የአ/አ ሀ/ስብከት የአደረጃጀትና አሠራር ለውጥን በመደገፍ ዛሬ ሊካሄድ የነበረው የድጋፍ ስብሰባ ለመጪው ሳምንት ዐርብ ተላለፈ፤ የድጋፍ መግለጫ የኾነውን ስብሰባ በሦስት ምዕራፎች በመክፈል በከፍተኛ ዝግጅት ለማካሔድ ዝግጅቱ ተጠናክሮ ቀጥሏል

  • በሦስት ምዕራፎች በተከፋፈለው የድጋፍ መግለጫ ስብሰባ መርሐ ግብር÷ የገዳማትና አድባራት አስተዳዳሪዎች፣ ካህናት፣ የአብነት መምህራንና ሰባክያነ ወንጌል በመጀመሪያው ምዕራፍ፤ የሰበካ መንፈሳዊ ጉባኤያት ሊቃነ መናብርትና ምእመናን በሁለተኛው ምዕራፍ፣ ሰንበት ት/ቤቶች በሦስተኛው ምዕራፍ ከብፁዕ ወቅዱስ ፓትርያርኩ ጋራ ተገናኝተው እንዲወያዩ ዕቅድ ተይዟል፡፡
  • ለዛሬው መርሐ ግብር መስተጓጎል ተጠያቂ የተደረጉት የፓትርያርኩ አቡነ ቀሲስ እና የፓትርያርኩ ልዩ ጽ/ቤት ሓላፊ እርስ በርሳቸው እየተወነጃጀሉ ነው፡፡ ሰነዱን ለመመልከት በቋሚ ሲኖዶስ ውሳኔ የተቋቋመው ‹‹የሊቃውንት ጉባኤ›› አባል መኾናቸው የተገለጸው ንቡረ እድ ኤልያስ ኣብርሃ ሁለቱንም የብፁዕ ወቅዱስ ፓትርያርኩን ረዳቶች እንቅስቃሴ እንደሚዘውሩና ከባድ ተጽዕኖ እየፈጠሩባቸው እንደሚገኙ ተመልክቷል፡፡
  • የአደረጃጀትና አሠራር ሰነዱ የመጀመሪያ ዙር ጥናታዊ ውይይት ተሳታፊ የነበሩት ንቡረ እድ ኤልያስ ይፋ ባልኾነ የሥራ ድርሻ በአማካሪነት ስም ብፁዕ ወቅዱስ ፓትርያርኩን ተጠግተው ይፈጥሩታል የሚባለው ይኸው አሉታዊ ተጽዕኖ ርግጥ ከኾነ፣ በጥናታዊ ውይይቱ ወቅት ስለ አደረጃጀትና አሠራር ሰነዱ ከሰጡት ገንቢ ሐሳብ ጋራ የሚጋጭና የንቡረ እዱን መሠሪነት የሚያረጋግጥ ነው – ‹‹ዛሬ የቤተ ክርስቲያን የልደት ቀን ነው፤ በሕይወቴ የቤተ ክርስቲያንን ችግር ከትክክለኛ መፍትሔ ጋራ እንዲህ ተስማምቶ ሲቀርብ አይቼ አላውቅም፤ ማስተካከያ ቢኖር እንኳ ኢምንት ነው፤ ጥናቱን የሠሩት ባለሞያዎች ከተለያዩ ልምዶቻቸው ተነሥተው ቀምረውታል፤ በውይይት ጊዜ ማባከን የለብንም፤ ወደ ሥራ ገብተን ተግባራዊ ማድረግ አለብን፤ ጥናቱ መተግበር ያለበት በጠቅላይ ቤተ ክህነቱም ነው፡፡››  
  • ከአቡነ ቀሲሱ ጋራ እየተወዛገቡ የሚገኙት የልዩ ጽ/ቤቱ ሓላፊ አቶ ታምሩ አበራ ብፁዕ ወቅዱስ ፓትርያርኩ በዛሬው የድጋፍ መግለጫ ስብሰባ ላይ እንደሚገኙ መርሐ ግብር እንደተያዘላቸው የስብሰባው አስተባባሪ ለኾኑ የክፍላተ ከተማ ቤተ ክህነት ጽ/ቤቶች ሥራ አስኪያጆች፣ የገዳማትና አድባራት አስተዳዳሪዎች ዐርብ ምሽት አረጋግጠው ነበር፡፡