፣ ቸርችል ጎዳና በሚገኘው ድላችን ሃዉልት ሥር ለማድረግ ነበር። ይህ በሰኔ ወር 2005 ዓ.ም አስተዳደሩ ሌላ የተቃዋሚ ፓርቲ፣ የሰማያዊ ፓርቲ በዚያ ሰልፍ እንዲጠራ የተፈቀደበት ቦታ እንደነበረ የሚታወስ ነው። ሌላዉ አማራጭ ከቀበና ተነስቶ በመስቀል አደባባይ ማድረግ ሲሆን፣ ይሄም በርካታ ጊዜያት ኢሕአዴግ እራሱ ሰልፍ የጠራበት ቦታ እንደሆነ ይታወቃል።
አስተዳደሩ በሕግ የቀረቡ ቦታዎች ላይ ችግር ካለው ሌላ አማራጭ ማቅረብ እንዳለበት በሕግ ቢደነገግም፣ ያንን ባለማድረጉ ፣ የአንድነት ፓርቲ የጠራዉ ከሆነ ምንም አይነት ሰልፎች በአዲስ አበባ ማድረግ እንደማይቻል የወሰነ ይመስላል።
የአንድነት ፓርቲ የአስተዳደሩን ደብዳቤ እንደማይቀበለው በመግልጸ የፓርቲዉ አባላትና ደጋፊዎች የቅስቀሳ ስራዎቻቸውን እያከናወኑ ናቸው። በዚህ ሂደትም በርካቶች እየታሰሩ እንደሆነም ለማወቅ ችለናል።
