አንድነት- አንድነት ፓርቲ ክስ የመሰረተባቸው የመንግስት ተቋማት መቃወሚያቸውን አሰሙ – በአሸናፊ ደምሴ
በዴሞክራሲያዊ መንገድ ሰላማዊ ሰልፍ የማድረግ ህገመንግስታዊ መብቴን ጥሰውብኛል ሲል አንድነት ለዴሞክራሲና ለፍትህ ፓርቲ (አንድነት) ክስ የመሰረተባቸው ሶስት የመንግስት ተቋማት በትናንትናው ዕለት በፌዴራሉ ከፍተኛ ፍርድ ቤት 8ኛ ፍትሃብሔር ችሎት ቀርበው መቃወሚያቸውን አሰሙ። ፓርቲው ክስ የመሰረተባቸው የአዲስ አበባ ከንቲማ ጽህፈት ቤት ፣ የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደርና የአዲስ አበባ ፖለስ ኮሚሽን ሲሆኑ በጠበቆቻቸው በኩል የክስ መቃወሚያቸውን በፍ/ቤቱ አቅርበዋል።
የአንድነት ፓርቲ በጠበቃው በኩል የመሰረታቸው ክሶች የአዲስ አበባ ከተማ ከንቲባ ጽ/ቤት ተሻሽሎ በተሰጠው ቻርተርና የፖሊስን የእለት ተእለት ስራ በአግባቡ አልተከታተለም። ሁለተኛ ፖሊስ ፓርቲው በህግ የተፈቀደለትን ቅስቀሳ በሚያደርግበት ወቅት እገታ ተፈፅሞበታል፤ በራሪ ወረቀቶችን ተቀምቶ ቅስቀሳውን አስተጓጉለዋል የሚል ሲሆን ማዘጋጃ ቤቱን በተመለከተ በህግ መፈቀድ ያለበትን ቦታ ትቶ በጦር ካምፕ አካባቢ 50 ሜትር እርቀት ውስጥ ሰላማዊ ሰልፉ ማድረግ ክልክል መሆኑን እያወቀ ከህግ የተጣረሰ ፍቃድ ሰጥቷል የሚል ቅሬታ ማቅረባቸውን በክስ ዝርዝራቸው አስረድተዋል።
ፓርቲው ክስ ከመሰረተባቸው የመንግስት ተቋማት ጠበቆች በኩል ክሱን ለመቃወም የቀረበው ሀሳብ ፍርድ ቤቱ ይህን ጉዳይ የመመልከት ስልጣን የለውም የሚል ሲሆን፤ ጉዳዩ መታየት ያለበት በማዘጋጃ ፍርድ ቤት በኩል ነው የሚል ሀሳብ ቢቀርብም ፓርቲው በበኩሉ ያቀረብኩት ጉዳይ ህገመንግስታዊ እንጂ የከተማና የቦታ ጉዳይ አይደለም ሲል የክስ መቃወሚያው ውድቅ እንዲደረግለት ጠይቋል።
የአዲስ አበባ ፖሊስ በበኩሉ የፌዴራል ፖሊስን በተመለከተም መግባት አለበት ይህን ጉዳይ የሚከታተለው ተቋም እርሱ ነው የሚል የክስ መቃወሚያ ለችሎቱ አቅርቧል። ከዚህም ሌላ የቀረበው መቃወሚያ ፓርቲው ከ500ሺህ በላይ ህዝብ ይመጣል በማለቱ የጃን ሜዳ እንደፈቀዱለት አስረድተዋል።
አንድነት በአባላቶቼ ላይ የደረሰው ጉዳት በማስረጃ የተደገፈ ነው ያለ ሲሆን ከ100 በላይ የሰው ምስክሮችን ማቅረብ እንደሚችልም አስቆጥሯል። ከዚህ በተጨማሪ በጋዜጣ የወጣው ዘገባ እና የፓርቲው አመራሮች እስከበላይ ባለስልጣናት ድረስ የተፃፃፏቸውን ደብዳቤዎች በሰነድ ማስረጃነት ለፍርድ ቤት አቅርቧል።
የግራቀኙን የክርክር ሂደት የተከታተለው የፌዴራሉ ከፍተኛ ፍርድ ቤት 8ኛ ፍትሐብሔር ችሎትም በጉዳዩ ላይ ብይን ለመስጠት ለሚያዚያ 7 ቀን 2006 ዓ.ም ተለዋጭ ቀጠሮ ሰጥቷል።