የቋሚ ሲኖዶሱ ውሳኔ ዳግመኛ ተሻረ! የፓትርያርኩ ልዩ ጽ/ቤት የድሬዳዋ ቅ/ገብርኤል ሕንፃ ግንባታ እንዳይመረመር ለሁለተኛ ጊዜ ተከላከለ! የከተማው ምእመን የደብሩን ጉዳይ በቋሚ ሲኖዶሱ ውሳኔ መሠረት ለመፍታት አንድነቱን አጠናክሯል!

Bidding documentየፓትርያርኩ ልዩ ጽ/ቤት በጓሮ በር ለሚገቡ ሙሰኞችና ጎጠኞች ሽፋን መስጠቱን ቀጥሎበታል፡፡ ልዩ ጽ/ቤቱ እንደቀድሞው ጊዜ ኹሉ ዛሬም በማይመለከተው ጉዳይ ጣልቃ እየገባ የሕገ ቤተ ክርስቲያን ጥሰት እየፈጸመ ይገኛል፡፡

ሙሰኞችና ጎጠኞች የበላይነት ይዘው በተቆጣጠሩት ጽ/ቤት የቅ/ሲኖዶሱን ውሳኔ እየተላለፈ በሚፈጽመው ኢ-ፍትሐዊ ተግባር የመንበረ ፓትርያርኩን ተቀባይነትና አገልጋዩና ምእመኑ በመልካም አስተዳደር መስፈን ላይ ያለው እምነት እንዲሸረሸር መንሥኤ እየኾነ ይገኛል፡፡

ከላይ የምትመለከቱት፣ የድሬዳዋ ሳባ ደብረ ኃይል ቅዱስ ገብርኤል ቤተ ክርስቲያን የሕንፃውን ሒሳብና ግንባታ በአማካሪ ድርጅት ለማስመርመር የካቲት ፪ ቀን ፳፻፮ ዓ.ም. በኢትዮጵያን ሄራልድ እና በአዲስ ዘመን ጋዜጦች ያወጣው የጨረታ ማስታወቂያ ነው፡፡ የሕንፃ ቤተ ክርስቲያኑ ግንባታ ከአማካሪ ድርጅቱ ጋራ በውል ከተያዘው ጊዜ ከስድስት ዓመት በላይ የዘገየና በሚልዮኖች የሚቆጠር የሕዝብ ገንዘብ የተዘረፈበት ነው፡፡ ይህንንም÷ በምእመናን ተሟጋች ቡድን፣ በጠቅላይ ቤተ ክህነቱ የቁጥጥር አገልግሎትና በቋሚ ሲኖዶሱ የተሠየመው ልኡክ በተለያየ ጊዜ ያካሔዱት ተደጋጋሚ ማጣራት በጉልሕ ያስረዳል፡፡

ቋሚ ሲኖዶሱ በእኒኽ ተደጋጋሚና ተደጋጋፊ ሪፖርቶች ላይ በመመርኮዝ የሕንፃ ግንባታው ጥራትና ሒሳብ በብቁና ገለልተኛ ባለሞያ እንዲመረመር መስከረም ፱ ቀን ፳፻፮ ዓ.ም. ውሳኔ አስተላልፏል፡፡ ውሳኔው ተፈጻሚ እንዲኾን የሀ/ስብከቱ ሊቀ ጳጳስ ለደብሩ አስተዳደር መመሪያ ሰጥተዋል፡፡ በዚኽም መሠረት ምርምራ የሚያከናውነውን ድርጅት በውድድር ለመለየት ግልጽ ጨረታ ወጥቷል፡፡

ይኹንና የሕንፃ አሠሪ ኮሚቴውን ከሰበካ ጉባኤውና ከሀ/ስብከቱ ቁጥጥር ውጭ በማድረግና ከጠቅላይ ቤተ ክህነቱ የምሕንድስና ዘርፍ ጋራ በመመሣጠር ምእመናን በገንዘብና በዐይነት ለግንባታው የሚያበረከቱትን አስተዋፅኦ ለግል ጥቅሙ ሲያካብት የቆየው ሊቀ መንበሩ ብርሃኔ መሐሪ፣ ምርመራው እስከ ግንባታው ፍጻሜ እንዲዘገይ የሚያዝ ደብዳቤ ከፓትርያርኩ ልዩ ጽ/ቤት በማጻፍ ሒደቱን ለማስተጓጎል ሙከራ አድርጓል፡፡

የቋሚ ሲኖዶሱን ውሳኔ የሚፃረረውን የፓትርያርኩን ልዩ ጽ/ቤት ትእዛዝ ያልተቀበሉት የሀ/ስብከቱ ሊቀ ጳጳስ የቅድመ ምርመራው ዝግጅት እንዲቀጥል መመሪያ በመስጠታቸው ግልጽ ጨረታ ወጥቶ የጨረታው ሰነዶች እየተሸጡ ባለበት ኹኔታ፣ መዝባሪው ብርሃኔ መሐሪ ለኹለተኛ ጊዜ ወደ ፓትርያርኩ ልዩ ጽ/ቤት በመሔድና የተለመደውን ኔትወርኩን በመጠቀም ምርመራው እስከ ግንባታ ፍጻሜው ድረስ እንዲዘገይ አስቀድሞ የተላለፈው ትእዛዝ እንደጸና መኾኑን የሚያሳስብ ሌላ የትእዛዝ ደብዳቤ ዳግመኛ በማጻፍ በፋክስ ለድሬዳዋ ሀ/ስብከት ጽ/ቤት እንዲደርስ አድርጓል፡፡

ከትላንት በስቲያ ምሽት ለሀ/ስብከቱ ጽ/ቤት የደረሰው የፓትርያርኩ ልዩ ጽ/ቤት ደብዳቤ ምርመራው እንዲዘገይ ማዘዝ ብቻ ሳይኾን ሌላም አስደንጋጭም አሳዛኝም ይዘት አለው – ‹‹ፓትርያርኩ በሰጡት መመሪያ መሠረት›› በሚል በልዩ ጽ/ቤቱ የበላይ ሓላፊና በቀድሞው የሀ/ስብከቱ ሊቀ ጳጳስ ብፁዕ አቡነ ገሪማ ፊርማ የወጣው ደብዳቤው፣ በሕንፃ አሠሪ ኮሚቴው ላይ የኦዲት ምርመራ ግኝቶች የሚያረጋግጡትን ደንብና አሠራር የጣሰ ክፍያ በመካድ ‹የድንቢጧን ምስክርነት› ለመስጠት የደፈረ ኾኖ ተገኝቷል፡፡

ነሐሴ ፳፮ ቀን ፳፻፫ ዓ.ም. የጠቅላይ ቤተ ክህነቱ የኦዲት ምርመራ ቡድን ባቀረበው ባለ47 ገጽ ሪፖርት ግንባታውን ለማጠናቀቅ በውሉ ከተገለጸው 2‚984‚562.51 ሌላ 1‚864‚372.33 ተጨማሪ ገንዘብ ለኮንትራክተሩ ውጭ ኾኖ መከፈሉን ያረጋገጠውና በወቅቱ ብፁዕ ዋና ሥራ አስኪያጅ አቡነ ፊልጶስ የአፈጻጸም ማስተካከያና የቅርብ ክትትል እንዲደረግበት ለሀ/ስብከቱና ለሰበካ ጉባኤው መመሪያ የተሰጠበት የኦዲት ግኝት ልዩ ጽ/ቤቱ ‹‹ምንም ችግር የለበትም›› በሚል በደብዳቤው ከደመሰሳቸው ሐቆች ተጠቃሹ ነው፡፡

የፓትርያርኩ ልዩ ጽ/ቤት የቋሚ ሲኖዶሱን ውሳኔ በመፃረር ከመዝባሪው ብርሃኔ መሐሪ ጋራ መቆሙን ያረጋገጠበት ይኸው ደብዳቤ በሀ/ስብከቱ አድባራትና በድሬዳዋ አገልጋዮችና ምእመናን ዘንድ መሰማቱን በመንበረ ፓትርያርኩ ላይ ተከትሎ ከፍተኛ ምሬትና ቁጣ መቀስቀሱ ተነግሯል፡፡

ችግሩን በቋሚ ሲኖዶሱ ውሳኔ መሠረት በተጀመረው መንገድ ለመጨረስ የቆረጠው አገልጋዩና ምእመኑ በተለያዩ ጊዜያት የተካሔዱ የኦዲት ምርመራዎችንና የማጣራት ሪፖርቶችን የፓትርያርኩ ልዩ ጽ/ቤት አላግባብ ከጻፋቸው ደብዳቤዎች ጋራ በመያዝ ወደ ከተማው አስተዳደርና የፀረ ሙስና ኮሚሽን ቅርንጫፍ ቢሮዎች ለማምራት መዘጋጀቱ ከስፍራው እየተገለጸ ይገኛል፡፡