አቡጊዳ – ግንቦት ሰባት በባህር ዳር የታየዉን ሕዝባዊ ተቃዉሞ ማደራጀትና መምራት ትልቅ ነገር ነው አለ።
የግንቦት ሰባት በድህረ ገጹ ላይ ይፋ ባደረገዉ የሳምንቱ ርእስ አንቀጽ፡ በመኢአድ እና አንድነት ፓርቲ ለተጠራዉ የባህር ዳሩ ሰላማዊ ሰልፍ ያለዉን አድናቆት ገለጸ።
«ፈታኝ ሁኔታዎችን ተቋቁመው የየካቲት 16 ቀን 2006 ዓ.ምን ሕዝባዊ ተቃውሞ ላደራጁና በተቃውሞውም ለተካፈሉ ሁሉ ያለውን አክብሮት ይገልፃል። ሕዝብ ብሶቱን የሚገልጽበት ሕዝባዊ ተቃውሞ ማደራጀትና መምራት መቻል ትልቅ ነገር ነው። ሕዝባዊ ተቃውሞዎች ወደ ሕዝባዊ እምቢተኝነት የማደግ እድል አላቸው። ስለሆነም ግንቦት 7 ለባህርዳሩ ሕዝባዊ ተቃውሞ አደራጆችና ተሳታፉዎች “እንኳን ደስ ያላችሁ”» ሲል የግንቦት ሰባት ርእስ አንቀጽ ያተተ ሲሆን በባህር ዳር ለታየው አይነት ሰላማዊ እንቅስቃሴም ያለዉን አጋርነት በይፋ አስቀምጧል።
ግንቦት ሰባት «ኢሕአዴግ ሰላም የሚያውቅ አይደለም» በሚል በሰላማዊ ትግል ለዉጥ ማምጣት አይቻልም በሚል ድምዳሜ፣ የትጥቅ ትግል አማራጭ ይዤ እንቀሳቀሳለሁ የሚል ድርጅት እንደሆነም ይታወቃል።