የአ/አበባ ሰንበት ት/ቤቶች ወጣቶች ሙስናና ብልሹ አስተዳደርን ለማረም የፓትርያርኩን ትእዛዝ በተጠንቀቅ ቆመው በመጠባበቅ እንዳሉና በታዘዙበት መሥመር ለመሰለፍ ዝግጁ መኾናቸውን ገለጹ

 

Sunday school Timket Mezemeran

  • የቤተ ክርስቲያን ዘርፈ ብዙ ችግር ለማረም በሚደረገው ጥረት ኹሉ በግንባር ቀደምነት መሰለፍ የእኛም የወላጆቻችንም ጽኑ አቋም ነው፡፡
  • አያሌ የሰንበት ት/ቤት ወጣቶች ሙስናና ብልሹ አስተዳደርን እስከ መታሰር ደርሰው እየታገሉት ነው፡፡
  • ፓትርያርኩ ሙስናና ብልሹ አስተዳደርን ለማረም የሚያደርጉት ጥረት ታሪክ የሚዘግበውና መዘገብም ያለበት እውነት ነው፡፡
  • ሰንበት ት/ቤቶች የጨቅላ አእምሮዎችና የሥራ ፈቶች መጠራቀሚያ ሳይኾን ካህናትና ዲያቆናት፣ የሥነ መለኰት ምሁራን፣ ኢንጅነሮች፣ ዶክተሮች፣ አካውንታንቶች፣ የሕግ ባለሞያዎችና የትምህርት ባለሞያዎች በአጠቃላይ እምነት የሚጣልባቸው የቤተ ክርስቲያን ልጆች ያሉበት ኹለገብ ተቋም ነው፡፡

*                              *                            *

በስመ አብ ወወልድ ወመንፈስ ቅዱስ አሐዱ አምላክ አሜን

 

ለብፁዕ ወቅዱስ አቡነ ማትያስ ቀዳማዊ ፓትርያርክ

ርእሰ ሊቃነ ጳጳሳት ዘኢትዮጵያ ሊቀ ጳጳስ ዘአክሱም

ወዕጨጌ ዘመንበረ ተክለ ሃይማኖት

አዲስ አበባ 

የቅዱስነትዎ የአባትነት ቡራኬ ይድረሰን እያልን እኛ የአዲስ አበባ ሀገረ ስብከት የሰንበት ት/ቤት አመራሮችና አባላት ኹላችንም ከኹሉ አስቀድመን የልጅነት ፍቅራችንንና ምስጋናችንን ለማቅረብ እንወዳለን፡፡ ፍቅራችንን የምንገልጽበትና ምስጋናችንን የምናቀርብበት ምክንያትም ቅዱስነትዎ ለዚኽ ታላቅ ተልእኮ ከተሾሙበት ማግሥት አንሥቶ፡-

  1. በርካታ የሰንበት ት/ቤት አባላት እስከ መታሰር ደርሰው ሲታገሉት የቆዩትንና በቅድስት ቤተ ክርስቲያናችን ውስጥ ከመንሰራፋቱ የተነሣ አይነኬ ኾኖ ቅድስት ቤተ ክርስቲያናችንን እያስተቻት ያለውን ሙስናና ብልሹ አስተዳደር በማውገዝዎና ለማስተካከልም አበክረው ሥራ በመጀመርዎ፤
  2. ሰንበት ት/ቤቶች ሲያበረክቱት የቆዩትን አገልግሎት በተጠናከረ መንገድ መቀጠል ይችሉ ዘንድ ያዘጋጁትን የአንድነት መዋቅር ዕውቅና እንዲያገኝና የሚተዳደርበት ሰነድ እንዲያገኝ ከቅዱስ ሲኖዶስ አባላት ጋራ በመኾን መፍቀድዎ፤
  3. በሢመተ ፕትርክናዎ የመጀመሪያ ዘመን በአጭር ጊዜ በየአህጉረ ስብከቱ በመዘዋወር አብያተ ክርስቲያን ያሉበትን ኹኔታ በአካል እየተገኙ በመመልከትዎና ተገቢውን ምክርና መመሪያ በመስጠትዎ ነው፡፡

ብፁዕ ወቅዱስ አባታችን፣ ይህ ያቀረብነው ምስጋና ታሪክ የሚዘግበውንና መዘገብም ያለበትን እውነታ ለማስቀመጥ እንጂ ለከንቱ ውዳሴ ወይም ደግሞ ለሌላ የተለየ ዓላማ እንዳላቀረብነው እንደሚገነዘቡልን ርግጠኞች ነን፤ ምክንያቱም በከንቱ ውዳሴ የቀረበን ምስጋና ቅዱስነትዎ እንደማይቀበሉት እናውቃለን፤ እኛም እንዲኽ ዐይነት ምስጋና የማቅረብ ልማድ እንደሌለንና ወደፊትም እንደማይኖረን በቀላሉ የሚገመት ጉዳይ ነውና፡፡

ብፁዕ ወቅዱስ አባታችን፣ ቅዱስነትዎ በይፋ የገለጹትንና እንዲስተካከል አበክረው ማሳሰቢያ የሰጡበትን የቤተ ክርስቲያን ዘርፈ ብዙ ችግር ለማረም በሚደረገው ጥረት ኹሉ በግንባር ቀደምነት መሰለፍ የእኛም የወላጆቻችንም ጽኑ አቋም እንደኾነና በታዘዝንበት መሥመር ኹሉ ለመሰለፍ ዝግጁዎች መኾናችንን ለቅዱስነትዎ በላቀ አክብሮትና ትሕትና ለመግለጽ እንወዳለን፡፡

ብፁዕ ወቅዱስ አባታችን፣ እኛ የሰንበት ት/ቤት አባላት ብዙዎች እንደሚገምቱን፣ ሕፃናትና ሥራ ፈቶች ሳንኾን ወይም ሰንበት ት/ቤቶች የጨቅላ አእምሮዎችና የሥራ ፈቶች መጠራቀሚያ ሳይኾን ካህናትና ዲያቆናት፣ የሥነ መለኰት ምሁራን፣ ኢንጅነሮች፣ ዶክተሮች፣ አካውንታንቶች፣ የሕግ ባለሞያዎችና የትምህርት ባለሞያዎች በአጠቃላይ እምነት የሚጣልባቸው የቤተ ክርስቲያን ልጆች ያሉበት ኹለገብ ተቋም ነው፡፡

ሰንበት ት/ቤትን የመሠረቱልን አባቶች ክብር ይግባቸውና በረከታቸውም ይደርብንና ሞያ፣ ዕውቀትና ሀብት ብቻም አይደለም ቅን ታዛዥነትና ሐቀኝነትም የዚኽ ኹለገብ ተቋም ፍሬዎች ናቸው፡፡

ብፁዕ ወቅዱስ አባታችን፣ የጀመሩትን የፀረ ሙስናና ብልሹ አስተዳደር የማረም ዘመቻ ከግብ ለማድረስ ሰንበት ት/ቤቶች በተጠንቀቅ ቆመው የእርስዎን ትእዛዝ በመጠባበቅ ላይ እንደሚገኙ በድጋሚ ልናረጋግጥልዎት እንወዳለን፡፡

የቤተ ክርስቲያን አምላክ ዕድሜና ጤና ይስጥልን፡፡

የቅዱስነትዎ ቡራኬ ይድረሰን፡፡

ወስብሐት ለእግዚአብሔር

የአዲስ አበባ ሰንበት ት/ቤቶች አንድነት

ጥር ፰ ቀን ፳፻፮ ዓ.ም.