ሁዳዴ ፆምን ለመፆም ተዘጋጅተዎል??

ሁዳዴ ፆምን ለመፆም ተዘጋጅተዎል??

ነገ ሠኞ የካቲት አስራ ሠባትቀን ሁለት ሺ ስድስት ዓመተ ምህረት በኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተክርስትያን ዐብይ ፆም ይጀመራል።
ለመፆም ተዘጋጅተዎል?ዘንድሮ ፆም ለነፍስ ብቻ ሣይሆን ለስጋም ጠቃሚ እየሆነ ነውና ሀኪም ቀይ አብርቶ በስጋ ምክንያት ሥጋት ላይ መሆንዎን ሣያረዳዎ በንስሃ አባትዎ ምክር ፆሚ ይሁኑ።
ቢፆሙ ሸንቃጣ ይሆናሉ።ስጋዎ ፈተና ላይ አይወድቅም።መንፈስዎ ይረጋጋል።ባይፆሙ ኪሎዎ ይጨምራል።ከሀኪም ፊት አይርቁም።ቁና ቁና ይተነፍሣሉ።ወጪዎ ይጨምራል።አልጋና ብልግና ሊያዘወትሩ ይችላሉ።
ኪስዎ ከመጀመርያው ፆሚ ከሆነ የኔ ምክር እርስዎን አይመለከትምና ዘና ይበሉ።ፆም ሲፆሙ ሆድዎን ብቻ ማዕቀብ አይጣሉበት። ምላስዎን አደብ አስገዟት።ዓይንዎን ከዳሌና ጭን ላይ ይንቀሉ።ጆሮዎ የአመት ረፍት ያስወጡት።እግርዎ አይንጦልጦል።ያኔ የወጣልዎ ምርጥ ፆሚ ይሆናሉ።አንድ ነገር ረሣሁ።በልብዎ ግርግዳ ያከማቹትን የቂምና የጥላቻ ዶሴ ፈጥነው ይደልዙ።ዲሌት ያርጉት።የቂምና የበቀል ጎሬ የሆነ ልብና ጭንቅላት ይዘው ከአምላክዎ ጋር መገናኘት እንደማይችሉ ይገንዘቡ።ልብዎ በቂም ኔትወርክ ተጨናንቆ ወደ ፈጣሪዎ የሚያደርጉት ማንኛውም ጥሪ አይሠማምና ውዝፍ ሂሣብዎን ያወራርዱ።ያኔ ሁዳዴን ፆም ለመፆም ሚኒማውን ያሟላሉ።
ሃምሣ አምስት ቀናት ወጥረው ቢፆሙ ለስጋዎም ሆነ ለነፍስዎ ርጋታና ዕርካታ ያገኛሉ።ቅበላን ለመሆኑ እንዴት አሣለፉት? ጮማ ቆረጡ? ከጠጇስ ጨለጡ ?ከስጋ ወደ ሽሮ ሊሸጋገሩ የቀረዎ እራት የተባረከ ይሁን።
አክሊለ ሠማያት ዘ መካነ ሠላም