ይህ ትዉልድ ትክክለኛዉን መላ እስኪያገኝ ፋታ ስጡን እንላለን

ይህ ትዉልድ ትክክለኛዉን መላ እስኪያገኝ ፋታ ስጡን እንላለን!

http://www.eaglewingss.com/%e1%8b%ad%e1 … %e1%8a%9d/

መላ ያጣ የጊዜአችን ሰሞንተኛ መካሪ ያጣ የቀንም የጭለማም አስማተኛ ፡፡ ደግሞ የተካነ ቶሎ የሚላመድ የሚያላምድ፣እባብን ከርግቡ ምላስን ከሆዱ፤ ደግሞ አዋኪም ኣዋቂም የምላስ ዳንኪረኛ፡፡

አንዳንዴ አበሻ የዋሁ ያዳምና የ ሔዋን ጠላት እባብ ነው ብሎ የራሱን ምላስ ትቶ የባቢቱን ሲጠነቀቅ ይኖራል ፡፡ አሁን አሁን እኮ ተናዳፊዉ ሰዉ ነዉ፡፡ ተናዳፊዉ እባብ ቀረና ሰዉ መርዘኛ እባብ ሆኖዋል ሂዩማን ቬኖም (human venom)፡፡ እናም ታዲያ የሰሞንተኛዉ አስማተኛ ምላስ ነገረ ስራዉ ሁሉ በምላሱ መርዝ የዋሁንም የሱንም አጫፋሪም ተቃዋሚም በራሱ መርዝ በክሎ አንድ ላይ ወደ ራሱ የሆድ ከርስ አንጦርጦስ ለመክተት የተነሳ ይመስላል፡፡

የምላስና የሆድ አስማተኛ ይቅርታም ይሉኝታም የሌለዉ ብቻ የሱ ስራ በነዛ በረጂም ለሁለት በተሰነጠቁ መርዛማ ምላሶቹ አሳስቶም አሞኝቶም ፤አግባብቶም አቆላምጦም፤አባብሎም ያ ካልሆነም ደግሞ እንደግዜው መስሎም ከዚህም ከዚያም ያገኘዉን ወደዚያ መዉጪያ ወደሌለዉ የከርስ ዎይንም የሆድ አንጦርጦስ መክተት ነው የሱ ዓላማ፡፡

ዛሬ እዚህ ያለንበት የፈረንጆቹ ማህበረሰብ ዉስጥ በተመስጦ እሚወያዩት ስለ ምህዋር ጠፈር ብላክ ሆል ስለሚሉት የስበትን ሚስጥር ሰለማወቅ ነዉ ሚስጥሩን ሳይንሳቸዉ ገና ትክክለኛዉን መልስ ባያገኝም፡፡ ዛሬ ዛሬ ግን የዕኛን የፖለቲካ አዙሪትና ስበት ብንፈልገዉ ደግሞ የሰዉ ሆድ ዉስጥ ሆኖዋል እምናገኘዉ ፡፡ሆድም ብላክ ሆል (black hole) ሆነ ላበሻ ፡፡ትዉልዱ ለፖለቲካ ለዉጥና ለመልካም አስተዳደር ለፋትሕና ለዲሞክራሲያዊ ለዉጥ ይታገላል ፣ነገር ግን ደግሞ ትግሉ በሆድ ዎይንም በከርስ ስበት ምክንያት ተኮላሽቶ ይኸዉ የዚህ ትዉልድ ስቃይና መከራ እንደ ዓዲስ እየትራዘመ ይገኛል፡፡

ባሁኑ ዎቅት ኢትዮጽያና ኢትዮጵያዉያንን ስላለባቸዉ የማህበራዊ የምጣኔ ሃብታዊ ፖለቲካዊ ችግሮች ተስታከዉ በሚካሄዱ ባስመሳዮችና ባላዋቂዎች ፖለቲከኛ ነን ባዮች ምክንያት የትግሉ አቅጣጫ ላይ ደንቃራ ሆነዉ ይታያሉ፡፡እነዚህ መርዛማ አስመሳዮች በዘመናዊ አዳራሾች በዘመናዊ የመገናኛ መረቦች የመላዕክትም የፃዲቅም የሴይጣንም ፤የታዋቂ ሰዉ ስምም የጅግናም ሰዉ ስምና ክብር ፤በምላሳቸዉና በባዶ እራሳቸዉም ላይ እየጫኑ ፡ቡድን እያበጁ በመዋገን በፖለቲካ ዕምነት፥ በፖለቲካ አመለካከት ዎይንም ደግሞ በምክንያታዊነት ሳይሆን፡ እንዳዉ ብቻ ለጥቅም አሊያም በመንደርተኝንትና በጥላቻ ባዶ ኢትዮጵያዊኛ ከበሮ ዕየተደለቀ እርስ በርስ ሲቆለማመጡ ሲካካቡ እና የኮሚቴ ሹምና የቴሌቭዥን የክብር ዕንግዳ እየተደራረጉ ሲካካቡ ከርመዉ ዛሬ ደግሞ አንዱ አስማተኛ ድንገት ከጉያቸዉ አፈትልኮ ወጥቶ የጥንት የጠዋቱን ከነጉዲት በፊት ያመልክ የነበረዉን ዋናዉን ሴይጣን መልሶ ተቀላቅሎ ዛሬ ሌላ ዙር ነጋሪት በተቃዋሚዉ ፓርቲና ማህበረሰቡ ላይ ዕየተጎሸመ ያለኛ በቀር የፖለቲካ መንገድም እዉነትም ሐርነትም የለም እየተባልን ነዉ፡፡

ዛሬ በሁለቱም ጎራ የሚታየዉ የባዶ ዓርበኝነት ድራማ የብዙሃኑን ህዝብ የለዉጥ ጥያቄና የዚህን ወጣት ትዉልድ ትግል እያጓተተና እየጎዳዉ ይታያል፡፡ለዚህም የሚታዩት ምክንያቶች ያላዋቂ ሳሚ መብዛትና ፥ያመራር ችግር፤ተጠያቂነት የሌለዉ የባለሞያና የፖለቲካ አናርኪዝም (anarchism) ዋናዎቹ ችግሮች ቢሆኑም እነዚህን ችግሮች ተንተርሰዉ ዘመኑ ባፈራዉ የሜድያ መረቦች የመስኮት (window )አስመሳይ ፖለቲከኞች ማን እንደኛ ለ ኢትዮጵያ የሚሉ ስግብግቦችና ራስ አድናቂ (narcissist) በ ኢትዮጵያ ህዝብ የለዉጥ ትግል ላይና በዚህ ዓዲስ ወጣት ትዉልድ የለዉጥና የዲሞክራሲያዊ ጥያቄ ላይ ትልቅ የተህዋስ ወረርሽኝ (virus epidemic) ሆነዉበት ይገኛል፡፡

ከድሮ ጀምሮ አንድ የለመድነዉና ያደግንበት አጉል ባህል አለ፡፡ ወቅታዊ ያልሆነ ዘመንተኝነት አብሮን አድጎ ይኸዉ ይኼን ኮተታችንን እዚህም እሰዉ አገር አምጥተን እርስ በርስ መደናቆር ይዘናል፡፡ ባንድ ዎቅት ንዋይ ደበበ የ ጥቅምት አበባ ነሽ አሉ ብሎ ዘፍኖ ጠዋትም ማታም በበጋም በክረምትም ትንሹም ትልቁም የዘፍነዉ ነበረ ከዛም ደግሞ ሐይልዬ ታደሰ የተባለ ድምጻዊ ይሞታል ዎይ ታዲያ ( Link )እምትለዉን ዘፈን አዉጥቶ በማህበረሰቡ ዉስጥ በጣም ከመደጋገሙ የተነሳ በግዜዉ የነበረዉን ማህበረሰባዊ ነዉር ማህበረሰባዊ የሞራል ዝቅጠት ራሱ ኪነትና ስነጥበብ አብረዉ ዓብረዉ ቡሄራዊ ነዉራችንን አንድ ላይ ስንዘፍነዉና ዳንኪራዉም ሲመታ ነበረ፡፡ ታድያ በግዜው የነበረዉ ማህበረሰባዊ ነዉር ከመደጋገም (cliches) ከመሆን አልፎ ግቦ ስጭም ግቦ ተቀባይም ራሱ ተጎጂዉም ማህበረሰብ ነዉሩን አብሮ ይዘፍነዉ ነበር፡፡ ዛሬም ያለዉ የሆድ ዎይንም የከርስ ነዉራችንን በትንሿ መስኮት (window) ዳንኪራዉ እየተመታልን ጠዋትና ማታ የግዜዉን ተደጋጋሚ ቃላቶች መስማት ግድ ይሏል፡፡የዘንድሮ የፓልቶክ አድማጭ እና እራሱ ፓልቶክ (paltalk) ክፍሉም እዛዉ አገራችን እንዳሉት የነ መላዉያኑ ሰፈር የመርካቶ ሙዚቃ ቤቶች ሲመስል ሰዉም ደግሞ ሙዚቃ ቤቶቹን ከቦ እሚዉለዉን መስሎኣል ፡፡

እዚህ በዳያስፖራዉ የዕለት ተዕለት ኑሮ ዉስጥ ለኑሮ ማደላደያና ለእንቶ ፈንቶ የፖለቲካ ፍጆታ መገልገያ ተደርገዉ የተያዙ የዘመኑ ተደጋጋሚ ቁልፍ ቃላቶች (cliches) ሆነዉ የቀሩ አሉ፤ለምሳሌ ብንወስድ፣ ኢትዮጵያዊ ዓርበኛ፤ ዎያኔ ሻዕቢያ ፤ግንቦት ሰባት አሸባሪ አዋኪ፤ዎይንም (terrorist) ባንዳ ሆዳም፤ ቅጥረኛ ሰላይ፤ እነዚህ ክሊሸስ (cliches) በገዢዉ መደብም ሆነ በተቃዋሚዉ ጎራ ሲያስፈልጋቸዉ ማዕረግ መስጫ ካስፈለገም ማዉገዢያና ማጥቂያም ማሰሪያም ሆነዉ ያገለግላሉ፡፡ማናቸዉም ነፃ የሆኑ አስተያየቶችና አመለካከቶች በነዚህ የዘመኑ የዳያስፖራ ፖለቲከኞች ዘንድ የስም ተቀፅላ ዎይንም ታፔላ እየተለጠፈላቸዉ በቀጥታ የነሱን የፖለቲካ ገበያና ህልዉና እንዲያስጠብቁ አርገዉ የጠቀሙባቸዋል፡፡

ዛሬ እየሰማን ያለነዉ የፖለቲካ ዓመለካከት ልዩነትን ዎይንም የፖለቲካ ዕምነትን ሳይሆን ይልቁንስ የግለሰቦችን የሆድ እና የዓመል ዥዋዥዌ እንደትልቅ የፖለቲካ አጀንዳ በየመገናኛ መረቡ ላይ ሲያራግቡት ነዉ፡፡ ዛሬ ይህ ትዉልድ እነሱ ባጨማለቁትና ባመሳቀሉት አሁን ድረስ እየተሰቃየበት ነዉ ፡፡ማህበረሰቦች በግለሰቦች ምላስና ሆድ ዋጋ እየወጣላቸዉ ማንም ባተሌ እየተነሳ የፈለገዉን ስም በራሱ ላይ እየጫነ በስደት ያለዉን ነፃ ማህበረሰብ እያመሱት ይገኛሉ፡፡እሚገርመን ደግሞ ከመላዉያን ሰሞንተኛ አስማተኛ ሰሞኑን የወሰደዉ በቀል አይሉት ክህደት፣ ቅጥፈት አይሉት ስሕተት፣ ርካሽ የፖለቲካ ኮተት፤ተዓማኒነት ዎይንም ደሞ ተቀባይነት እንዲያገኝና የነፃዉን ህብረተሰብ ድጋፍና ቀልብ ለመሳብ የብዙሃኑን የልብ ትርታ አፈንፍኜ አግኝቻለዉ በማለት ባዶ ዲስኩር ሲያረግ ከርሞአል ፡፡

ዛሬ ባብዛኛዉ ኢትዮጵያዊ በዝምታ የሁለቱን የውሸት ዓርበኞች ዳር ሁኖ የቆመበትን ምክንያቶች ይኸዉ ተዓምረኛ አስማተኛ ለከርሱ ፍጆታ ሲል እንደፖለቲካ አቝዋምና በዝምታ ላለዉ ህብረተሰብ ደርሶ አሳቢ ሆኖ ይህንኑ ማህበረሰብ እንደ አንድ ዕምቅ የተፈጥሮ ሃብት የፖለቲካ ገፀ በረከት አድርጎ እዛዉ ላለዉ የገዢ መደብ ለማቅረብ ባዶ የዓርበኝነት ዕምቢልታ እየተነፋ ይገኛል።ይብላኝልኝ ግን በደመቀበት ሲደምቁ ለነበሩ አዋቂ ነን ባዮች ፣በዘር በሃይማኖት ፣በእከክልኝ ልከክልህ ፣ በሰዉ ያንገት ስፋት ፣በከርሱ ስፋት ፣ወርድና ቁመት ማዕረግ እየሰጡ ሆይ ሆይ ሲሉ ለነበሩ ይብላኝልኝ።

በነዚህ አስመሳዮች ከርስ እዚህም እዚያም አሁንም ድረስ እንደትንሿ የጠረጴዛ ኳስ ሲመቱና እየተመቱ ላሉ ፣እነሆ ከያለንበት እንዲህ እንላለን፡፡ ዛሬ የምናያቸዉ የመድረክ ተዋንያን በትንሽዋ መስኮት (window) እየተወኑ ያሉት የፖለቲካ ተዉኔት በራሳቸዉ ድርሰት እራሳቸዉንና ቡችሎቻቸዉን እየተውኑ መሆኑን እንዲያዉቁት ። መላ ያጣዉ ይህ ትዉልድ ግን ትክክለኛዉን መላ እስኪያገኝ ፋታ ስጡን እንላለን።