የኲሓ ዓፈና – ከአብርሃ ደስታ
ትናንት እሁድ መጋቢት 21, 2006 ዓም ዓረና ከእንደርታ ህዝብ ጋር ለመወያየት በኲሓ ከተማ ሐየሎም አዳራሽ ቀጠሮ መያዙ ይታወሳል። ለስብሰባው በስፒከር ለመቀስቀስ ሞክረን እንደተከለከልን፣ የአመራር አባሎቻችንም መታሰራቸው እንደዉጤቱም የቅስቀሳ ሂደቱ መተጓጎሉ ጠቅሼ ነበር። ሁኖም ግን የዓረና አማራጭ ሐሳብ የያዘ በራሪ ወረቀት ለኗሪዎች በማደል የተወሰነ ቅስቀሳ አድርገናል።
ከሌሎች አከባቢዎች ለየት ባለ መልኩ በእንደርታ ወረዳ በስፒከር እንዳንቀሰቅስ የተፈለገበት ምክንያት ህዝብ ስለ ዓረና ስብሰባ እንዳይሰማ ለማፈን ነው። ምክንያቱም በቅስቀሳው ወቅት የማዳበርያ ዕዳ፣ የማረትና የደደቢት ብድር እንዲሰረዝ፣ መሬት የህዝብ እንዲሆን፣ ትእምት ወደ ህዝብ ንብረትነት እንዲሸጋገር፣ የሊዝ አዋጅ እንዲሻር፣ በትግራይ ሰለማዊ ሰልፍ እንዲፈቀድ ወዘተ የሚሉ ነጥቦች ይነሱ ነበር። የህወሓት ካድሬዎችም ዕዳ መሰረዝ ምናምን እንዳናነሳ አስጠንቅቀውናል። እናም ህወሓት እነዚህ ነጥቦች ወደ ህዝብ እንዲደርሱ አልተፈለገም።
ቅዳሜ ማታ የእንደርታ (በተለይ የኲሓ) ህዝብ በዓረና ስብሰባ እንዳይሳተፍ ማስጠንቀቅያ ተሰጠው። ማስጠንቀቅያው በዓረና ስብሰባ የተሳተፈ ይታሰራል፣ ይገደላል፣ ዓረናዎች ወደ ኲሓ የመጡ ብጥብጥ ለመቀስቀስ ነው። ስለዚህ ዓመፅ ሊኖር ስለሚችል ልጆጃችሁ እንዳይገደሉ፣ እሁድ እንዳትንቀሳቀሱ … የሚል ነበር።
እሁድ ጧት ህዝብ ከቤተክርስትያን ወደ ስብሰባ አዳራሽ እንዳይገባ የማርያም ቤተክርስትያንና የሐየሎም አዳራሽ የሚከፍለውን መንገድ በፖሊስ ታጥሮ ነበር (እሁድ 21 የማርያም ዝክር ነው)። በአደራሹ አከባቢ ከእንደርታ ወረዳ (ዓይናለምና ኲሓ ጨምሮ)ና መቐለ ከተማ የተውጣጡ ከሁለት መቶ በላይ ካድሬዎች ነበሩ። ቁጥራቸው በትክክል የማይታወቅ ፖሊሶች ታርጋ በሌላቸው ፒክ አፕ መኪኖችና ሞተርሳይክሎች በከተማው እየተዘዋወሩ የአስቸኳይ ግዜ አዋጅ የታወጀ አስመስለውታል። በከተማው በዓረና ስብሰባ ለመሳተፍ የሚመጣ ሰው ለማስፈራራትና ለመመዝገብ ከተቀመጡ ካድሬዎች ዉጭ ሌላ ሰለማዊ ሰው አይንቀሳቀስም ነበር።
የህወሓት ደህንነቶች፣ የፖሊስ ደህንነት፣ የመከላከያ ደህንነት በከተማው ተሰማርተዋል። ሻዕብያ የወረረ ነው የሚመስለው (በሻዕብያ ወራር ግዜም እንዲህ የፀጥታ ሃይሎች ተሰማርተው ነበር ብዬ አላስብም)። ህዝብ ከቤቱ እንዳይወጣ ታዟል። ካድሬዎች ብቻ ይንቀሳቀሳሉ። የሚንቀሳቀስ ሰው ቤቱ ዉስጥ እንዲቀመጥ ያደርጋሉ። እነሱ የሚንቀሳቀስ ሰው ይመዘግባሉ። እኛም ህዝብን የሚመዘግቡ ካድሬዎችን እያጣራን እንመዘግባለን። አንዳንዶቹ ካድሬዎች (የወረዳው ሓላፊዎች ጨምሮ) አይዟቹ፣ መንግስት በጣም ፈርቷል ይሉናል። ቅዳሜ ያሰረን የፖሊስ አዛዥ ራሱ ህዝብ እየተከታተለ ለኛ ግን ሞራል ይሰጠን ነበር። የሚያደርገው ሁሉ ስለታዘዘ መሆኑ ነግሮናል።
ይህን ሁሉ ዓፈና ጥሰው (እንዴት አባታቸው እንደጣሱት እንጃ) የተወሰኑ የዩኒቨርስቲ ተማሪዎች፣ የሃይስኩል አስተማሪዎች፣ አርሶአደሮችና የህወሓት የደህንነት አባላት ተገኙ። የደህንነት አባላት ተልከው ነበር የገቡ። ሌሎቹ ግን በምን ድፍረት እንደገቡ ይደንቋል። ምክንያቱም ሁኔታው ሁሉ አስፈሪ ነበር። እኛ ራሳችን ገርሞናል። ማነው እንዲህ የሚያስፈራቸው ብለን ራሳችን ጠየቅን። እኛ ብንሆን ህዝባዊ ስብሰባ ነው የጠራነው እንጂ ጦርነት አልከፈትንም! ይህን ያህን ስጋት ከየት የሚመነጭ ነው?
ለሰለማዊ ታጋዮች እንዲህ ከተፈራ ትጥቅ ትግል ለመረጡ ሃይሎችስ ምን ሊደረግ ነው? ለማንኛውም ተሰብሳቢው ብዙ አልነበረም። የራሳችን አባላት ጨምረን ስብሰባው አካሂደነዋል። የተደረገው ዉይይት አመርቂ ነበር። ብዙ ጥያቄዎች ተጠይቀን መልስ ሰጥተናል። ስለዚህ በዓረና በኩል የተሳካ ስብሰባ ነበር።
ህዝብ በማስፈራራት ህወሓቶችም ተባብረውናል ማለት ይቻላል። ቅስቀሳው ስለተስተጓጎለ ስለ ዓረና ስብሰባ መረጃ ያልደረሰው ሰው ህወሓቶች ወደ ዓረና ስብሰባ እንዳትሄዱ እያሉ እንዲሰማ አድርገዋል። ህዝብ ግን በህወሓቶች ድንጋጤ ተገርሟል።
ህወሓት በምርጫ ሙሉ በሙሉ እንደሚሸነፍ አረጋግጧል። መሸነፉ እንደማይቀበልም ያውቃል። የህወሓት ሃይማኖት ስልጣን እስከሆነ ድረስ ህወሓት በሰለማዊ መንገድ ስልጣን እንደማያስረክብ የታወቀ ነው። ጠብመንጃ ደቅኖ ተመርጫለሁ ብሎ ማወጁም አይቀርም። ታድያ ለምንድነው በምርጫ የህዝብን ድምፅ መስረቅ እየቻለ አሁን ህዝብ በዓረና ስብሰባ እንዳይሳተፍ የሚከለክለው? መልሱ ቀላል ነው። በ2007 ሀገራዊ ምርጫ እንደማያሸንፍ አውቋል። ስልጣን መልቀቅ እንደማይፈልግም የተረጋገጠ ነው። ህዝብ ካልመረጠውና የህዝብን ድምፅ ካከበረ ስልጣን የለም። ህወሓት የህዝብን ድምፅ አክብሮ ስልጣን ከመልቀቅ ይልቅ ህዝብን ዓፍኖ በስልጣን መቆየት ይመርጣል። ማፈንም ይችላል። ግን አንድ የሚፈራው ነገር አለ። የህዝብ ዓመፅ።
ህወሓት የህዝብን ድምፅ እንደሚያፍን ስለሚያውቅ ህዝብ በተቃዋሚ ፓርቲ ስብሰባዎች እየተሳተፈ መማር የለበትም፣ ተቃውሞን መልመድ የለበትም፣ ፖለቲካን ማወቅ የለበትም። ምክንያቱም ህዝብ ስለ መብቱ ካወቀ ነፃነቱን መጠየቁ አይቀርም። ህዝብ ካወቀ ድምፁ ለማስከበር ጥረት ማድረጉ አይቀርም። ድምፁ ለማስከበር ጥረት ካደረገ የህወሓትን የስልጣን ህልም ይጨልማል። እናም ህወሓቶች መብቱን ለሚጠይቅ ህዝብ የሃይል እርምጃ መወሰዳቸው አይቀርም። ህዝብ ፖለቲካ ካወቀ ነፃነቱን ለማስከበር መታገሉ አይቀርም። እናም በህወሓትና ህዝብ መካከል ግጭት ይኖራል፤ ግጭቱ ወደ ዓመፅ ሊያመራ ይችላል። ከቀጠለ ህወሓት በህዝባዊ ዓመፅ ከስልጣን ሊባረር ይችላል። ይህን የሚሆነው ህዝቡ የፖለቲካ ግንዛቤው ሲያድግ ነው። ለዚህም ነው ህወሓት የትግራይን ህዝብ ፖለቲካን እንዳያውቅ የሚያፍነው። ለዚህም ነው የህዝብ በተቃዋሚ ፓርቲ ስብሰባዎች መሳተፍ የሞትን ያህል የሚያስፈራው። ለዚህም ነው ህወሓት የትግራይ ህዝብ ከዓረና መሪዎች ጋር ተገናኝቶ እንዳይወያይ መዓት ካድሬዎች እያሰለጠነ ህዝብ በስብሰባ እንዳይሳተፍ የሚከለክለው፣ የሚያስፈራራው። ይህን ሁሉ የሚደረገው ህዝብን እንዳያውቅ ለማድረግ ነው። ይህ ተግባር አደንቅሮ የመግዛት አረሜናዊ ስትራተጂ ነው።
ህወሓት አደንቁሮ ሊገዛን ይፈልጋል። ምክንያቱም እኛ ካወቅንማ ማንም አይገዛለትም። ህዝብ ካወቀ ሊያምፅ ስለሚችል ገና ሳያውቅ መታፈን አለበት ነው የተባለው። አሁንም አንድ ዕድል አለ። ህወሓት የራሱን ካድሬዎች እንዲክዱትና በነፃነት ትግሉ እንዲሳተፉ ማድረግ ይቻላል። በኲሓ ከተማ ተሰማርተው ከነበሩ ካድሬዎች መንፈስ እንደተረዳሁት ካድሬዎቹ ራሳቸው የእህል ዉኃ ነገር ሆኖባቸው እንጂ ለውጥ እንደሚፈልጉ ለመረዳት ችለናል። ስለዚህ አሁን ያለን አማራጭ ካድሬዎቹን መያዝ ነው። ካድሬዎቹ ራሳቸው በዓፈና ተግባሩ ስለሚሳተፉ የህወሓት አምባገነናዊ ባህሪ ከህዝቡ በላይ ያውቁታል። ስለዚህ በገንዘብ ካልገዟቸው በቀር እነሱን ማሳመን ቀላል ነው። ሁሉንም በገንዘብ መደለል ደግሞ አይቻልም። ስለዚህ እነሱን ለለውጥ በማነሳሳት የህወሓትን የታችኛው መዋቅር ሽባ ማድረግ ይቻላል። በዚሁ መንገድ ህወሓትን ማሸነፍ ይቻላል።
ይህን ካልተቻለ ስልጣን የመያዝ ዕድሉ የትጥቅ ትግል ለመረጡ ሃይሎች ይሆናል። ዓረና በሰለማዊ መንገድ ለመታገል ህዝብን ያነሳሳል፣ ይቀሰቅሳል፣ የለውጥን አስፈላጊነት ያስረዳል፣ ያስተምራል። ለለውጥ የተነሳሳ ህዝብ ድምፁ ሲታፈን በሰለማዊ ትግል ዉጤታማነት ተስፋ ይቆርጥና የትጥቅ ትግል ብቸኛ አማራጭ አድርጎ ይወስዳል። እናም የትጥቅ ትግልን ወደ መረጡ እንደነ ዴ.ም.ህ.ት ያሉ ድርጅቶች ይቀላቀላል። ወጣቶች በትጥቅ ትግል ከተሳተፉ ህወሓት በቀላሉ ይሸነፋል። ስለዚህ ህወሓት አንድም በሰለማዊ መንገድ አልያም ደግሞ በትጥቅ ትግል በቅርቡ መሸነፉ አይቀርም። የሰለማዊ መንገድ ሲዘጋ የትጥቅ ትግል በር ይከፈታል። ወላጆቻችን የትጥቅ ትግል መርጠው ደርግን ያባረሩበት ምክንያት የሰለማዊ ትግል በር ስለተዘጋባቸው ነው። ህወሓት የደርግን መንገድ እየተከተለ ነው። የደርግን መንገድ የሚከተል ደግሞ ደርግ የገባበትን ይገባል።
የህወሓት መፈክር: ስልጣን ወይ ሞት!
የዓረና መፈክር: ነፃነት ወይ ሞት!
የህወሓት መሳርያ: ጠብመንጃ
የዓረና መሳርያ: ሐሳብ
ህወሓት ጠብመንጃና ገንዘብ አለው። ዓረና የህዝብ ድጋፍ አለው። የጠመንጃና የገንዘብ ሃይል በህዝብ ሐይል ይሸነፋል። የህዝብ ሐይል የበላይነት አለውና። አምባገነኖች ህዝብን በጠመንጃ የሚገዙ ህዝብ እውነተኛ ሃይሉን መጠቀም እስኪችል ድረስ ብቻ ነው። ህዝብ ያሸንፋል። ስብሰባዎቻችንም ይቀጥላሉ።
It is so!!!