“አብርሃ ደስታ: ያልበሰለ ወረኛ!” – አብርሃ ደሳታ
ወደ ዉቅሮ ከተማ ጎራ ብዬ ነበር። የትግራይ ክልል ዕጩ ዳኞችና ዓቃብያን ሕግ የሚሰለጥኑት በዉቅሮ ከተማ ነው። ዳኞቹ ከዩኒቨርስቲዎች በሕግ የተመረቁ ወጣቶች ናቸው። ዳኞችና ዓቃብያን ሕግ ሁነው ለማገልገል ስልጠና ይሰጣቸዋል። ስልጠናው ግን ስለ ዳኝነት ሳይሆን ስለ ህወሓታዊ ፖለቲካና ፕሮፓንጋንዳ ሁኖ ተገኝቷል። የሚሰለጥኑት ስለ ወያናይ ዴሞክራሲ (አብዮታዊ ዴሞክራሲ) ነው፤ ስለ ልማታዊ መንግስት ነው (ልማታዊ መንግስት በኢህአዴጋዊ ቋንቋ ማለት ነው)። አሰልጣኖችም የሕግ ባለሙያዎች ሳይሆኑ የህወሓት የማእከላዊ ኮሚቴ አባላት ናቸው።
ስልጠናው የሚያተኩረው ሰልጣኞቹ በዩኒቨርስቲዎች የተማሩትን የዳኝነት መርህና ስርዓት በአብዮታዊ ዴሞክራሲ ፕሮፓጋንዳ መተካት ላይ ነው። “ከዩኒቨርስቲዎች ያገኛችሁት የሕግ እውቀት የኒዮሊብራል አስተሳሰብ ስለሆነ አያስፈልጋችሁም” ይሏቸዋል። በምዕራባዊ የዳኝነትና የሕግ የበላይነት መርሆች ሰልጥነው ለዜጎች መብትና ነፃነት እንዳይቆሙና እንዳያገለግሉ ለማድረግ የምዕራባውያን ፍልስፍና “ስህተት” እንደሆነና በዩኒቨርስቲ በተማሩት መሰረት ሳይሆን አሁን በህወሓቶች በሚሰለጥኑት ፖለቲካ መሰረት መፍረድና መስራት እንዳለባቸው ይሰለጥናሉ። ስለዚህ ዓላማው ፍትሕ ለመጠምዘዝ ይመስላል።
ሰልጣኞቹ በሚሰለጥኑበት ተቋም የመፃሕፍት ሪፈረንስ (reference) እንደሌለና የሕግ መፃህፍቶችን እንደሚያስፈልጋቸው ሲጠይቁ … ለሰልጣኞቹ የሚሆን ብቸኛና ዋነኛ ሪፈረንስ መፅሐፍ “አዲስ ራእይ” መሆኑና አዲስ ራእይ መፅሓፍ እንደተቀመጠላቸው ሰልጣኞቹ በመገረም አጫውቶውኛል። የሕግ ስልጠና ተብሎ የአዲስ ራእይ ስልጠና እየተሰጣቸው ነው።
በኢትዮጵያ የተቃዋሚ ፓርቲዎች እንደማያስፈልጉም ይነገራቸዋል። ምክንያት ደግሞ “በኢትዮጵያ ያሉ ተቃዋሚ ፓርቲዎች ሕገመንግስታዊ ስርዓቱ በሃይል ለመናድ የሚፍጨረጨሩ ናቸው” የሚል ነው። ተቃዋሚዎች ሕገመንግስቱ ለማጥፋት ነው የሚሰሩ፤ ስለዚህ ፀረ ኢትዮጵያ ናቸው፤ ለኢትዮጵያ ዴሞክራሲ አይበጁም የሚል መልእክት ይተላለፋል። ዓረና ፓርቲ የትግራይ ጠላት እንደሆነ ይሰበካል። ዓረና ፓርቲ “ትግራይን ወደኋላ ለመመለስ የሚታገል ድርጅት” መሆኑና ለትግራይ መጥፎ መሆኑ ይነገራቸዋል።
በስልጠናው አብርሃ ደስታም አጀንዳ ነው። አብርሃ ደስታ “ያልበሰለ ወረኛ” መሆኑና ማንም ወጣት ሊያዳምጠው እንደማይገባ ይነገራቸዋል። አቶ ገብሩ አስራትም “ኪራይ ሰብሳቢ” እንደሆነ ይሰለጥናሉ። ስለ አንድ “ያልበሰለ ወረኛ” በሰልጣኞች ክፍል ዉስጥ መናገር ምን አመጣው? ዕጩ ዳኞቹ ዉቅሮ ከተማ የሚገኙ ስለ አብርሃ ደስታ ያልበሰለ አስተሳሰብ ሊማሩ ነው ወይስ ስለ ዳኝነትና ፍትሕ ሊሰለጥኑ? አብርሃ ደስታ ያልበሰለ ወረኛ ከሆነ በሰልጣኝ ዳኞች ፊት አጀንዳ ማድረጉ ምን አስፈለገ? ወይስ ስላልበሰሉ ወሬዎች መናገር ለዳኝነት ስልጠናው ይጠቅማል ተብሎ ስለታመነ ነው? ዓላማው ግልፅ ነው; ወጣት ዳኞቹ የህዝብ አገልጋዮች ሳይሆኑ የህወሓታዊ ስርዓት አገልጋዮች እንዲሆኑ ለማድረግ ነው።
ለማንኛውም ባልበሰለ ወሬ አትጨነቁ። ሰልጣኞችም የሚመለከታቸውን ስልጠና ስጧቸው። የተማሩ ወጣቶች እስከሆኑ ድረስ በህወሓት ስም የማጥፋት ርካሽ ፖለቲካ የሚሸወዱ አይደሉም። ስለ ፖለቲካ ስታስተምሯቸው የራሳቹ የፖለቲካ ዓቅምና ግንዛቤ ነው የሚታጋልጡ። የተማሩ ወጣቶች ከናንተ በላይ ፖለቲካ ሊያውቁ እንደሚችሉ አስቡ።
ለማንኛውም መልካም የዳኝነት-ወያናይ ፖለቲካ ስልጠና ይሁንላቹ። ሰልጣኞችም በህወሓቶች የፖለቲካ ጅንጀና ሳይሆን በተማራችሁት የአካዳሚክስ የዳኝነት እውቀት መሰረት እንደምትዳኙና ህዝብን እንደምታገለግሉ ተስፋ አደርጋለሁ።