ከመመሪያ ወደ ዐዋጅ ከፍ የተደረገው ‹‹የሃይማኖት ተቋማት ምዝገባና የዕድሳት አገልግሎት›› ረቂቅ በሐዋሳ ለውይይት ይቀርባል
- ከጥር ፴ – የካቲት ፪ ቀን ፳፻፮ ዓ.ም. በሐዋሳ – ሌዊ ሪዞርት በሚካሔደው ውይይት ላይ፣ በፓትርያርኩ የሚመራ ኻያ ያህል የቤተ ክርስቲያናችን ልኡክ ይሳተፋል፤ ልኡኩ በዛሬው ዕለት ከቋሚ ቅዱስ ሲኖዶሱ የሥራ መመሪያ ይቀበላል፡፡
- የዐዋጁን ረቂቅ አስቀድሞ ለመመልከትና የቤተ ክርስቲያናችንን አስተያየትና አቋም ለመወሰን ለፌዴራል ጉዳዮች ሚኒስቴር የቀረበው ጥያቄ አዎንታዊ ምላሽ አላገኘም፡፡
- ‹‹የሃይማኖት ወይም እምነት ተቋማትን ለመመዝገብና የዕድሳት አገልግሎት ለመስጠት›› በሚል በፓርላማው ጸድቆ እንደሚወጣ የተመለከተው ዐዋጅ÷ የእምነት ተቋማትና ከእምነት ጋራ የተሳሰሩ መንግሥታዊ ያልኾኑ አደረጃጀቶች፣ ‹‹ፀረ ሕገ መንግሥታዊ ተግባር ላይ እንዳይሳተፉ ለመከላከልና ተጋላጭ ከሚያደርጉ አሠራሮች እንዲቆጠቡ ለመደገፍ እንዲሁም ሕገ ወጥ የፋይናንስ ዝውውር አካል እንዳይኾኑ ለመጠበቅ ያስችላል›› ተብሏል፡፡
- የ‹‹ኢትዮጵያ የሃይማኖት ተቋማት ጉባኤ›› አባል ከኾኑ የእምነት ተቋማት በተውጣጡ ምሁራን እንደተዘጋጀ እና በአገር አቀፍ ደረጃ በየአብያተ እምነቱ ተግባር ላይ እንደሚውል የተገለጸው፣ የሃይማኖት ተቋማት የሰላም ዕሴት ማሠልጠኛ መመሪያ ረቂቅ የመጨረሻ ይዘት ተገምግሞ እንደሚጸድቅ ይጠበቃል፡፡
- በኢትዮጵያ የሃይማኖት ተቋማት ጉባኤ የምክክር መድረኮች፣ ዐውደ ጥናቶች እና የኅትመት ውጤቶች የሚሳተፉ ልኡኰቻችን አግባብነትና የተሳትፎ ፋይዳ ከሽርሽር ጉዞ፣ ከፖሊቲካ ቅኝትና አድርባይነት ይልቅ የቤተ ክርስቲያናችንን መብቶችና ጥቅሞች በማስጠበቅ ለጋራ ጉዳይ የሚሠራ ስለመኾኑ በጥልቀት መገምገም እንደሚገባው እየተጠየቀ ነው፡፡