ጉራማይሌ ፖለቲካ ክፍል 3 (አያሌው ጎበዜና ባሕር ዳር) – ተመስገን ደሳለኝ

አቶ አያሌው ጎበዜ ድርጅቱን የተቀላቀለው አስተማሪ ሆኖ እየሰራ በነበረበት አዲስ ዘመን ከተማ በ1984 ዓ.ም ቢሆንም በተፋጠነ ሂደት የሽግግር መንግስቱ የስራ አስፈፃሚ አባል መሆን ችሎ ነበር፤ ከ1987-1992 ዓ.ም የክልሉ አስተዳዳሪ አዲሱ ለገሰ ምክትል ሆኖ ተሹሟል፤ በዮሴፍ ረታ የአስተዳደር ዘመን (ከ1992-97 ዓ.ም) ደግሞ መጀመሪያ የክልሉ ገንዘብና ኢኮኖሚ ኃላፊ፣ ቀጥሎ አፈ-ጉባኤ ሆኖ ሰርቷል፡፡

ይሁንና በምርጫ 97 ዮሴፍ በተወዳደረበት ሰሜን ሸዋ በቅንጅት እጩ ሲሸነፍ፣ አያሌው ደግሞ በማርቆስ ከተማ በባሶ ሊበን ወረዳ ሊያሸንፍ ችሏል (አሸናፊነቱ ምንም እንኳ እንደ ሌሎቹ የኢህአዴግ ተወዳዳሪዎች በድርጅታዊ የድምፅ ስርቆት የተገኘ ቢሆንም) ከ1998 ዓ.ም አንስቶ እስከያዝነው አመት መጀመሪያ ወራት ድረስ የክልሉ ፕሬዚዳንት ሆኖ የቆየው አያሌው ጎበዜ ‹‹ለሱዳን ተሰጠ›› ወይም ‹‹ሊሰጥ ነው›› ከተባለ መሬት ጋር ተያይዞ የማጀገኑና የማንፃቱ ቅስቀሳ የኑፋቄን መንገድ የተከተለ ይመስለኛል (የጉዳዩ ስሁትነት የኛይቷን ‹ፋክት› መፅሄትንም ይጨምራል) በደፈናው ከዚህ ቀደም ‹አያሌው ለሱዳን በሚሰጥ መሬት ላይ አልፈርምም በማለቱ፣ ደመቀ መኮንን ፈረመ› የሚባል ምንጩ የማይታወቅ ወሬ ሁላችንም ጋ ደርሶ እንደነበረ ይታወሳል፡፡

ይሁንና ከብአዴን የመረጃ ምንጮቼ እንዳረጋገጥኩት፣ አያሌው ያውም ርህራሄ አልባ የነበረውን የጉልበታሙ ጠቅላይ ሚንስትር መለስ ዜናዊን ውሳኔ ተቃውሞ ‹ፈርም›፣ ‹አልፈርምም› አይነት አንጃ ግራንጃ የሚፈጥር ደፋር ልብ ያሌለው መሆኑን ነው፡፡

በግልባጩ ፖለቲካችን ጉራማይሌ ነውና ለብአዴን ፍቅር በሌላት ባሕር ዳር አያሌው ተወዳጅ እንደሆነ ይነገራል፤ ይህ የተወዳጅነቱ ሚስጥር ግን ከድርጅቱ ይልቅ ‹‹መረጠኝ›› ለሚለው ሕዝብ ታማኝ በመሆኑ እና በሀገር ጥቅም ከእነ ‹ኦቦ› አዲሱ ለገሰ ተሽሎ ሳይሆን፣ ከራሱ የግል ባህሪና ሰብዕና ጋር ስለሚያያዝ ነው፤ ይኸውም በመኖሪያ ቤቱ አካባቢ ካሉ ነዋሪዎች እና አብረውት ከሚሰሩ የበታች ሰራተኞች ጋር የመሰረተው ማሕበራዊ ግንኙነት ዋነኛው ነው፤ በርግጥም የሚያውቀውም ሆነ የማያውቀው ሰው ሲሞት ቀብር ላይ ይገኛል፤ ማታም እዝን ይዞ በመሄድ ሲያፅናና ያመሻል፤ ሰርግን በመሳሰሉ የደስታ ዝግጅቶችም ላይ እንዲሁ ይሳተፋል፤ እነበረከት ስምዖን ለሚያቀነቅኑት ግራ ዘመም ፖለቲካም ሩቅ በመሆኑ፣ እጅግ መንፈሳዊ የሆነ ባህሪይ ይስተዋልበታል፤ ለአብነት እምነቱ የሚያዝዘውን (ከመፆም ጀምሮ በቤተ-ክርስቲያን ተገኝቶ እስከ ማስቀደስ ያሉ ጉዳዮችን) እንደ ባለሥልጣን ግብዝ ሳይሆን እንደ ማንኛውም ተራ አማኝ ዕለት ተዕለት ሲፈፅም ይታያል፡፡ በቤተሰብ አስተዳደርም ቢሆን አራት ልጆቹን መንግስት ትምህርት ቤት ከማስተማር አልፎ በኢትዮጵያዊ ጨዋ ስነ-ምግባር ማሳደጉን፣ ብልሹ አድርገው ልጆቻቸውን እያሳደጉ ካሉ ከአንዳንድ ኃላፊነት ከማይሰማቸው ባለሥልጣናት ጋር አነፃፅረው የሚያመሰግኑት የድርጅቱ የቅርብ ሰዎች አጋጥመውኛል፤ ከጥቂት ወራት በፊት በህክምና በማዕረግ የተመረቀችውን ብቸኛና የመጀመሪያ ሴት ልጁንም እንደ ምሳሌ ይጠቅሳሉ፡፡

በአናቱም የትኛውም ባለ ጉዳይ ቢሮው ሲመጣ ያለ ቢሮክራሲ ማስተናገዱም ሆነ ለሚቀርብለት አቤቱታም ጥያቄ ‹አይሆንም› አለማለቱን እንደ በጎ ተግባር የቆጠሩለት ሰዎች ለሰውየው ገፅታ ግንባታ የራሳቸውን ሚና ተጫውተዋል፡፡ በተቀረ ኢህአዴግ እንደ አሰባሰባቸው በርካታ ባለስልጣናት እርሱም አለቆቹን አብዝቶ የሚፈራ ሽቁጥቁጥ ሰው መሆኑን በቅርብ የሚያውቁት ይናገራሉ፡፡ በተለይም የብአዴን ካድሬዎች ‹‹ሽማግሌው›› እያሉ በሹክሹክታ የሚጠሩትን አዲሱ ለገሰን እና ሞገደኛውን በረከት ስምዖንን የ‹መለአኩ ገብርኤል› ያህል እንደሚፈራቸው ሰምቻለሁ፡፡

ይህ ፍራቻውም በፍትሕ እና በሙስና ቢሮዎች አካባቢ ከብቃት ይልቅ ‹‹የራሴ›› የሚላቸውን የትውልድ መንደሩን ሰዎች በመሾሙ ‹‹እመራዋለሁ›› የሚለውን ሕዝብ ለከፋ ብሶትና መከራ አጋልጦ ነው ከሥልጣኑ የተሰናበተው፡፡ ይህም ሆኖ ከኃላፊነቱ ለመልቀቅ ጥያቄ ካቀረበ ከአንድ አመት በኋላ ነው ፓርቲው ያፃደቀለት፤ ያለፈውን ሙሉ ዓመትም በቢሮው ከመገኘቱ እና በትላልቅ ጉዳዮች ላይ ከመሳተፉ ባለፈ፣ ሁሉንም ሥራ ሲሰራ የነበረው ዛሬ በምትኩ የተሾመው የዋድላ ደላንታው ገዱ አንዳርጋቸው ነው፤ ገዱ ድርጅቱን የተቀላቀለው ከአያሌው አንድ ዓመት ቀደም ብሎ ዋድላ ደላንታን ኢህአዴግ ከደርግ መዳፍ በኃይል ነጥቆ በወሰደበት ወቅት ነበር፤ ያን ጊዜ የገበሬ ማሕበር ሕብረት ሱቅ ሠራተኛ የነበረው ገዱ ዛሬ የክልሉ ፕሬዚዳንት ለመሆን ችሏል፤ በርግጥ ይህ ሰው ጠንካራ ሠራተኛ እና የበላይአመራሮችን ተጋፋጭ እንደሆነ ይነገርለታል፤ እንዲሁም እንደ አያሌው ከሙስና ጋር ብዙም ንክኪ የለውም (በነገራችን ላይ የብአዴን ዋነኛአመራሮች ለሙስና ሩቅ እንደሆኑ በወሬ ደረጃ ይሰማል፤ ግና! ይህንን እንደምን ማመን ይቻላል? …በርግጥ በክልሉ በተዘዋዋሪ መንገድ የጀነራል አበባው ታደሰ ነው ከሚባለው ባለ አራት ፎቁ ‹‹አልዋቅ›› ሆቴል ሌላ በወሬ ደረጃ የአመራር አባላቱ ንብረት የሆነ አላጋጠመኝም፤ ነገር ግን እኔን አላጋጠመኝም ማለት ሰዎቹ ንፁሃን ናቸው እንደ ማለት አይደለም)

የሆነው ሆኖ ብአዴን በበረከት ስምዖን፣ በአዲሱ ለገሰ፣ በካሳ ተክለብርሃን፣ በታደሰ ጥንቅሹ እና በከበደ ጫኔ ስም የመሰረተው ‹‹ጥረት›› የተሰኘው ኮርፕሬሽን ዳሽን ቢራ፣ ጥቁር አባይ ትራንስፖርት፣ ዘለቀ እርሻ፣ አምባሰል አስመጪና ላኪ፣ ጣና ሞባይል እና ጣና ፍሎራ የተሰኙ የንግድ ድርጅቶችን ያስተዳድራል፡፡ ከእነዚህም ውስጥ አትራፊ የሚባለው ዳሽን 49 ፐርሰንቱን እንግሊዝ አገር ለሚገኝ አንድ ቢራ አምራች ድርጅት ሲሸጥ፤ ጣና ሞባይልም በአሜሪካን ሀገር የታወቀው የሶፍት ዌር ኢንጂነር ባለሙያው ወልደሉዑል ካሳን ጨምሮ ለአራት ሰዎች የአክሲዮን ድርሻን አስተላልፏል፡፡ ይህ ሁኔታም ድርጅቶቹ ትርፍና ኪሳራቸውን በውጪ ኦዲተር እንዲያስመረምሩ የሚያስገድድ መደላድል ፈጥሮላቸዋል፡፡ በርግጥም እንዲህ አይነቱ አሰራር የእነ አዜብ መስፍን መቀለጃ ከሆነው ‹‹ኤፈርት›› በተሻለ መልኩ ለዘረፋ እንዳይጋለጥ መታደጉ አከራካሪ አይደለም፡፡ ምክንያቱም እንግሊዛዊው ድርጅት የዳሽን ቢራ 49 ፐርሰንት ድርሻን ገዝቶ ሲያበቃ፣ ወጪና ገቢውን አይከታተልም ማለቱ ሩቅ ነውና፡፡

በትግራይ ሕዝብ ስም እየነገደ፣ ለህወሓት አመራር አባላትና ቤተሰቦች ብቻ መምነሽነሺያ የሆነው ‹‹ኤፈርት››ም በእንዲህ አይነት መልኩ ለውጭ ድርጅቶች ድርሻ እንዲሸጥ ካልተገደደ በቀር ለቁጥጥር አስቸጋሪ ሆኖ መቀጠሉ ሳይታለም የተፈታ እውነታ ነው፤ ይህ ሁኔታም የፖለቲካ ሥልጣን የጨበጠ ሁሉ የቻለውን የሚዘግንለት ከመሆን የሚተርፍበትን እድል ያመቻችለታል (በነገራችን ላይ እንደሚወራው የብአዴን አመራሮች ወደ ሙስና አለመግባታቸው እውነት ከሆነ፣ ምክንያቱ ጠፍጥፎ የሰራቸውን ህወሓት በመፍራት ብቻ ነው ሊሆን የሚችለው፡፡ በግልባጩ ህወሓት በኢትዮጵያ ሰማይ ስር የሚፈራው የለምና እንዲህ እንደቀለደ በሚቀጥለው ወር የተመሰረተበትን 39 ዓመት ለማክበር ሽር-ጉዱን ከወዲሁ ተያይዞታል)

ሌላው የብአዴን አመራሮች አስገራሚ ታሪክ ከዋነኞቹ መካከል ታምራት ላይኔ፣ በረከት ስምዖን፣ አዲሱ ለገሰ፣ ሕላዊ ዮሴፍን… የመሳሰሉት የትዳር አጋራቸውን ያጩላቸው አንዲት ሴት መሆናቸው ነው፡፡ እኚህ የዋግ ኡምራ ተወላጅ በታጋዮች ዘንድ ‹‹ማዘር›› እየተባሉ ሲጠሩ፣ ኢህአዴግ ውስጥ ባሉ አንዳንድ አሽሟጣጮች ደግሞ ‹‹ጣይቱ›› በሚል ቅፅል ስም ይታወቃሉ፤ ይህ ስያሜ የአጼ ምንሊክ ባለቤት የነበሩት እቴጌ ጣይቱ ታላላቅ መኳንቶችን እየመረጡ ከቅርብ ዘመዶቻቸው ጋር ያጋቡ ነበር ከሚለው ትርክት የሚነሳ ነው፡፡ የሆነው ሆኖ ይህንን ኩነት ጉራማይሌ የሚያደርገው የ1993ቱን የህወሓት ክፍፍል ተከትሎ የብአዴን መሪዎች ‹‹ቦና-ፓርቲዝም››ን በአደባባይ ሲያወግዙና ሲተቹ መስማታችን ነው፡፡

(ቀሪውን ጉራማይሌ የፖለቲካ ወጋችንን በሚቀጥለው ሳምንት እመለስበታለሁ)