አቡጊዳ – አቶ ሌንጮ ለታ በርግጥ አዲስ አበባ ገብተው ይሆን ?

«የቀድሞ የኦነግ አመራር ሌንጮ ለታ፣ አዲስ ፓርቲ ይዘው አዲስ አበባ ገቡ» ሲል አዲስ አድማስ በቅዳሜ ጥር 10 እትሙ ላይ ዘገበ። አቶ ሌንጮን ለማነጋገር ያደረግነዉ ሙከራ እንዳልተሳካለት የዘገበው አዲስ አድማስ ፣ መረጃዎን ያገኘነው ከምንጮቹ እንደሆነም ገልጿል።

አቶ ሌንጮ በጀርመን ድምጽ ራዲዮ በቅርቡ ባደረጉት ቃለ ምልልስ፣ ኢትዮያጵያ ዉስጥ ገብቶ በሰላም ለመታገል ፍልጎቱ እንዳላቸው ገልጸው፣ ከኢሕአዴግ ጋር ምንም አይነት ድርድር እንዳላደረጉ መናገራቸው ይታወቃል። የአዲስ አድማሱ ዘገባ፣ በቀጥታ አቶ ሌንጮ ለጀርመን ድምጽ ራዲዮ ከሰጡት ጋር የሚቃረን ሲሆን፣ ጉዳዩን በትክክል ለማጣራት ያደረግነዉ ሙከራ አልተሳካም። የአቶ ሌንጮ የጀርመኑ ቃለ ምልልስ ወይንም የአዲስ አድማስ ጋዜጣ ዘገባ ትክክል መሆኑ የሚያመላከት መረጃ እንዳገኘን ለአንባቢያ ግልጽ እናደርጋለን።

«ከአንድ አመት በፊት አቶ መለስ ሞተው በነበረ ጊዜ የተለያዩ እርስ በርስ የሚቃረኑ ዘገባዎች አገር ቤት በሚታተሙ ጋዜጦችና በድህረ ገጾች ይወጡ እንደነበረ የሚታወቅ ነዉ። አዲስ አድማስ የተጨበጡ ማስረጃዎች እስካላቀረበ ድረስ፣ አቶ ሌንጮ እራሳቸው በጀርመን ድምጽ የተናገሩትን ለጊዜዉ መቀበሉ ነው የሚያስኬደው» ያሉት አንድ የፖለቲካ ተንታኝ፣ አቶ ሌንጮ በርግጥ አዲስ አበባ ገብተዉ ከሆነ፣ በቅርብ ጊዜ ዉስጥ በቀላሉ እንደሚታወቅ ይናገራሉ። «የኢትዮጵያ ሕዝብ በስፋት በሚያዳምጠዉ የጀርመን ድምጽ ራዲዮ ‘ከኢሕአዴግ ጋር ድርድር አላደረግንም ብለው አቶ ሌንጮ መዋሸታቸውም፣ በድርጅታቸው ላይ ከወዲሁ ጥላሸት እንደቀቡት ነዉ የሚቆጠረዉ» ሲሉ ያከሉት እኝሁ ተንታኝ፣ በአንጻሩም አቶ ሌንጮ ኖርዌይ ሆነው ከሆነ አዲስ አበባ ገቡ የሚባለው፣ የአዲስ አድማስ ጋዜጣ ተአማኒነት ክፉኛ እንደሚጎዳም አስረድተዋል።

አቶ ሌንጮ ለታ የሚመሩት የኦሮሞ ዴሞክራቲክ ግንባር ፣ እንደ ዶር በያን አሴቦ፣ አቶ ሌንጮ ባቲ፣ ዶር ዲማ ነግዎ የመሳሰሉ የኦነግ መስራችን አንጋፋ አመራር አባላት የተመሰረተ እንደሆነ ይታወቃል። ላለፉት ሰላሳ አመታት ኦነግ ወደ ፊት እንዳይሄድና ከተቀረዉ ኢትዮጵያዊ ጋር በቀጥታ እንዲላተም ያደረገዉን፣ የመገንጠል ፖለቲካ ወደ ጎን በመጣል.፣ የኢትዮጵያን አንድነት በመቀበል፣ የኦሮሞ ጥያቄ በዴሞክራሲ መከበር ይፈታል የሚል አቋም በመያዝ ነዉ ኦዴፍ የተመሰረተዉ።

እነ አቶ ሌንጮ ለታ፣ በኢሳያስ አፈወርቂ ከሚመራዉ የኤርትራ መንግስት ጋር በመወዳጀት፣ የትጥቅ ትግል ያደርግ የነበረዉን ኦነግን ትተዉ ፣ ሰላማዊ በሆነ መንገድ ለመታገል መወሰናቸው፣ የኦነግ ዉጤት አልባና ኤርትራ ጥገኛ፣ የሃያ አመታት የትጥቅ ትግል፣ ኦሮሞዉን በስመ ኦነግ ስም ከማስጨረስ ዉጭ ምንም ጠቀሜታ እንዳላመጣለት ከመረዳት ሊሆን እንደሚችል ብዙዎች ይናገራሉ።

የአቶ ሌንጮ የቀድሞ ኦነግ፣ ለአራት የተከፋፈለ ድርጅት መሆኑም ይነግራል። እነርሱም አዲስ አበባ ገባ የሚባለዉ የአቶ ሌንጮ ለታ ኦዴፍ፣ በጄነራል ከማል ገልቹ የሚመራዉና በኢትዮጵያ አንድነት የሚያምነው አስመራ የሚገኘዉ የኦነግ ቡድን፣ በአቶ ዳዎድ ኢብሳ የሚመራዉ ሌላዉ አስመራ የሚገኝ፣ ኦሮሞዉ ሕዝብ ዉሳኔ ያደርግና ይወስን የሚለው ቡድን እና እነ ዶር ነጋሳ ዲልቦ ያሉበት ኦሮሞያ የሚሉትን ለመገንጠል የሚፈልገዉ የአክራሪዉ ኦነግ ቡድን)

አቶ ሌንጮ ከኢሕአዴግ ጋር ድርድር አላደረግንም ያሉበት የጀርመን ድምጽ ራዲዮን ለማዳመጥ እዚህ ይጫኑ !

አዲስ አድማስ ጋዜጣ፣ “አቶ ሌንጮ ደርጅታቸውን ይዘው ገቡ” የሚለውን ዘገባ ለማንበብ እዚህ ይጫኑ !