ሐውልቱ ሥር ሆኜ እነዚያን ሰማዕታት ሳስብ! ክፍል.2 (በላይ ማናዬ)
በክፍል.1 ላይ ቃል በገባሁት መሰረት ዛሬ የካቲት 12 ሰማዕታት ሐውልት ስር ሆኜ «ስለነዚያ» ወጣቶችና በዙሪያቸው ስለነበሩ የአርበኝነት ተጋድሎው አጋሮች በጥቂቱ አወሳልሃለሁ፡፡ አዎ፣ ዛሬ ስለ የካቲት 12 ቀን፣ በዋነኛነትም ስለ አብርሃ ደቦጭና ሞገስ አስግዶም እንዲሁም ሌሎች ከጉዳዩ ጋር የተገናኙ የታሪኩ ዋና ዋና ተዋናዮችና ነጥቦችን እያነሳን እንጥላለን፡፡
የካቲት 12/1929 ዓ.ም የአዲስ አበባ ህዝብ የግፍ እልቂት በተነሳ ቁጥር ሞገስ አስግዶም እና ጓደኛው አብርሃ ደቦጭ አብረው ይነሳሉ፡፡ ሁለቱም ወጣቶች የኤርትራ ተወላጆች ናቸው፡፡ ሁለቱም ከኤርትራ ወደ አዲስ አበባ በጣሊያኖች አማካኝነት እንዲመጡ ከተደረጉ በሗላ ሞገስ በዳግማዊ ምኒልክ ት/ቤት፣ እንዲሁም አብርሃ በተፈሪ መኮንን ት/ቤት ገብተው መማር ቀጠሉ፡፡ እዚህ ላይ መረሳት የሌለበት ነጥብ ወጣቶቹ ወደ አዲስ አበባ የመምጣታቸው ምስጢር ለፋሽስት ጣሊያን አስተርጓሚና ሰላይ ሆነው እንዲያገለግሉ ታስቦ እንደነበር ነው (ፈረንሳይኛ፣ ጣሊያንኛ፣ እንግሊዝኛና በመጠኑ ጀርመንኛ እንዲሁም የሀገሬውን ቋንቋ ይናገሩ እንደነበር ተጠቅሷል)፡፡
በሌላ ወገን ደግሞ የወጣቶቹን ወደ አዲስ አበባ መምጣት በወቅቱ በፋሽስት አስተዳደር ስር በነበረችው ኤርትራ ያለውን ጭቆና ገፊ ምክንያታቸው እንደነበር የሚጠቅሱ አሉ፡፡ በተለይም ወጣት ሞገስ ኢትዮጵያን አብዝቶ ይወድና በኢትዮጵያዊነቱ የሚኮራ ነበር፡፡ ስለሆነም ወደ አዲስ አበባ ለመምጣት የዘወትር ፍላጎቱ ሆኖ ቆይቷል፤ «ሞገስ ጣሊያንን ሳያስፈቅድ የቅኝ ግዛት ድንበር አቋርጦ ወደ ኢትዮጵያ ገባ» እንዲል፡፡ ኸረ እንዲህም ተመስክሮለታል፤ «His heart and mind was for Ethiopia.»፤ ከዚህ ነጥብ መረዳት እንደሚቻለው ኢትዮጵያ በህልሙም በእውኑም ሞገስ ውስጥ ነበረች፡፡
ሞገስና አብርሃ ትምህርታቸውን እንዳጠናቀቁ ሞገስ በመሬት ይዞታ መስሪያ ቤት ጸሐፊ ሆኖ ሲቀጠር አብርሃ በበኩሉ በጣሊያን ሌጋሲዮን ተቀጥሮ መስራት ቀጠሉ፡፡ በጊዜው በጣሊያን ፖለቲካ ውስጥ ከሞገስ ይልቅ አብርሃ ብዙ ስራዎች ሲሰራ ነበር፤ ሞገስ ባብዛኛው የአብርሃ ረዳት ነበር ማለት ይቻላል፡፡ የካቲት 12/ 1929 ዓ.ም በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ ግቢ ውስጥ (ያኔ ገነተ ልዑል ቤተ መንግስት) በግራዚያኒ ላይ አብርሃና ሞገስ ቦምብ ጥለው አቆሰሉት ከመባሉ በፊት በጣሊያን ላይ አኩርፈው ተቀምጠዋል ከተባሉ መኳንንት ጋር ወጣቶቹ ምስጢራዊ ግንኙነት ሲያደርጉ ቆይተዋል፡፡
በነገራችን ላይ የካቲት 12 ግራዚያኒንና ሌሎች የፋሽስት ወታደራዊ ባለስልጣናትን ለመግደል በተሸረበው ሴራ ዋና ተዋናዮቹ ሞገስና አብርሃ ብቻ አልነበሩም፡፡ መረጃዎች እንደሚጠቁሙት በእለቱ ለተፈጸመው ጸረ ፋሽስት ድርጊት ከጽንስሱ ጀምሮ ስድስት ኢትዮጵያዊያን ስማቸው ይነሳል፡፡ እነዚህም ቀደም ብለን የጠቀስናቸው ሞገስና አብርሃ፣ በመምህርነት ሞያ ይሰራ የነበረው ስብሃት ጥሩነህ፣ ስምዖን አደፍርስ፣ ቤጅሮንድ ለጥይበሉ ገብሬና ባሻህውረድ ሃብተወልድ ነገሩን አውጥተው አውርደው ጥቃቱ እንዲፈጸም ታትረዋል፡፡ (ስምዖን አደፍርስ እነ አብርሃን ከጥቃቱ በሗላ በታክሲ በመሸኘት እንዲሸሹ ያስቻላቸው እሱ መሆኑን ስላሴ ካቴደራል በሚገኘው የመቃብር ስፍራው ላይ የሰፈረው ጽሑፍ ይናገራል፡፡)
የሚገርመውና የሚደንቀው ግን ስደት ላይ የነበሩት ንጉሰ ነገስት ቀዳማዊ ሃይለስላሴ በሴራው ላይ እጃቸው ነበረበት መባሉ ነው፡፡
ስደተኛው ንጉስ በየካቲት 12ቱ ሴራ እቅድ እጃቸው እንደነበረበት የሚጠቅሱት ወገኖች የሚያነሱት ነጥብ ንጉሱ ከቤጅሮንድ ለጥይበሉ እና ባሻህውረድ ጋር ምስጢራዊ ግንኙነት ማድረጋቸውን ነው፡፡ ዝርዝር እቅዱንና አፈጻጸሙን ሁሉ ያውቁ ነበር ባይባልም እነ ቤጅሮንድ ለጥይበሉ ከእነ አብርሃ ጎን እንዲቆሙ ግን ድጋፋቸውን አሳይተው እንደነበር ታውቋል፡፡
ማይጨው ላይ ዘምተው ድል መሆናቸው የማይቀር መሆኑን የተገነዘቡት ንጉሰ ነገስቱ ሸሽተው ወደ አውሮፓ ቢሰደዱም ትግላቸው ግን አልተገታም ነበር፤ በተለይ በዲፕሎማሲው መስክ፡፡ ከዚህ ባለፈ ግን ንጉሱ እንግሊዝ ሎንደን ሆነው አርበኞችን በመደገፍና ምስጢራዊ ግንኙነት በማድረግ ወራሪው ፋሽስት የኢትዮጵያ ቆይታው በአጭር እንዲቀጭ ሚናቸው የላቀ ነበር፡፡
አሁንም የሰማዕታት ሐውልቱ ስር ነን፡፡ ድጋሜ ላስታውስህ፤…ሞገስና አብርሃ ቦምብ በጣሉበት አዲስ አበባ ብቻ 30,000 ህዝብ የፈጀ ጅምላ ጭፍጨፋ ተካሂዷል፡፡ ቀጥሎም አብርሃና ሞገስ ሸሽተው በሄዱበት ደብረሊባኖስ ገዳም በተመሳሳይ ግንቦት 12 ቀን ብዙ ህዝብ ተጨፍጭፏል፡፡ በሗላም ሰሜን ሸዋ ወደነበሩት የተባበሩት አርበኞች ግንባር ይዞታ በሄዱ ጊዜ አንዳንዶቹ በሰላም ሲቀበሏቸው አዲስ አበባ ከተማ ውስጥ ምን እንደሚሰራ በቂ መረጃ እንደነበራቸው የሚታወቀው እነ ሻለቃ መስፍን ስለሺ እና ባላምባራስ አበበ አረጋይ ግን ወጣቶቹን እንዲታሰሩ አደረጓቸው፡፡
እነሞገስ ከእስር እንደተፈቱ ሀገር ጥለን ወደ ጠረፍ እንሄዳለን ብለው ምክንያት ከመስጠታቸው በቀር በትክክል ወደየት እንደሄዱ አይታወቅም የሚሉ አሉ፡፡ ሌሎች ደግሞ ከእስር እንደተለቀቁ ወደ ዳር ሀገር በመሸሽ ላይ እያሉ ቋራ ላይ እንደተገደሉ ይናገራሉ፡፡
የግራዚያኒ የጭፍጨፋ ትዕዛዝ መነሻ «እነ አብርሃ ቦምብ ወርውረውብኝ ሲሄዱ ህዝብ ወንጀለኞችን በዝምታ ከመመልከቱም በላይ ትብብሩን አሳይቷል» የሚል ነበር፡፡ በጊዜው ግራዚያኒ ወጣቶቹ የሚገኙበትን ለጠቆመ እስከ 10,000 ማሪያ ትሬዛ ብር ለመስጠትም ቃል ገብቶ ነበር ይባላል፡፡ ይህም ሆኖ ግን ሰላማዊውን ህዝብ በጥይት፣ በአዷማ፣ በገጀራ፣ በአካፋ፣ በመጥረቢያ… በአውሬያዊ ጭካኔ ከማንኮት አልተመለሰም፡፡
ወራሪው ጣሊያን የፈጀውን ህዝብ ስንመለከት አስከፊነቱ በቁጥር ብቻ የሚገለጽ አልነበረም፡፡ ኢትዮጵያ ባለ በሌለ አቅሟ ውጭ ሀገር ድረስ ልካ ያስተማረቻቸው ውድ ልጆቿ በፋሽስታዊ ጭፍጨፋ ጠፍተዋል፡፡ እንዲያውም በወቅቱ አንድ የተማረ ትውልድ «ሙሉ ለሙሉ» ወድሟል ይባላል፡፡ ይህም ሀገሪቱን ምን ያህል ዋጋ እንዳስከፈላት መገመት ትችላለህ፡፡
የፋሽስት ግፍ ሌላም ታሪክ እንድናስታውስ ያደርገናል፡፡ አዎ፣ ከዚህ የጭፍጨፋ ታሪክ አንድ አመት ቀደም ብሎም ጣሊያን አቡነ ጴጥሮስን በግፍ መግደሉ ይታወሳል፡፡ በሐምሌ 22 ቀን 1928 ዓ.ም በማዘጋጃ ቤት አጠገብ በጥይት ተደብድበው እንዲሞቱ የተፈረደባቸው አቡነ ጴጥሮስ የኢትዮጵያን ህዝብ ለአርበኝነት ያነሳሱና ለፋሽስት መገዛትን ያወግዙ የነበሩ ጀግና አባት ነበሩ፡፡ በዚህ ድርጊታቸው ምክንያትም አቡኑ ለይስሙላ በተሰየመ የፋሽስቶች ችሎት ቀርበው የመሐል ዳኛ በነበረው ጣሊያናዊ ዳኛ እንዲህ የሚል ጥያቄ ቀርቦላቸው ነበር፡፡
«ካህናቱም ሆነ የቤተ ክህነት ባለስልጣኖች፣ ሊቀ ጳጳሱ አቡነ ቄርሎስም ጭምር የጣሊያንን መንግስት አሸናፊነት አምነውና አሜን ብለው ሲቀበሉ እርስዎ ለምን አመጹ? ለምንስ ብቻዎን አፈንጋጭ ሆኑ?»
አቡነ ጴጥሮስ እንዲህ ሲሉ መለሱ፤ «አቡነ ቄርሎስ ግብፃዊ ናቸው፤ ስለ ኢትዮጵያና ኢትዮጵያዊያን የሚገዳቸው ነገር የለም፡፡ እኔ ግን ኢትዮጵያዊ ነኝ፤ ሃላፊነትም ያለብኝ የቤተ ክርስቲያን አባት ነኝ፡፡ ስለዚህ ስለሀገሬና ስለቤተ ክርስቲያኔ እቆረቆራለሁ፡፡ ከዚህ በቀር ለእናንተ ችሎት የማቀርበው ነገር የለኝም፤ ለፈጣሪዬ ብቻ የምናገረውን እናገራለሁ፡፡ እኔን ለመግደል እንደወሰናችሁ አውቃለሁ፤ ስለዚህ በእኔ ላይ የፈለጋችሁትን አድርጉ፡፡ ተከታዮቼን ግን አትንኩ» በማለት ተናገሩ፡፡ (በነገራችን ላይ ግብፃዊው አቡነ ቄርሎስ በየካቲት 12ቱ ጥቃት ወቅት ከግራዚያኒ ጎን ነበሩ፤ በዚህም በቦምብ ፍንዳታው ቆስለው እንደነበር መረጃዎች ያሳያሉ፡፡)
አቡነ ጴጥሮስ እንዳሉትም ሆነ፤ ፋሽስት ቀድሞውኑ አቡኑን ለመግደል ወስኖ ስለነበር የአዲስ አበባ ህዝብ መቀጣጫ እንዲሆነው ግድያው ሲፈጸምባቸው እንዲመለከት በማድረግ አረመኒያዊ እርምጃውን ወሰደባቸው፡፡ አቡኑም ከመሞታቸው በፊት የኢትዮጵያ ህዝብና መሬት ለፋሽስት ጣሊያን እንዳይገዙ አወገዙ፡፡ አቡነ ጴጥሮስ የፍቼ ቀዬ ያፈራቸው ድንቅ አርበኛና የቤተ ክርስቲያን አባት ነበሩ፡፡
ከዚህ ጋር በተገናኘ ሌላ ነገር እናስታውስ፤ ስመጥሯ ሴት አርበኛ ሸዋረገድ ገድሌ የካቲት 12 ቀን 1929 ዓ.ም ከደረሰው አደጋ ጋር በተያያዘ በጣሊያን ሰዎች ተይዘው ወደ አዚናር ተወስደው ታስረው ነበር፡፡
ይህ ሁሉ ዋጋ የተከፈለበትን የነጻነት ትግል እና መስዋዕትነት ለመመስከር የቆመው ሐውልት ስር ሆኜ ታሪካቸውን ሳወሳ ለአሁኑ ማንነቴ የዋሉልኝን ውለታ እውቅና በመስጠት ነው፡፡ አቤት፣ ነጻነት ዋጋዋ ብዛቱ! አቤት፣ ኢትዮጵያዊነት እና የአልገዛም ባይነት ስሜት የተቆራኙበት ሲባጎ ጥንካሬ! በል ለእነዚህ ሰማዕታት የከበረ ምስጋና እናቅርብ….የወደቁላትን ሀገር መልካሙን ብቻ ልናደርግላትና ነጻነቷን ልንጠብቅ ቃል እንግባላቸው፤ ስለ ኢትዮጵያ የተሰዋችሁ ሁሉ ክብር ለእናንተ ይሁን!
(የቀዳማዊ ሃይለስላሴን ህይወቴና የኢትዮጵያ እርምጃ፣ የፋንታሁን እንግዳ ታሪካዊ መዝገበ ሰብ፣ የኢያን ቻምቤል «Ethiopia 1937: The Plot to Kill Graziani» እና የአምስቱ የመከራ አመታት አጭር ታሪክ የተሰኙ መጽሐፍትን መረጃ ተውሸባቸዋለሁ፤)