ጉራማይሌ ፖለቲካ ክፍል 1 ( ጎንደር እና ጥምቀት) – ተመስገን ደሳለኝ

በምንወዳት ኢትዮጵያችን ከኑሮ እስከ ሮሮ፤ ከማሕበራዊ እስከ ፖለቲካ፤ ከኢኮኖሚ እስከ ትምህርት ፖሊሲ፤ ከመንፈሳዊ እስከ ዓለማዊ… ያሉ ጉዳዮች ጉራማይሌነት ከቀን ወደ ቀን እየጎላ ነው፡፡ በዚህ ፅሁፍም ጥቂት ያህል ማሳያዎችን በአዲስ መስመር እንመለከታለን፡፡

የሁሉም መነሻና መድረሻ ዓላማ መንፈሳዊ ይሁን እንጂ እንደ መስቀል፣ ጥምቀትና ሬቻ… ያሉ አንዳንድ በዓላት ከመንፈሳዊነታቸው በተጨማሪ የባሕል መገለጫ እስከመሆን ደርሰዋል፡፡ ከዚህ የተነሳም በዓላቶቹ በሚከበሩባቸው ቦታዎች የሚገኘው ስፍር ቁጥር የሌለው ሕዝብ፣ ሰማያዊውን ፅድቅ ብቻ ሳይሆን፣ በባህላዊው አከባበርም በእጅጉ ስለሚማርክ ጭምር ነው፡፡

የሆነው ሆኖ በወዳጆቼ ጋባዥነት የዛሬ አስራ አምስት ቀን በጎንደር ከተማ በተከበረው የጥምቀት በዓል ላይ ተገኝቼ ነበር፤ በወቅቱም የታዘብኩት ጉዳይ ከሺህ ዓመታት በፊት የተፈፀመ አንድ ክስተትን እንዳስታውስ ገፊ-ምክንያት ሆኖኛል፤ ይኸውም በዘመነ ኦሪት የምድረ ባቢሎን ሰዎች አምላካቸውን ከመንበረ ሥልጣኑ ለመገልበጥ አሲረው ወደ ሰማይ የሚያወጣቸውን ታላቅ ግንብ መገንባት የጀመሩ ጊዜ አምላክ በድርጊታቸው ተቆጥቶ ቋንቋቸውን በማደበላለቁ ውጥናቸው በአጭር እንደተቀጨባቸው በመፅሀፉ የተተረከ ነው፡፡ …እነሆም ይህ በሆነ ከሺህ ዓመታት በኋላም የጎንደር ሕዝብ እና መንግስት በአንድ አደባባይ፣ በአንድ ድግስ ላይ ከመቼውም ጊዜ የበለጠ የመግባባት መንፈስ ርቆባቸው፣ ጉራማይሌነታቸው ደምቆ አስተውያለሁ፡፡

እንደሚታወቀው ኢህአዴግ መራሹ-መንግስት ከበረሃ ‹የብሔር ፖለቲካ› የተሰኘ መርዝ ቀምሞ መምጣቱ ሳያንስ፣ አረንጓዴ፣ ቢጫ፣ ቀይ ሰንደቃችን (ባንዲራችን) ላይም ኮከብ ይሉት ዲሪቶ ለጥፎ ‹ጨው ቢጠቀለልበት፣ ስኳር ቢቋጠርበት… ምንድን ነው? ያው ጨርቅ ነው!› ማለቱ ብዙሃኑን ኢትዮጵያዊ እጅግ አስቆጥቶት ነበር፡፡ በነዚህና መሰል ድርጊቶቹም የተነሳ ግንባሩ በሀገር ጉዳይ ላይ ዛሬም ድረስ መናፍቅ ተደርጎ ተቆጥሯል፤ ደግሞም ነው! ምክንያቱም ያቺ ልባችንን በደስታ የምትሞላው ባንዲራ እስከ ደርግ ውድቀት ጧትና ማታ በክብር ስትሰቀልና በክብር ስትወርድ ነው የኖረችው፡፡ ያን ጊዜ በየመንገዱ መኪና ውስጥ ያለው ከመኪናው ወርዶ፣ እግረኛውም የደረሰበት ቦታ ላይ ቀጥ ብሎ ቆሞ፣ ጠዋት ከፍ አድርጎ ሲያውለበልባት፣ አመሻሻ ላይ ደግሞ በዝማሬ አውርዶ በክብር አጣጥፎ ሲያስቀምጣት ማየት በእውነቱ ልብን በከፍተኛ ሃሴት ይሞላ እንደነበር አይዘነጋም፡፡

ግና! ዛሬ ዘመን ተቀይሮ፣ ታሪክ ተሽሮ ስንት የደም መስዋዕትነት የተከፈለባት ውድ ባንዲራችን በተሰቀለችበት ዞር ብሎ የሚያያት ጠፍቶ ተበጫጭቃ ሰርግ ቤት የተጎዘጎዘ ወረቀት መስላ መታየቷ በቁጭት አንገብግቦ፣ በሀዘን ልብ ይሰብራል፡፡ እናም ብዙሃኑ ባንዲራ የሚያውለበልብበት አጋጣሚ በተፈጠረ ቁጥር ከፍ የሚያደርጋት ያችኑ ንፅኋን (የድሮዋን) ሰንደቅ ሆኖ ዘልቋል፡፡ ይሁንና ካለፉት ጥቂት ዓመታት ወዲህ ድንገት ከእንቅልፉ የባነነው ኢህአዴግ በየትኛውም ጊዜና ቦታ ሁሉ መውለብለብ ያለበት ኮከብ የታተመበት ባንዲራ ብቻ እንዲሆን በአዋጅ እስከመደንገግ ደርሷል፡፡ ይህንንም አዋጅ ተከትሎ በተለይም አዲስ አበባን ጨምሮ በዋና ዋና ከተሞች ባንዲራን በተመለከተ ጠበቅ ያለ ቁጥጥር ሲያደርግ ተስተውሏል፡፡

ሰሞኑን በጎንደር ከተማ ያያሁት ግን የዚህን ተቃራኒ ነው፤ ባንዲራችን የባህላዊም ሆነ ኃይማኖታዊ በዓላት ዋነኛ አድማቂ መሆኗ ነባር ልማድ ነው፤ እናም ጎንደር ላይ ዘንድሮ የጥምቀት በዓል በተከበረበት ወቅት በታቦታቱ ዙሪያ በተለያየ መልኩ የተዘጋጀውም ሆነ ሕዝቡ ያነገበው ሰንደቅ፣ አገዛዙ ‹‹ከዚህ ውጪ…›› ብሎ ለእስር እንደሚዳርግ በአዋጅ የለፈፈለትን ባለ ኮከቡን አይደለም፤ ይልቁንም በብዙሃኑ የሀገሬ ሕዝብ ልብ ላይ የታተመችውን ያችን ንፁህ አረንጓዴ፣ ቢጫ፣ ቀይ ባንዲራ ብቻ ነበር፡፡ …ኩነቱም የፓርቲ ‹ፖለቲካዊ ፍቺ› ሰጥቶ ሰንደቁን ላዥጎረጎረው ኢህአዴግ ‹‹እመራዋለሁ›› ከሚለው ሕዝብ ያለውን ዕርቀት አመላካች ሆኖ አልፏል፡፡

ሌላው የዕለቱ ጉራማይሌ ክስተት በተለያየ ቅርፅ የተሰሩ፣ የኢትዮጵያን መልከዓ-ምድር የሚያሳዩ ሶስት ግዙፍ ካርታዎች በመኪኖች ላይ ተጭነው ለዕይታ አደባባይ መቅረባቸው ነው፤ እነዚህ ካርታዎች የሚያመላክቱት የሀገራችን ሰሜናዊ ድንበር መለስ ዜናዊ እና ጓደኞቹ ትግራይ ላይ ተገድቦ እንዲቀር ከሻዕቢያ ጋር የተዋዋሉበትን አይደለም፤ ስመ-ጥሩው ጀግና አሉላ አባነጋ ጦሩን ሰብቆ ‹ቼ ፈረሴ› ብሎ እስከጋለበበት ቀይ ባህር ድረስ የሚዘረጋውን የቀድሞውን የኢትዮጵያ ይዞታ ያካተተ እንጂ፡፡

ይህ መሳጭ ትዕይንትም ሕዝብና መንግስት ያለፉትን ሃያ ሁለት ዓመታት መደማመጥ የማይችሉ (ቋንቋቸው የተደበላለቀባቸው) ሆነው እዚህ እንደደረሱ ማሳያ ተደርጎ ሊወሰድ ይችላል፡፡ ለዚህ አይነቱ ጉራማይሌ ግንኙነት ገፊ-ምክንያት ደግሞ የጎንደር ሕዝብ ሕገ-ወጥ በመሆኑ አልነበረም፤ ገዥው ፓርቲ ይቺን ሀገር ለመመስረት እልፍ አእላፍ ቀደምት አባቶች የሞቱላትን፣ ታሪክ የተሰራባትን ባንዲራ በማን ጋዜጠኛ ተመስገን ደሳለኝ አህሎኝነት ያሻውን የለጠፈባት ከመሆኑም በላይ የኢትዮጵያን ጥቅም ያላስከበረ የሀገር ግንጠላ ላይ መሳተፉ የፈጠረው ቁጭት ነው፡፡…መቼም የዕለቱን ኩነት ቋራ ሆቴል በረንዳ ላይ ከእኛ በጥቂት ሜትሮች ዕርቀት ተቀምጦ ቁልቁል ሲከታተል የነበረው በረከት ስምዖንየተጠናወተው የእብሪት ፖለቲካ አይነ-ልቦናውን ካልጋረደበት በቀር ይህ ጉዳይ የሚያስተላልፍለት አንዳች አገራዊ ምስጢር ያለው መሆኑ አይጠፋውም፡፡