አቡጊዳ – ሰባቱ የጣይቱ ሴቶች እና ሶስቱ ወንዶች ከ11 ቀናት እሥር በኋላ ተፈቱ
ሰባቱ የጣይቱ ሴቶች እና ሶስቱ ወንዶች ከአራ አንድ ቀናት በዋስትና መፈታታቸውን ዳዊት ሰለሞን ከአዲስ አበባ ዘገበ።

«በመደበኛ ፍርድ ቤት ክሴን እንዳቀርብ ይፈቀድልኝ በማለት ቀበና ለሚገኘው የመጀመሪያ ደረጃ ፍርድ ቤት ትናንት ጥያቄ አቅርቦ የነበረው ፖሊስ ዛሬ ማለዳ አስሩን ተጠርጣሪዎች ቀበና የመጀመሪያ ደረጃ ፍርድ ቤት አቅርቧል፡፡» ሲል የዘገበው ጋዜጠኛ ዳዊት ሰለሞን «በወጣቶቹ ላይ ክስ ለመመስረት የሚበቃ ወንጀል አለመገኘቱን በመጥቀስ ታሳሪዎቹ እንዲለቀቁ አቃቤ ህግ ለፖሊስ ምክር መስጠቱን የሰሙት ጠበቃ አቶ አለሙ ጎቤቦ ደምበኞቻቸው ያለ ዋስትና እንዲለቀቁና መዝገቡ እንዲዘጋ ቢከራከሩም ፖሊስ ክሴን እመሰርታለሁ በማለቱ ፍርድ ቤቱ እያንዳንዳቸው 1300 ብር እንዲሁም የአዲስ አበባ ቀበሌ መታወቂያ ያለው ሰው በማቅረብ በዋስ እንዲፈቱ ወስኗል» ሲል በፌስቡክ ዘግቧል።
የጣይቱ ሰባቱ ሴቶች ተብለው የሚታወቁት ሰባቱ ኢትዮጵያዉያን እና ሴቶቹ በፖሊስ ሲያዙ ለምን ብለው የጠየቁት ሶስት ወንዶች፣ ከየካቲት 30 ጀምሮ በአጠቃላይ ለአሥራ አንድ ቀናት የታሰሩ ሲሆን በእሥር ቤት በነበሩም ጊዜ ከፍተኛ ዛቻና ማስፈራሪያ እንደደረሰባቸው ይናገራሉ።