አይ ስብሐት ነጋ!
ፕ/ር መስፍን ወልደ ማርያም
በኢትዮጵያ ውስጥ ሥልጣን ሳይኖረው ባለሙሉ ሥልጣን፣ እውቀት ሳይኖረው ባለሙሉ እውቀት የሆነ ሰው ስብሐት ነጋ ብቻ ነው፤ እንዲያውም ከዚያም አልፎ ራሱን የቻለ ሉዓላዊ ነጻነት ያለው ግለሰብ ነው ለማለት የሚቻል ይመስለኛል፤ በዚህ ግለሰብ ላይ የማደንቃቸው ሁለት ነገሮች ናቸው፤ በሉዓላዊነቱ የተጎናጸፈውን ሥልጣን ሙሉ በሙሉ ይጠቀምበታል፤ ይቆጣኛል ወይም ይቀጣኛል ብሎ የሚፈራው የለም፤ ስብሐት ነጋ የሚፈራው ምንም ነገር የለም፤ ሁለተኛ በሉዓላዊነቱ ያለውን ሙሉ ነጻነት በሙሉ ልብ ይጠቀምበታል፤ ናስ በላይ ከበደ እንዳለው ‹‹የቅብጠት መዘላበድ›› ሊሆን ይችላል፤ ስብሐት ነጋ የተናገረው ነገር ትክክል ይሁን አይሁን ጉዳዩ አይደለም፤ ዋናው ነገር መናገሩ ነው።