ፈቃደ ሸዋቀና ስለፍቅረስላሴ ወግደረስ መጽሃፍ የሰጠው ግምገማ፣ ኢሰፓ ደርግን ሊተች የሚችልበት የሞራል ብቃት የለውም
ፈቃደ ሸዋቀና ስለፍቅረስላሴ ወግደረስ መጽሃፍ የሰጠው ግምገማ፣ ኢሰፓ ደርግን ሊተች የሚችልበት የሞራል ብቃት የለውም
ከታዛቢ
ጽሁፉን በፒ.ዲ.ኤፍ. ለማንበብ እዚህ ላይ ይጫኑ ፍቃደ ሸዋቀና
በቅርቡ ለንባብ የበቃውን የአምባገነኑ፣ የጨፍጫፊውና ኢትዮጵያን አሁን ለደረሰችበት ውድቀት ከፍተኛ ድርሻ ለነበረው የደርግ መንግስት ቁንጮ የነበረው ፍቅረስላሴ ወግደረስ የቀላመደውን “መጽሃፍ” ተብዬ ከቁምነገር በመቁጠር በዛው በደርግ ስርዓት በኢሰፓ ውስጥ ቁልፍ ሚና የነበረው ፈቃደ ሸዋቀና “ጅብ የማያውቁት አገር ሄዶ ቁርበት አንጥፉልኝ አለ” እንደሚባለው አይኑን በጨው አጥቦ ገምጋሚና ተች ሆኖ መቅረቡ እጅግ ያሳዝናል።
ፍቃደ ሸዋቀና በአዲስ አበባ ዩኒቨርስቲ የጆግራፊ ትምህርት ክፍል ውስጥ በመምህርነት ተቀጥሮ ደመወዝ ሲበላ የኖረ ቢሆንም ዋንው ስራው ግን የአዲስ አበባ ዩኒቨርስቲ የኢሰፓ መሰረታዊ ድርጅት ዋና ጸሃፊ ለነበረው ተስፋዬ ሸዋዬ ተላላኪ ይሁን ረዳት በማይለይበት ሁኔታ ላይ-ታች ሲል እንደነበር በስፍራውና በጊዜው የነበርን የምናውቀው ሁኔታ ነው። ደርግ ዩኒቨርስቲውን ለመቆጣጠርና ለማፈን የዘረጋው የኢሰፓ መዋቅር ዩኒቨርስቲውን ከነጻ የአካዳሚ መስክነት ይልቅ የፕሮፓጋንዳ ማካሄጃ ውድማ አድርጎ ከፍተኛ ጉዳት በዩኒቨርስቲው የመማር-ማስተማር ሂደት ላይ አድርሷል።
በተስፋዬ ሸዋዬ የሚመራውና በፍቃደ ሸዋቀና አጋፋሪነት የሚካሄደው የዩኒቨርስቲው የኢሰፓ አመራር፤ መምህራን ዕውቀታቸውን በማስተማር፣ በጥናትና በምርምር ማሳለፍ ሰገባቸው ለአገርና ህዝብ ጥቅም በሌለው ውይይት ክበብ፣ የጉልበት ስራና የመንደር ምስረታ ዘመቻ ጊዜያቸውን እንዲያባክኑ በማድረግ በአገሪቱ ውስጥ ያደረሰው ጉዳት እጅግ ከፍተኛ ነው። ለምሳሌ ያህል በነፍቃደ ሸዋቀና አዝማችነት በ1977 ዓ.ም. በመተከል አውራጃ (ጎጃም) እንዲሁም በጋምቤላ (ኢሉባቦር) ውስጥ ዩኒቨርስቲው ለ3 ወራት ያህል ተዘግቶ ተማሪዎች፣ መምህራንና የአስተዳደር ሰራተኞች “ለሰፋሪዎች ቤት ለመስራት” በሚል ምክንያት የተደረገው ጥፋት በዩኒቨርስቲው ታሪክ ውስጥ ትልቅ ጠባሳ ጥሎ አልፏል።
እነፍቃደ ሸዋቀና ዩኒቨርስቲውን ጥርቅም አድርገው ዘግተው የዩኒቨርስቲውን ዘማቾች ሜዳ ላይ በትነው ለከፍተኛ እንግልትና በሽታ ዳርግው የተገኘው ውጤት የኢሰፓን የበላይነት በዩኒቨርስቲው ላይ ከመጫን ያለፈ አልነበረም። በተለይ እኔ በነበርኩበት ጉብላክ ጣቢያ እልም ያለ በረሃ ከመሆኑም በላይ የመጠጥ ውሃ፣ምግብ፣ መጸዳጃ፣ መጠለያና ምንም ዓይነት የሰብዓዊ መገልገያዎች ባልተሟሉበት ቦታ ከፍተኛ ቁጥር ያለው ሰው ተበትኖ ሲንከራተት ማየት ለኢሰፓዎች ኃይላቸውን ማሳያ አድርገው ከመጠቀም ያለፈ ምንም የተሰራ ስራ አልነበረም። ለይስሙላ በቤት ስም ደርድረናቸው የነበሩት የቀርከሃ የጎጆ ቤት ማገሮችና የውሸት ጣሪያዎች እንኳን ሰው ሊኖርባቸው ይቅርና ለማስታወሻ የሚሆን ፎቶግራፍ ለመነሳት ስንደገፋቸው ተፈንግለው ይወድቁ ነበር። ነገር ግን ኢሰፓዎች በሚቆጣጠሩት የዜና ማሰራጫዎች ለኢትዮጵያ ህዝብ የመንደር ምስረታ በተሳካ ሁኔታ ተካሄደ እያሉ ውሸት ይቀልቡ ነበር።
ፍቃደ ሸዋቀና በዩኒቨርስቲ ውስጥ ዕውቀቱና ትምህርቱ ካለው በማስተማርና በምርምር ስራ መሰማራት ሲገባው ዩኒቨርስቱው ውስጥ የደርግን መመሪያዎችን በኢሰፓ በኩል በማቀናጀት ስራ ላይ ከሚያውሉትና ከሚያስፈጽሙት መካካል አንዱ ነበር። በወቅቱ ከነበሩት አስተማሪዎችና ተመራማሪዎች መካከል የኢሰፓ አባላት የነበሩት እጅግ በጣም ጥቂት ነበሩ። ብዙዎቹ ሀቀኛ ምሁራን የነፍቃደ ሸዋቀና ኢሰፓ መሰረታዊ ድርጅት በሚያደርስባቸው የተለያዩ በደሎችና ጫናዎች በመማረር አገር እየለቀሱ ለስደት ተዳርገዋል። በዩኒቨርስቲው ውስጥ ኢሰፓና አ.ኢ.ወ.ማ. በቅንጅት በመንቀሳቀስ ችሎታና የአካዳሚ ብቃት ያላቸው መምህራን ሳይሆን ለደርግ ሥርዓት ታማኝና አገልጋይ የነበሩ እንዲቀጠሩ በዲኖችና በዲፓርትመት ኃላፊዎች ላይ ጫና በማድረግ ዩኒቨርስቲውን አበላሽተዋል። እንደውም ወደመጨረሻው የደርግ ዘመን ላይ ዩኒቨርስቲውን ከየካቲቲ 66 የፖለቲካ ትምህርት ቤት ለመለየት የማይቻልበት ጊዜ ነበር ለማለት ያስደፍራል።
የከፍተኛ ትምህርት ተቋማት አባላት ሲሆን አስከፊውን የደርግን ስርዓት ለመጣል የህዝብን አጀንዳ አስንተው መታገል ሲገባቸው፣ ካልቻሉና ከፈሩ ደገሞ ግብር ከፋዩ የኢትዮጵያ ሕዝብ ለሚከፍላቸው ደምወዝ ሙያዊ ተግባራቸውን ብቻ መወጣት ሲገባቸው ካድሬ ሁነው እራሳቸው ቀለውና ተዋርደው ሌሎችንም ማስጨነቅና ማወከ አይገባቸውም ነበር። ለምሳሌ ያህል ፕሮፌሰር መስፍን ወልደማርያም በዩኒቨርስቲው ውስጥ በግላጭ ደርግን ይቃወሙ የነበሩ ሲሆን ለዚህም ታሪካቸው በወርቃማ ቀለም ተጽፎላቸው ለዘላለም ይኖራል።
ፍቃደ ሸዋቀና ግን ሽንጡን ገትሮ ያገለግል የነበረውን ደርግ ኢሰፓን ለመቃወም መጀመሪያ የራሱን ሀጢዓት ተናዞና እውነቱን ከነገረን በኋላ የጌቶቹን የነፍቅረስላሴ ወግደረስና የነመንግስቱ ኃይለማርያንም ሊነግረን ይችላል። ቢያንስ ማንነቱንና በኢሰፓ ውስጥ የነበርውን ሚና መግለጽ ይገባው ነበር።ስለሆነም ለስልጣንና ለጥቅም እንደ ፍቃደ ሸዋቀና አይነቶች በዩኒቨርስቲው ኢሰፓ ጽ/ቤት ውስጥ የሰሩት ወንጀል አሁን አገራችን ላይ የተጫነው የወያኔ አገዛዝ ላይ ትኩረታችንን ስላደረግን የነሱን የረሳንላቸው እንዳይመስላቸው።
ለወደፊት ደግሞ እንዳስፈላጊነቱ ተጨማሪ ዝርዝር መረጃ ማውጣት ይገባል። ፍቃደ ሸዋቀና በኢሰፓነት ደርግን በማገልገል ኢትዮጵያ ላይ ለፈጸመው ወንጀል በተለይም ለበደላቸው የዩኒቨርስቲው አካላት ይቅርታ ሊጠይቅና ከህዝብ ጋር ሊታረቅ ይገባዋል። እኔ ይህችን አጭር ማስታወሻ ለመጻፍ የወሰንኩት ፍቃደ ሸዋቀና እራሱ የደርግ አስፈጻሚ ሆኖ እንደ ገለልተኛ ወይም በደርግ እንደተበደለ ሆኖ መቅረቡን ለማጋለጥ ስለፈለኩኝ ነው። ፍቅረስላሴ ስለሚቀላምደው ገለልተኛ የነበሪ እውነተኛውን የሚያውቁና ግፉና በደሉ የደረሰባቸው ቢናገሩ ይሻላል። ፍቃደ ሸዋቀና አለቃው የነበረውን ፍቅረስላሴን መተቸቱ የራሱን ኃጢአት ለመሸፈን ይረዳኛል ብሎ ከሆነ በጣም ተሳስቷል። ኢሰፓ ደርግን የሚተችበት ምንም ምክንያት የለውምና። ኢሰፓና ደርግ ተንኮታኩተው እስኪወድቁ ድረስ እጅና ጓንት ሆነው አብረው አገራችንን ወደ ገደል ሲመሩ እንደነበር የሚረሳ አይደለም። ኢሰፓ ደርግን መተቸት በኔ አመለካከት አመድ በዱቄት ይስቃል ዓይነት ነው።