ፍኖተ ሕይወት – የመጽሐፍ ቅኝት
ደራሲ – ሣህለ ሥላሴ ብርሃነ ማርያም፤ ቅኝት – መስፍን ማሞ ተሰማ
መንደርደሪያ
ሥነ ፅሁፍ የሀገር ታሪክ ባህልና የህብረተሰብ ህይወት … በቃላት ደርዝ ተደርዘው ላለውና ለሚመጣው ትውልድ የሥነ ፅሁፍ ጠቢባን የሚያበረክቱት ቅርስ ነው። ጥበብ ነው ሥነ ፅሁፍ፤ የሀቅ መልህቅ። ጥበብን ያላሸተ፤ እውነትንና ፍትህን ያላማጠ፤ ያልወለደ ሥነ ፅሁፍ – ምን ቢኳኳል ቃል በቃል፤ ምን ቢቀማጠል፤ ቢያማልል – እንኳንና ዘመን ከዘመን ተሻግሮ፤ ትውልድን በትውልድ አጥፎ ‘ዘለዓለማዊ ህልው’ ሊያገኝ ቀርቶ – እንደ ጠዋት ጤዛ አረጋገፉ፤ ፋታም አይሰጥ አሟሟቱ። እንዲህ ያሉ – በየዘመኑ የመከኑ ብዕራት፤ በየዘመኑ ነበሩ፤ ዛሬም አሉ፤ ነገም ይኖራሉ።