አባትም አባት ልጅም ልጅ እንዲኾን፣ ተክለ ሃይማኖት ሆይ ጸልይልን

His Holiness Abune Mathias with their Graces the archbishops winding up the Synod meetingመላዋ ኢትዮጵያ እንደ አንድ የኮፕት ኦርቶዶክስ ቤተ ክርስቲያን ሀገረ ስብከት ትቆጠር የነበረችበት የ1600 ዓመታት የሞግዚትነት ታሪክ ከብዙ ተጋድሎና እልክ አስጨራሽ ጥረት በኋላ አክትሞ የመንበረ ፕትርክናውን ነጻነት መቀዳጀቷ ለቤተ ክርስቲያናችንና ለሀገራችን የተበሠረበት ዘመን ነው – በዓለ ሢመተ ፓትርያርክ፡፡

ቅድስት ቤተ ክርስቲያናችን በመንበረ ተክለ ሃይማኖት የመጨረሻውን የክህነት ማዕርግ መብቷን (የኤጲስ ቆጶስነት፣ የሊቀ ኤጲስ ቆጶስነትና የፓትርያርክነት ጸጋን) ለማረጋገጥ የፈጸመችው ተጋድሎ እንዲኹ ያለራእይ አልነበረም – በራስዋ ቋንቋና በራስዋ ልጆች ምእመናኗን በማስተማር የኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ሃይማኖትን በሀገር ውስጥና ከሀገር ውጭ በከፍተኛ ደረጃ ለማስፋፋት፤ መንፈሳዊ፣ ማኅበራዊና ኢኮኖሚያዊ አቅሟን በማጎልበት ለሕዝብዋ በቂ አገልግሎት ለማበርከት ነበር፡፡

Abune Gerima Sept_21_2006በብፁዕ አቡነ ገሪማ አገላለጽ÷ ከ1600 የዘመናት ደጅ ጥናት በኋላ ፈቃደ እግዚአብሔር ኾኖ ጊዜው ሲደርስ በጊዜው ጊዜ የኢትዮጵያውያን ምኞት ተፈጽሞ ኢትዮጵያውያን በኢትዮጵያውያን ኤጲስ ቆጶሳት ሊቃነ ጳጳሳትና ፓትርያርኮች መባረክ መቀደስ ሥልጣነ ክህነት መቀበል ችለዋል፡፡

እግዚአብሔርን የሚያምን፣ ሀገሩን ወገኑን የሚወድ፣ እውነትን የሚከተል በማንኛውም ጊዜ የመንፈስ ደስታ ይሰማዋል፤ ይህንም ያዩ ዐይኖች ብፁዓን ናቸው፡፡

ለቀደምት አበው ምስጋና ይድረሳቸውና፣ ጥንታዊትና ሐዋርያዊት ቤተ ክርስቲያን በመንበረ ፕትርክና ራስዋን ከቻለችበት ከ፲፱፻፶፩ ዓ.ም. ጀምሮ ላለፉት 54 ዓመታት ስታከብረው በቆየችው የመንበረ ተክለ ሃይማኖት የነጻነት በዓል በሀገር ውስጥና ከሀገር ውጭ ከኀምሳ በላይ በኾኑ አህጉረ ስብከት ተስፋፍታለች፤ በሌላ አገላለጽ ከብሔራዊነት ወደ ዓለም አቀፋዊነት ተሸጋግራለች፤ ለሐዋርያዊ ሥራዋ የሚያገልግሉ የጠነከሩ መሠረቶችን በዓለም ዙሪያ መሥርታለች፡፡

በብፁዕ አቡነ ገሪማ የበዓለ ሢመት ጽሑፍ እንደተመለከተው፣ ይህ የቤተ ክርስቲያን ታሪክ ፊትና ኋላ የኾነ፤ የሚኾን ብዙ የተነገረ፤ የሚነገር የታሪክ ገጽታ ያለው በመኾኑ ዕለታዊ፣ ወርኃዊ፣ ዓመታዊ ብቻ አድርገን መተው የለብንም፡፡ ዛሬ በመንበረ ጸባዖት ቅድስት ሥላሴ ካቴድራል የብፁዕ ወቅዱስ አቡነ ማትያስ ቀዳማዊ አንደኛ ዓመት በዓለ ሢመት የምናከብረው፣ ቅዱሳን ፓትርያርኮች በየዘመነ ክህነታቸው ያስመዘገቧቸውን የሥራ ውጤቶችንም በማዘከር ነው፡፡

ዛሬ በዓለ ሢመት ሲከበር፣ ያን ኹሉ የአባቶቻችንን ተጋድሎ በማስታወስ ሐዋርያዊ ተልእኳችንን ከዳር ለማድረስ የሐዋርያዊ መሠረቶቻችንን ዕንቅፋት በማስወገድ አንድነታቸውን የመጠበቅና አቅማቸውን የማጎልበት ሥራ መሥራት አለብን፡፡ ብፁዕ ወቅዱስ አቡነ ማትያስ በአንደኛ ዓመት በዓለ ሢመታቸው አከባበር ላይ እንደተናገሩት፣ ‹‹በዓለ ሢመት የአንድ ግለሰብ በዓል ሳይኾን የቤተ ክርስቲያኒቱ ክብርና ልዕልና ለመጠበቅ የሚፈጸም ሃይማኖታዊና ቀኖናዊ በዓል ነው፤ ፓትርያርኩ የቤተ ክርስቲያኒቱ ወኪል እንጂ ባለቤት አይደለም፤ ለዚኽም ነው ይህ ክብረ በዓል የሚደረግለት፡፡››

የቅዱሳን ፓትርያርኮች በዓለ ሢመት መከበር ያለበት በሓላፊነት ስሜት ለተሻለ ሥራ በመነሣሣት መኾኑን ያስገነዘቡት ቅዱስነታቸው፣ ዓላማውም ይኸው ነውና የቤተ ክርስቲያን ኹለንተናዊ ክብር በምን ላይ አለ? በፊትስ እንዴት ነበረ? አኹንስ ሐዋርያዊ ተልእኮዋን በተሳካ ኹኔታ ለማከናወን ምን መደረግ አለበት በሚል አስተውሎት በዓሉ ሊከበር እንደሚገባ አሳስበዋል፡፡

Megabe Mistir Wolde Rufael Fetahiእኒኽንና የመሳሰሉትን የነጻነቱን በዓል ቁም ነገሮች፣ ያጋጠሙ ችግሮችና ተግዳሮቶች የሚጠቁሙ ቅኔዎች በበዓለ ሢመቱ አከባበር ቀን የዜና ቤተ ክርስቲያን ጋዜጣ ዋና አዘጋጅ ከኾኑት መጋቤ ምስጢር ወልደ ሩፋኤል ፈታሒ ቀርበው ተሰምተዋል፡፡ ‹‹ያልተቀኙትን ቅኔ መተርጎም ያላሳደጉትን ውሻ ጆሮ እንደመቆንጠጥ ነው›› ይባላልና ባለቅኔው ባቀረቡበት አኳኋን በጡመራ መድረኩ ተስተናግደዋል፡፡ የማበረታቻ ውዳሴውን ያኽል ወቅቱን የተመለከተ ታሪክ፣ ትምህርት፣ ማሳሰቢያና ምክርም ተካቶበታልና በጎ በጎውን እንረዳበት፡፡ ‹‹አባትም አባት ልጅም ልጅ እንዲኾን፣ ተክለ ሃይማኖት ሆይ ጸልይልን›› ይላል የመጀመሪያው ጉባኤ ቃና…

ቅኔያት

ከመጋቤ ምሥጢር ወልደ ሩፋኤል ፈታሒ

ጉባኤ ቃና

አበዊነ አበ ወውሉድነ ውሉደ

ከመ ይኩኑነ ጸሊ ተክለ ሃይማኖት ፈድፋደ

ጉባኤ ቃና

ተክለ ሃይማኖት ዕቀቦ በጸሎትከ ዘዘልፍ

ለርእሰ አበው ማትያስ እስመ ፈተናሁ ግዙፍ

ጉባኤ ቃና

ጳውሎስ ንቃሕ እምንዋምከ ይእዜ

በበዓለ ማትያስ ለከ አኮኑ ይደልዎከ ኑዛዜ

ጉባኤ ቃና

ለበዓለ ቅዱስ ማትያስ ግዝፈ ሥጋ አልቦቱ

እም ዓመት ዓመተ እስመ ጸዋሚ ውእቱ

 

ኩልክሙ

ለርእሰ አበው ማትያስ እመንገለ ጽሕሙ

ናስተማስሎ በአሮን ዘእንበለ ከንቱ ውዳሴ

ወእመንገለ ዓይን ይመስል ሱስንዮስሃ ነጋሤ

አምጣነ ወአሉ ወኃደሩ

እንዘይፈጥሩ ኪያሁ ሥላሴ

ወተፈጥረ ለሕዳሴ

ከማሁ ለኖኅ ድኅረ ተፈጥረ ድምሳሴ

 

ለዓለም

ትካትሂ በደብረ ሲና በከመ አርአዮ ለሙሴ

እንዘ ያስተፃምር ነበልባለ ምስለ ሐመልማል አምላከ አውሴ

ኢይፈቅድ ይፍልጥ እምነ ብእሲ ብእሴ

ለማትያስ ሕሊናሁ እመ የአብዩ ለቅዳሴ

እምአጽባዕት አጽባዕት ወእምናሴ ምናሴ

ለማትያስ ሕሊናሁ እመ የአብዩ ለቅዳሴ

 

፪ኛ ኩልክሙ

ኦ ማትያስ አግአዜ ኩሉ

አግአዚተ ትኩን ለዓመትከ ስድዳ

ለወልደሩፋኤል ምስሌሁ ወምስለ ካልአን ውሉዳ

ወበዓመትከ ጽጌሬዳ

ሙስና ተሰደ እም ቤተ ክህነት ቤርሙዳ

 

ለዓለም

ዕቀባሂ ለብኩርናከ ፍጥረተ ዓለም ዘንዕዳ

ወአስምዕ ተጽእኖታ ለበዓለ ቤት ወለእንግዳ

ውሉደ ቤታ ለአጋር እስመ ዖድዋ በዐውዳ

ወቦ በአመክሮ እምሉዓላሌሃ ከመያውርዳ

ላእከ ቤተ ቦንኬ ሥሉጥ በውስተ ስፉሕ ማሕፈዳ

ወቦ በአመክሮ እምሉዓሌሃ ከመያውርዳ

 

መወድስ

አበ ብዙኃን ማትያስ ናስተበቁአከ

እም ዝንቱ ዓመት ወሚመ እምይእዜ

በበሕቅ ትግበር ለውሉድከ ኑዛዜ

ወከመትጸጉ ለጊዜከ ጊዜ

እስመ እግዚእነ በበሕቅ

ዘኩሎ ፈጸመ ወአሰሰለ ትካዜ

ወሚመ በእራሁ እንዘይከውን አኃዜ

ዓለማተ ለፍጥረቱ ዘኮነ ተአዛዜ

ወእንበለ ዕረፍት የሐውጽ ነገደ ጉራጌ ወዶርዜ

አሕጸረ ጊዜያተ ጳውሎስ ዘሳንሆዜ

 

ኩልክሙ

አበዊነ ቁሙ በእግረ ዋህድና

ጸላኢ ኢይርከብ በውስትነ ቤተ

ወኢይባዕ ውስጠ እንዘ ይተሉ ፍልጠተ

ወቤቴል አሐቲ ኢትኩን ዝርወተ

አኃዝ ማኅበራተ*

መዋግደ ብዙኅ ጸጋከ ወአስተናድፍ ሥርዓተ

ማትያስ ኖላዊነ በዘረሰይከ ክሡተ

ለቤቴል ሙስናሃ ዘኮነ ኅቡአተ

እንዘ ያውእዙ ደመ ወይሰብሩ አዕፅምተ

ዘአወፈዩከ አበዊከ ጥንታዊተ ሃይማኖተ

ወአባግኢከ ትዕቀብ እስመረከብከ እብሬተ

ዘአወፈዩከ አበዊከ ጥንታዊተ ሃይማኖተ