ነገ ጠዋት ጥምቀትን ሐበሾች በዩጋንዳ በልዩ መንፈሣዊ ስርዓት ያከብሩታል!

ሐበሾቹ ነገ ጠዋት የጌታን ጥምቀት በዩጋንዳ በልዩ መንፈሣዊ ስርዓት ያከብሩታል!!!

መንበረ ፓትርያኩን በሰሜን አሜሪካ ባደርገው በስደት ላይ በሚገኘው ሕጋዊው ቅዱስ ሲኖዶስ የሚመራው የካምፓላ መካነሠላም መድሐንያለም ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተክርስትያን የደብሩ ማሕበረ ካህናትና ማህበረ ምዕመናን በዩጋንዳ ነገ ጠዋት ጥር ዐሥራ ዐንድ ቀን የጌታችን መድሐኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ የጥምቀት በዓልን በከፍተኛ መንፈሣዊ ሥነ ሥርዓት እንደሚያከብሩ ተገለፀ።
ከሠንበት ቅዳሤ በኋላ የመድሃኒያለምና የቅዱስ ሚካዔል ታቦታት በምዕመናን ታጅበው በመሪጌታ ይህይስ ዓለሙ መሪነት ያሬዳዊ ዝማሬ የዕለቱ ምልጣን<ክርስቶስ ተወልደ ክርስቶስ ተጠምቀ ወልደነ ዳግመ እማየ ወእመንፈሠ ቅዱስ እሙነኮነ ለፀሐየ ፅድቅ አስተርዕዮቱ አማን መንክር ስብሐተ ጥምቀቱ > የሚቀርብ ሲሆን የደብሩ ማሕበረ ካህናት ከማህበረ ምዕመናን ጋር ፈጣሪ አምላካቸውን በያሬዳዊ ዜማ ያመሠግናሉ። ጥምቀተ ባሕሩም ይባርካል።
አስተማማኝ የፖሊስ ጥበቃ ስለሚደረግ ምዕመናን መኪናቸውን ደብሩ ባዘጋጀው የማቆሚያ ስፍራ በማድረግ ያለስጋት በዓሉን እንዲያከብሩ የቤተክርስትያኒቱ አስተዳደር ጽ /ቤት መልዕክቱን አስተላልፏል።
ሐበሾቹ ኢትዮጵያዊያንና ኤርትራዊያን በካምፓላ መካነሠላም መድሐንያለም የኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተክርስትያን በዩጋንዳ በጋራ በመሆን ፈጣሪያቸውን በተለይ ዘወትር ዕሁድ እንደሚያመሠግኑ ይታወቃል።አባ ኃይለማርያም በአሉን በማስመልከት የወንጌል ማዕድ የሚያቀርቡ ሲሆን የደብሩ አስተዳዳሪ ቀሲስ ፀሐይ ደስታ በበበዓሉ ፍፃሜ ላይ ቃለ ምዕዳን እንደሚያቀርቡ ይጠበቃል።

የካምፓላ መካነሠላም መድሐንያለም ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተክርስትያን ማህበረ ካህናትና የደብሩ አስተዳደር ጽ /ቤት ለመላ የኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ዕምነት ተከታዮች እንኳን ለብርሐነ ጥምቀቱ አደረሣችሁ እያሉ መልካም ምኞታቸውን እንዳስተላለፉ የዚህ ዜና ዘጋቢ ጨምሮ ገልጿል።
አክሊለ ሠማዕት
penEthiopian