ጥንታዊው የደብረ ብሥራት አቡነ ዜና ማርቆስ ገዳም ተፈታ

  • ገዳሙ ጨርሶ ሳይጠፋ ጉዳያቸው በቅዱስ ሲኖዶሱ እንዲታይ መናንያኑ ጠይቀዋል
  • በገዳሙ ህልውና ላይ የተጋረጠው አደጋ በሀ/ስብከቱ የተንሰራፋው ችግር የከፋ መገለጫ ነው

(አዲስ አድማስ፤ ጥር ፳፬ ቀን ፳፻፮ ዓ.ም.)

በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን የሰሜን ሸዋ ሀ/ስብከት ሞረትና ጅሩ ወረዳ የሚገኘው የመካከለኛው መቶ ክፍለ ዘመን የደብረ ብሥራት አቡነ ዜና ማርቆስ አንድነት ገዳም ተፈትቶ፣ መናንያኑና መነኰሳቱ መበተናቸውን ምንጮች ለአዲስ አድማስ ገለጹ፡፡

ጥንታዊውን ገዳም ለመፈታት፣ ማኅበረ መነኰሳቱንም ለመበተን ያበቃቸው፣ በአካባቢ ተወላጅነት የገዳሙን መሬት በተለያዩ ጊዜያት ተቆጣጥረው ለግላቸው ይጠቀሙ ከነበሩ ግለሰቦች ጋር ተፈጥሮ የቆየውና በተለያዩ ምክንያቶች እየተካረረ የመጣው አለመግባባት መኾኑን ምንጮቹ ተናግረዋል፡፡

በኅዳር ወር 2006 ዓ.ም መጀመሪያ ላይ ገዳሙን ለቀው የወጡት በቁጥር ከ50 – 80 የሚገመቱ መናንያኑ ከተለያዩ አህጉረ ስብከትና ክልሎች የተሰባሰቡና በጸሎት ተወስነው የራስ አገዝ ልማት እያለሙ በአንድነት የኖሩ መነኰሳትና መነኰሳዪያት ሲኾኑ በሀገረ ስብከቱ ውሳኔ ከአስተዳዳሪነት የተነሡትን አበምኔቱን መ/ር አባ ተክለ ብርሃን ሰሎሞንን ጨምሮ ከፊሎቹ በአሁኑ ወቅት በደነባ በኣታ ለማርያም ገዳም ተጠልለው እንደሚገኙ ተገልጿል፡፡

የሀገረ ስብከቱ ሊቀ ጳጳስ፣ የወረዳው መንግሥታዊ አስተዳደር፣ ከእነዋሪና ደነባ ከተሞች የተውጣጡ የሀገር ሽማግሌዎች ገዳማውያኑንና ግለሰቦቹን በተለያየ ጊዜ በማገናኘት ለአለመግባባቱ የመፍትሔ ሐሳብ ሲሰጡና ውሳኔ ሲያሳልፉ እንደቆዩ ያስታወሱት መነኰሳቱ፤ ‹‹ተሰዳጅና መጤ›› ከሚል በቀር ግለሰቦቹ በገዳሙ አበምኔትና በመናንያኑ ላይ የሚያቀርቧቸው ክሦች መሠረተ ቢስ መኾናቸው ተረጋግጧል ብለዋል፡፡

የገዳሙን ሥርዐተ ማኅበር በመጣስ የመሬት ይዞታውን፣ ቅርሱንና የልማት ቦታውን ለመከፋፈል የሚሹ ግለሰቦች በሥነ ምግባር ጉድለት ከማኅበሩ ከተወገዱ የስም መናንያን ጋራ በማበር ያቀረቡትን አቤቱታ ብቻ በመቀበል በፓትርያርክ የሚሾሙት አበምኔት፤ በሀ/ስብከቱ አስተዳደር ጉባኤ ውሳኔ ከሓላፊነት መነሣታቸውን ያስረዱት ማኅበረ መነኰሳቱ፣ አንዳንድ የሀ/ስብከቱን ሓላፊዎች በስም በመጥቀስ ለችግሩ መባባስ ተጠያቂ አድርገዋቸዋል፡፡

ማኅበረ መነኰሳቱ እንደሚገልጹት ከሓላፊነት የተነሡት የገዳሙ አስተዳዳሪ÷ የገዳሙን መሬት ይዘውና ጋብቻ መሥርተው ከገዳማውያኑ ጋራ ተቀላቅለው ይኖሩ የነበሩት የአካባቢው አርሶ አደሮች ትክ መሬት አግኝተውና ካሳ ተሰጥቷቸው ከገዳሙ ክልል እንዲወጡ በማድረግ የገዳሙን ይዞታና ሥርዐተ ማኅበሩን በሕግ አስከብረዋል፤ ገዳሙንና ገዳማውያኑን ከሰብአ ዓለም ለይቶ በአግባቡ በማስተዳደር ጣልቃ ገብ ድርጊታቸውን ተከላክለዋል፤ በግብርናና በሽመና ሥራዎች፣ በንዋያተ ቅድሳት ማከፋፈያ፣ በሙዓለ ሕፃናትና በኪራይ ቤቶች ግንባታ የራስ አገዝ ልማትን በማስፋፋት መስቀል ልመናን አስቀርተዋል፡፡

ሀገረ ስብከቱ አበምኔቱን ከሓላፊነት ያነሣበት ውሳኔ የገዳሙን መተዳደርያ ደንብ የሚጥስ ከመኾኑም በላይ ከጥቅመኝነት፣ ጥንቆላና ኑፋቄ ጋራ ተያይዞ በሀ/ስብከቱ ሌሎች አብያተ ክርስቲያናት ላይ የተንሰራፋው የመልካም አስተዳደር ችግር አስከፊ መገለጫ ነው የሚሉት ማኅበረ መነኰሳቱ÷ ሥርዐተ ማኅበራቸውን ጠብቀው በገዳሙ የጀመሩትን መንፈሳዊ፣ ማኅበራዊና ልማታዊ አገልግሎት ለመቀጠል እንዲችሉ፣ የገዳሙ ቅርሶች፣ ቋሚና ተንቀሳቃሽ ንብረቶች እንዲጠበቁ፣ በገዳሙ ያለጧሪ የቀሩ ድኩማን አረጋውያን ደኅንነትም እንዲታሰብበት ቅዱስ ሲኖዶስ አስቸኳይ ውሳኔ እንዲሰጣቸው ጠይቀዋል፡፡

የደብረ ብሥራት ጻድቁ አቡነ ዜና ማርቆስ ገዳም የአቡነ ተክለ ሃይማኖት ደቀ መዝሙር በኾኑት አቡነ ዜና ማርቆስ የተመሠረተ የ፲፪ው መቶ ክፍለ ዘመን ገዳም መኾኑን የታሪክ መዛግብት ያስረዳሉ፡፡

በገዳሙ ታሪክ እንደሚነገረው፣ እስከ 8000 መናንያንን እያስተዳደረ ገዳምነቱን ሳይለቅ በሥርዐተ ማኅበር በቆየው ገዳም፣ ሰበካ ጉባኤ በማቋቋም ወደ ደብርነት እንዲቀየርና በቃለ ዐዋዲ እንዲመራ ለማድረግ ተሞክሮ እንደነበር የገለጹት የዜናው ምንጮች÷ ቅዱስ ሲኖዶሱ፣ የጠቅላይ ቤተ ክህነቱ የገዳማት አስተዳደር መምሪያና የቅርስ ጥበቃ አካላት ኹሉ ከጻድቁ ዐፅም፣ የእጅና የመጾር መስቀሎች ጀምሮ በርካታ ቅርሶች ተጠብቀው የሚገኙበትን የመካከለኛው መቶ ክፍለ ዘመን የሥርዐተ ምንኵስናና የትምህርት ማዕከል ጨርሶ ሳይጠፋ መታደግ እንደሚጠበቅባቸው አሳስበዋል፡፡