‹‹የ’66ቱ አብዮት የፈነዳው ስርዓቱ ጠንቃቃ ስላልነበረ ነው›› ‹‹የኑሮ ውድነቱ እሳት እንደነደደ ይቆጠራል›› ቆንጅት ብርሃኑ የኢህአፓ ታጋይና የምርኮኛ መጽሐፍ ደራሲ፣

ለኢትዮጵያ የዛሬ አርባ አመት ነው አዲስ ህይወትና ምዕራፍ የተከሰተው፡፡ ሆኖም 1966 ዓ.ም የነገሮች ሁሉ መነሻ አልነበረም፡፡ በዛች ወቅትና አመት በተከሰተው ሁኔታ ብቻ አይደለም ወጣቱ ህይወቱን ለመስጠት የተሰናዳው፡፡ ነገር ግን የአብዮት መፈንዳት የእያንዳንዳችን የውስጥ ስሜት ስለነካ ይመስለኛል፡፡ ለዚህም ምሳሌ የማደርገው ራሴን ነው፡፡ ማህበረሰብ እንዲለወጥ የአንድ ጊዜ የጋራ እርምጃ ሳይሆን የተጠራቀመ ነገር ያስፈልገዋል፡፡ በወቅቱ ወደ 11ኛ ክፍል አልፌ ነበር፡፡ እኔ እኖር የነበረው ከአዲስ አበባ ውጭ ፍቼ ከተማ ነው፡፡ ይህም ለገጠሩ ህዝብ ቅርብ እንድሆን አድርጎኛል፡፡ ቤተሰቦቼ የሀይማኖት ሰዎች ናቸው፡፡ አባቴ ቄስ ነው፡፡ የአባቴ ወንድሞች፣ የአባቴ አባት፣ የእናቴ ወንድሞች፣ የእናቴ አባት…ብዙዎቹ ቄስና የሀይማኖት ሰዎችና ቤተሰብ ነበሩ፡፡ እንደሚታወቀው በነበረው ስርዓት የቤተ ክርስትያን ሰዎችና የመንግስት አስተዳደር ቅርብ ነበር፡፡ በመሆኑም እኔም ለሀይማኖት ቅርበት ነበረኝ፡፡ ቅረበቴ ግን ለእኔ የሰጠኝ ከስርዓቱ ጋር መሳሳብና መዋደድ አልነበረም፡፡ እኔ የቄስ ልጅ እንደመሆኔ የሀብታም ልጅ አልነበርኩም፡፡ (መቼም ዛሬ ካልሆነ ቄስ ሀብታም ሆኖ አያውቅም፡፡)
ለቤተ-ክርስቲያን ቅርብ ስትሆኑ ለጪሰኛውና ለመሬት ቅርብ ትሆናላችሁ፡፡ ምክንያቱም ቤተ ክርስቲያን ‹‹እኩል ከእርስት›› የሚባል ነገር ስለነበራት ነው፡፡ እኔ ቤት ባይሆንም የአባቴ ቤተሰቦች ቤት ይህን ስርዓት በግልጽ ማየት ችያለሁ፡፡ ገና 6ኛ እና 7ኛ ክፍል ሆኜ ጭሰኞች ከገጠር እህል ሲያመጡ፣ ግብር ሲበላ፣ ድግስ ሲደገስ፣ ሲስተናገድ (እንዴት ህዝብ በየ ደረጃው ይስተናገድ እንደነበር) በቅርብ ማየት ችያለሁ፡፡ በነገራችን ላይ ገና 6 እና 7ኛ ክፍል ሆኜ ይመስለኛል ፍቅር እስከ መቃብር የታተመው፡፡ ፍቅር እስከ መቃብርን አነበብኩ፡፡ ፍቅር እስከ መቃብር ላይ የፊውዳልና የጭሰኛውን ግንኙነት ሳነብም በስርዓቱ የተማረርኩት እኔ ብቻ አለመሆኔን አመንኩ፡፡ ፍቅር እስከ መቃብር ለልቤ ጥያቄ መልስ ሰጠኝ፡፡ ከእኔው ውጭ ሌሎች ሰዎች እንደሚከፋቸው ማየት ችያለሁ፡፡ ከዛ በፊት ግን የጭሰኞችን ግንኙነት አይቻለሁ፡፡ አንድ ሰው ሁለት አጥር ይኖረዋል፡፡ ጭሰኞች የውስጠኛውን አጥር ከመግባታቸው በፊት ማደግደግና፣ አጋሰሶቻቸውን ማራገፍ አለባቸው፣ እህሉን ተሸክመው ለመግባት፡፡
6ኛ ክፍል ሆኜ ትምህርት ቤት ስሄድ ትንሽ ልጅ የሚመራቸው አንድ መንገድ ዳር ላይ የሚለምኑ ሽማግሌ ነበሩ፡፡ እናም በዛች ትንሽ ጭንቅላቴ ብዙ አስብ ነበር፡፡ ጭሰኞቹ ሲያረጁ እንደዚህ ሰውዬ እንደሚሆኑ አስብ ነበር፡፡ ምክንያቱም ያፈሩትን እየሰጡ ነው፤ ሲያረጁ ደግሞ ከመሬታቸው ይነሳሉ፡፡ እናም ግን ለምን? ግን ለምን? ግን ለምን? የሚል ጥያቄ በብዛት በአዕምሮዬ ይመላለስ ነበር፡፡ ፍቅር እስከ መቃብርን እንዳገኝና እንዳነብ ያደረገኝ ወንድሜ ስለ ችግሮቹ እንድጽፍ ያደርገኝ ነበር፡፡ የተሰማኝን መጻፍ ጀመርኩ፡፡
እስከ 9ኛ ክፍል እስክደርስ ድረስ ሶስትና አራት ባለ 50 ገጽ ደብተር ጻፍኩ፡፡ በ1966 የጻፍኳቸውን ደብተሮች ብቻ ይዤ አዲስ አበባ በመምጣት ንግድ ስራ ትምህርት ቤት ገባሁ፡፡ በ1967 ዘመቻ መሄድ ነበረብኝ፡፡ ዘመቻ እንደሄድኩ ለመጀመሪያ ጊዜ ያነበብኩት የማኦን ስለ ጭሰኞች የሚያወራ ‹‹The peasant uprising›› የሚለውን መጽሃፍ ነበር፡፡ ውስጤ ያለውን የሚነካ ነገር ተፈጠረ፡፡ ይህ ነገር (አብዮት) ያስፈልገናል ብዬ አመንኩ፡፡ የቄስ ልጅ፣ አክራሪ ኦርቶዶክስ ነበርኩ፡፡ ሆኖም በዘመቻው ወቅት በመጾምና ባለመጾም ተፈትኛለሁ፡፡ ወጣት ስትሆኑ ደግሞ አዲስ ነገር መቀበልና መሆን አለባችሁ፡፡ በሶሻሊዝም መጾም የለም፣ እንዲያውም በሶሻሊዝም ስም ማረድ (መባረክ) አለብን ሁሉ ይባል ነበር፡፡ በዚህ ጉዳይ ለ6 ወር ያህል ተፈትኛለሁ፡፡ በኋላ ተሸነፍኩና ተቀላቀልኩ፡፡ ስለ ኮምኒዝም የሰማሁት 7ኛ ክፍል ሆኜ ነው፡፡ ስለቻይና ሶቬት አብዮት ነው፡፡ ኮሚኒስት ከሆንን መኪና የለም፣ ቤት የለም፣ ሱፐር ማርኬት ሄዶ መግዛት የለም፣ በካርድ ብቻ መግዛት ነው የሚል ነው፡፡ ይህ ለእኔ በውስጤ የነበር ነው፡፡ የማኦ መጽኃፍና ሌሎች መጽሃፎች ሲጨመሩ ሶሻሊዝም ለኢትዮጵያ እንደሚያስፈልጋት አመንኩ፡፡ ይህ መነሻ ሆኖ ዘመቻ ጣቢያ እያለሁ ዴሞክራሲያን ሳነባት ደግሞ ይበልጡን አመንኩበት፡፡ እንዲያውም ዴሞክራሲያን የሚጽፉት ሰዎች መላዕክት ይመስሉኝ ነበር፡፡ እስከዚያ ድረስ የሚመስጥ ጽሁፍ ነበር፡፡ ያ መመሰጥ ውስጤ ከነበረው መመሳሰል ጋር በመመሳሰሉ ነው ኢህአፓ ውስጥ ያስገባኝ፡፡ ማንም ቀስቅሶኝ አይደለም፡፡ እኩል ተቀስቅሰን እኩል መሄድ አልቻልንም፡፡ እኩል እንደ እኔ ቢቀሰቀሱም ከዘመቻ ተመልሰው ትምህርታቸውን የቀጠሉና ሌላ አቅጣጫን የመረጡ ነበሩ፡፡ ስለዚህ ውስጤ ያለውን ነገር ስለነካ ነው ገብቼ የቀረሁት፡፡ ባላምንበት ኖሮ ከተቀሰቀስኩ በኋላ ቤት ስመለስ በተውኩት ነበር፡፡
1966 አብዮት በእኔ ምሳሉ ሳየው ድንገተኛ አልነበረም፡፡ የካቲት ወር በአንድ ሰልፍ ዩኒፎርም ለብሰን መንገድ ላይ ስንወጣ ‹‹እንኳን ደስ አላችሁ!››፣ ‹‹እንኳን ጀግና ሆናችሁ!›› እንባል ነበር፡፡ ነባራዊ ሁኔታው፣ የኑሮ ውድነት (ከዛሬው ጋር የሚወዳደር አልነበረም) አስተዋጽኦ አድርጓል፡፡ አባቴ በርካታ ቤተሰብን በ80 ብር ማስተዳደር ይችል ነበር፡፡ የዛን ጊዜና የአሁኑን ማመሳሰል አይቻልም፡፡ የተወደደው ቅቤ ሳንቲም ጨምሮ 3 ብር፣ ዘይት ሁለት ብር፣ ጤፍ 50 ብር ይሸጥ ነበር፡፡ የ1966ቱ የኑሮ ውድነት ከዛ በፊት ከነበረው ርካሽ ኑሮ ጋር የሚነጻጸር ነው፡፡ ከድሮው ጋር ሲነጻጸር የኑሮ ውድነቱ እሳት እንደነደደ ይቆጠራል፡፡ ያ የምርት ግንኙነት፣ ማህበራዊና ስነ ልቦናዊ ችግር ጋር ሲደማመር እንጅ ወታደሩና ተማሪው ስለተሰለፈ ብቻ የመጣ አይደለም፡፡ ያን ሁኔታ ወደ አንድ ሁኔታ (አብዮት) ለመቀየር፣ የታክሲ ሾፌሮች፣ የወታደሩ የደሞዝ ጭማሬ፣ የሴክተር ሪቪው ተጨምሮበት 1966ን የኢትዮጵያ አንድ ምዕራፍ አደረገው፡፡ ስርዓቱ ጠንቃቃ ባለመሆኑና ብዙ ስላልተሰራ ነው አብዮቱ የፈነዳው፡፡ አሁን እኮ እየተመለስን ያለነው ወደ ካፒታሊዝም ነው፡፡ ስርዓቱ ጠንቃቃ ቢሆን ያለምንም ውጣ ውረድ የተሳካ ስርዓት በገነባን ነበር፡፡ የከፈልነው መስዕዋትነት የማይገባ ነበር፡፡
በዘመቻው ወቅት ከአዲስ አበባ ወጥተን ገጠር በመግባታችን ለማንበብም ሆነ ለህዝብ ቅርብ መሆን ችለናል፡፡ ውስጣችን የነበረውን እምነት የቀየረው ይህ ነው፡፡ ወጣቱም አንዴ ከተነሳ መመለስ ያቃተው ለዚህ ነው፡፡ ኢህአፓ ውስጥ ስገባ ያጋጠመኝ ነገር ደግሞ በፊት ከማስበው የተለየና እምነቴን ያሳደገልኝ ነበር፡፡ እነዚህ ሰዎች እንደ ሰው አይደሉም የሚለውን እምነቴን አጠናክሮልኛል፡፡ በወጣት ማህበራት እንገናኝ ነበር፡፡ የፓርቲው ሳይሆን ኢህአወሊ (የወጣት ማህበሩ) አባል ነበር፡፡ ኢህአወሊ ራሱን የቻለ ፓርቲ ነበር ማለት ይቻላል፡፡ ከወጣት ሊጉ ከገባሁ በኋላ ሀይለኛ ስብዕና አግኝቻሁ፡፡ ከዛ በፊት የነበረኝ አላማ ዩኒቨርሲቲ መግባት የዩኒቨርሲቲ መምህር፣ ፕሮፌሰር ሆኜ የምሁር ህይወት መኖር ነበር፡፡ ያ ሁሉ ህልሜ ቀርቶ ከዘመቻ ስንመለስ ‹‹ከትግል በኋላ ትምህርት›› የሚለው የወጣት ሊጉን መፈክር ይዘን ትግል ገባን፡፡ ትግሉ እየከረረ መጣ፡፡ ደም በደም ሆነ፡፡ የመጀመሪያው ደም በሚኒስትሮቹ ጀመረ፡፡ በእነሱ የተጀመረው ግድያ ወደ ሌላ ግድያ ተቀየረ፡፡
ኢህአፓ ውስጥ ከገባን በኋላ የሰዎቹ መልካምነት፣ እድገት በህብረት ሄጄ የዩኒቨርሲቲ ካየሁ በኋላ ባገኘኋቸው ተማሪዎች ስብዕና በማየቴ ከውስጤ ነው ያመንኩት፡፡ ምክንያቱም ኢህአፓ የውስጣችን ስሜት ነው የነካው፡፡ ፓርቲ ውስጥ ያየሁት ደግሞ ይበልጡን ልቤን የሚሞላ ነበር፡፡፡ ለራሳችን መኖርና ስብዕናችንን መጠበቅ እንዳለብን፣ ነገር ግን ቅድሚያ ለህዝብ እድንኖር በተግባር አስተምረውናል፡፡ ኢህአወሊ እያለሁ አንድ ሰልፍ ነበር፡፡ ለማምለጥ ስንሮጥ አንድ ሰፈር ውስጥ የተደረመሰ ሽንት ቤትና ውጭ ደግሞ የሚመጥ የቆመ መኪና ላይ ደረስን፡፡ በዚህም ምክንያት አስም ተቀሰቀሰብኝ፡፡ ትንሽ እንደሄድን መራመድ አቃተኝና ተቀመጥኩ፡፡ ሌላው እየሮጠ አንድ በእድሜ የሚበልጠኝ ሰው ቆሞ ይጠብቀኛል፡፡ ‹‹ለምንድን ነው የቆምከው? አምልጥ!›› ስለው ‹‹ለምን ጥየሽ እሮጣለሁ? ይልቁን ጥቂት እርጅኝና ጥግ አስይዤሽ እሄዳለሁ›› አለኝ፡፡ ጥይት እየተተኮሰ እኔን ይጠብቃል፡፡ ይህ ድርጅቱ ለእኔ እንደሚቆም ማወቅ ስላስቻለኝ ብርታት ሰጥቶኛል፡፡ አስሙ እየባሰብኝ ሲሄድ ባልጠበኩት ሁኔታ የአስም መድሃኒት ተላከልኝ፡፡ ይህኛውም ሌላ ጉልበት ነበር፡፡
ሌላ ጊዜ ደግሞ አዲስ አበባ ላይ መኖር ከባድ ሆነ፡፡ ወደ አሲምባ ለመሄድም አይቻልም ነበር፡፡ ናዝሬት ላይ አንድ ቤዝ ሊቋቋም ነበር፡፡ ያኔ ከእኛ ሰፈር ሶስት ወጣቶች ወደ ቤዙ ሊሄዱ ነበር፡፡ ግን መድረስ ባለመቻላቸው ተመልሰው መጡ፡፡ ከተመለሱ በኋላ ታሰሩ፡፡ ልጆቹ በመታሰራቸው ለእኔ ሂስ መጣልኝ፡፡ ቁጭ ብየ አነበብኩት፡፡ ሂሱም ልጆቹ በቁጥጥር ስር የዋሉት በሚተዋወቁት ሰዎች መካከል ሊሆን እንደሚችልና፤ መረጃ ከእኔ በኩል አፈትልኮ እንደሆነ የሚያሳይ ጠንከር ያለ ሂስ ነው፡፡ እኔ የት እንደሄዱ ስላላወቅሁ በጣም አዘንኩ፡፡ መልስ መጻፍ እንዳለብኝ አሰብኩ፡፡ እኔም ለእንዲህ አይነት ድርጅት ከሆነ አባል የሆንኩት መሳሳቴንና ከድርጅቱ እንደምወጣ ጻፍኩ፡፡ በሳምንቱ ግን የሚገርም መልስ ጻፉልኝ፡፡ መልሱ ለእኔ ለትንሹዋ ልጅ የሚሰጥ አልነበረም፡፡ ‹‹ተንበርክከን ይቅርታ እንጠይቃለን›› የሚል ከጸኃፊው ማብራሪያ ጋር ተዳምሮ ይቅርታ ተጻፈልኝ፡፡ ‹‹እንደ አንቺ ያለ ጠንካራ አባል ስላለን እንኮራለን›› አሉኝ፡፡ ይህም ሌላ ጉልበት ነበር፡፡ ይህን የጻፉልኝ ለአባላት ትልቅ ክብር እንዳላቸው መሆኑን አምኛለሁ፡፡ ሂስና ግለሂስን የተማርኩት ያኔ ነው፡፡
ብዙዎቹ ጓደኞቻችን ሞቱ፣ የተረፍነው ዳንን፣ ከእስር ተፈታን፣ መኖር የግድ ነውና መኖር ጀመርን፡፡ ያ ውስጤ የነበረን አላማ የነካውን ኢህአፓና ኢህአወሊ ውለታ ተሸክሜ መኖር አቃተኝ፡፡ በእርግጥ 20ና 30 አመት አልፎታል፡፡ ያ ትውልድ የሞተው፣ እኔ ያን ሁሉ የሆንኩት ኢትዮጵያን ለማጥፋት ባይሆንም በርካቶች ግን መኖር እንዳንወድ አድርገው ይወቅሱናል፡፡ በእርግጥ ስለማያውቁን ነው የሚል ጥያቄ ይመላለስብኝ ነበር፡፡ አንድ ወቅት ይህን መልስ እንዳገኝ አደረገኝ፡፡ አንድ ዓለም አቀፍ ድርጅት በምሰራበት ወቅት አንድ ቡድን ይዤ ለልምድ ልውውጥ ወደ ኬንያ ሄድኩ፡፡ በእረፍት ሰዓት ሰብሰብ ብለን ስናወራ ስለ ‹‹ያ ትውልድ›› መወራት ጀመረ፡፡ አጥፍተውት አለፉ እያሉ ይወቅሱታል፡፡ የአንድን ነገር ውጤቱን ብቻ አይቶ መገምገምና መውቀስ ተገቢ አይደለም፡፡ ‹‹ለምን እንዲህ ትወቅሷቸዋላችሁ?›› ስለቻው፤ ‹‹አታውቂያቸውም!›› አሉኝ፡፡ ‹‹እኔን አታውቁኝም? እንዴት ነው እኔ የማላውቃቸው? ያ ትውልድ ማለት እኔ ነኝ!›› አልኳቸው፡፡ ‹‹አንቺ ምንድን ነሽ?›› አሉኝ፡፡ ‹‹ኢህአፓ ነበርኩ!››፡፡ አላመኑም፡፡ ‹‹እኔ አላማ የለኝም? ጭራቅ ነኝ? እኔ ክፉ ነኝ? እኔ ኢትዮጵያን አልወድም?›› የሚል ጥያቄ አነሳሁላቸው፡፡ ‹‹አትቀልጅ! ያ ትውልድማ እንዲህ ሊሆን አይችልም›› አሉኝ፡፡ በእርግጥ በደርግ ጊዜ ሲማሩ ኢህአፓን እንደ ጭራቅ አድርገው ይስሉላቸው ስለነበር ነው፡፡ ‹‹እንግዲያውስ የጠፋው ጠፍቷል ነገር ግን አውቀን አላጠፋነውም አልኳቸው፡፡›› አንድ ነገር መለካት ያለበት በውጤቱ ብቻ አይደለም፡፡ የእኛ አጀንዳ ኢትዮጵያን ማጥፋት አልነበረም፡፡
ልጆቹን ‹‹ስለዛ ትውልድ፣ ስለ ኢህአፓ ማወቅ ትፈልጋላችሁ ልጻፍ?›› አልኳቸው፡፡
‹‹አዎ ጻፊ!››
‹‹ምን አይነት ልጻፍ?››
‹‹ትንሽ እንጨት እንጨት እንዳይል እንጅ ጻፊ!››
‹‹ምንድን ነው እንጨት እንጨት እንዳይል ማለት?
‹‹ትንሽ ፍቅር ቢጤ ጣል አድርጊበት?
‹‹እንዴ! እኛም እኮ ፍቅር እናውቅ ነበር ከየት አምጥቼ ነው ጣል የማደርገው?››
ከዛም ‹‹ምርኮኛ››ን መጻፍ ጀመርኩ፡፡ ከ30 አመት በኋላ ይህን መጽኃፍ የጻፍኩት የዛ ዘመን ፖለቲካ ስላሳመነኝ ነው፡፡ ከአንድ ነገር ጋር ለመዝለቅ ውስጣችን መነካት አለበት፡፡ ሌላ አጀንዳ ካለን፣ ሌላ የምናስበው ነገር ካለን፣ ያንን አጀንዳ ብለን የምንገባ ከሆነ በጊዜ መውጣት ነው የሚያዋጣው፡፡ እኔ የምችለውን ያህል ሄጃለሁ ብዬ አስባለሁ፡፡ ተሂዶ ተሂዶ መዝለል የማይቻል ጎርጅ ላይ ሲደረስ የግዱን ይቆማል፡፡ ከዛ በኋላ ያ ትውልድ ለምንድን ነው ያልቀጠለው የሚለው ሌላ ጉዳይ ነው፡፡ በደርግ ዘመን የደረሰውን ስነ ልቦናዊ ችግር ሲታሰብ ከባድ ቢሆንም ከዛም በኋላ ግላዊ ህይወት ባሻገር ለአገር መስራት አይቻልም ነበር ወይ? የሚለው የእኔም ጥያቄ ነው፡፡ የትውልዱ አለመቀጠል ግን በርካታ ምክንያቶች ይኖሩታል፡፡
የ1966 አብዮት ሲፈነዳ ከላይ የጠቀስኳቸው እርሾዎች ሆነው አብላልተውታል፡፡ ተማሪውም ጥያቄ የጀመረው ቀደም ብሎ ስለነበረ ነው፡፡ የዓለም የፖለቲካ ሁኔታም ስላገዘው ነው፡፡ ይህ ጉዳይ የ1966ን አብዮት አዲስ ምዕራፍ ቢያስከፍተውም ያ ምዕራፍ ግን መዝለቅ አልቻለም፡፡ ምክንያቱም አንዳንዴ ያልታሰበ ውጤትና ስኬት ሰውን ወደ ሰማይ እንዲመጥቅ ያደርጋል፡፡ በዚህም ምክንያት መነሻን አለማሰብ ነገር ተከስቷል፡፡ ብዙ ፖለቲካ ብስለት ሳይኖር ብዙ ነገሮች ተከሰቱ፡፡ ስለዚህ የ1966 አብዮት ለውጥ አምጥቶ ነበር፡፡ ሆኖም የመከነ ለውጥ ነበር ማለት ይቻላል፡፡ በሌላ በኩል ለብዙዎቻችን ዛሬ ድረስ የተሻገረ የአገር ፍቅር ሰጥቶን አልፏል፡፡ ስብዕናችንን እንድንሞርድና እንድንሻሻል አድርጎናል፡፡ እኔ ስለ እራሴ ብቻ ነው መናገር የምፈልገው፡፡ ቢያንስ እኔ አጭበርብሬ አላውቅም፡፡ እንዳላጭበረብር ያደረገኝ ግን እኔ ልዩ ሰው ሆኜ ሳይሆን ያኔ የተፈተሸው ማንነቴ ይመስለኛል፡፡ እኔ ለራሴ ጥቅም ብዬ በማንም ላይ ተራምጄ አላውቅም፡፡ ዛሬ 55 አመት ያለፈኝ ትልቅ ሰው ነኝ፡፡ ግን አጭበርብሬ አላውቅም፡፡ ይህን ያላደረኩት ግን የሚፈትነኝ ነገር ጠፍቶ አይደለም፡፡ ህይወትን ለማሸነፍ ይህኛውን መንገድን (ማጭበርበሩን) ብመርጥ እንደሚያዋጣኝ አጥቸው አይደለም፡፡ ግን በዛን ወቅት የተሞረደው ስብዕናዬ ዛሬም ድረስ አብሮኝ ስላለ ነው፡፡ ብዙዎቹ ይህ ስብዕና አላቸው፡፡ እናም 1966 ብዙ ሰው ፈጥሯል፣ ብዙ ሰው ገድሏል፡፡ የገደለው ግን ያመዝናል፡፡ ለዚህም ይመስለኛል ኢትዮጵያ አሁን ለምትገኝበት ሁኔታ የደረሰችው፡፡ የትም አልደረስንም፤ መዋሻሸት አያስፈልግም፡፡ ዛሬም የትም አይደለንም፡፡ የኢትዮጵያን ህዝብ ወደ ውስጥ ገብተን ካየነው ዛሬም የምንበላው የለንም፣ ዛሬም ድሃ ነን፣ እኔ በዙሪያዬ ብዙ በልተው የማያድሩ ሰዎች አሉኝ፡፡ በዙሪያየ የሚኖረው ህብረተሰብ በታክሲ መሄድ የማይችልና ድሃ ነው፡፡ ጤፍ መግዛት የማይችል ማህበረሰብ ነው፡፡ እነዚህ ሁሉ ምክንያት ከ1966 በኋላ በተከሰተው ችግር ነው፡፡ እሴቶቻችንን አጥተናል፡፡ እምነታችንን አጥተናል፡፡ ድሮኮ የእኛ ቤተሰቦች የሆነ ቦታ መሄድ ፈልገው የተሸከሙትን ነገር ቁጥቋጦ ውስጥ ደብቀው ተመልሰው ያገኙት ነበር፡፡ ይህን መጣል ነበረብን? በምን ተክተነው? መጣል አልነበረብንም፡፡ ነገር ግን እምነትን ጣልን፣ መታመንን ጣልን፡፡ አገር ባላደገበት ግን ለራሳችን ለማደግ ብንፍጨረጨርም ከመውደቅ አንድንም፡፡ አንድን ነገር ይዞ ለመዝለቅና ለመነሳሳት ከውስጥ እርሾ ታስፈልጋለች፡፡ 1966ንም የወለደው ያ እርሾ ነበር፡፡ ነገር ግን መነሻው ጥሩ አልነበረምና የተጋገረው ዳቦ ሊጥ ሆነብን፡፡ እናም እዚህ ደረስን፡፡
(ከአዘጋጁ:- ይህን ጽሑፍ ያሰናዳነው ቆንጅት ብርሃኑ ባለፈው ቅዳሜ በሰማያዊ ፓርቲ ቢሮ ተገኝተው ለወጣት የፓርቲው አባላት የትግል ልምዳቸውን ባካፈሉበት ወቅት ከተናገሩት ውስጥ ነው፡፡)