ሰበር ዜና – ለደመወዝ ጭማሪ ጥናት ድጋፍ ለማግኘት በሚል በተጭበረበረ መንገድ የተሰበሰበ የካህናት ፊርማ የአ/አ ሀ/ስብከት የአስተዳደር መዋቅር ጥናት መቃወሚያ ኾኖ ለፓትርያርኩ ቀረበ፤ በጥናታዊ ውይይቱ ገና ያልተሳተፉ ሙሰኛ አለቆችና ሠራተኞች የተቃውሞው አካል መኾናቸው በተቋማዊ ለውጡ ላይ ያላቸው ጥያቄ በጥላቻና ጥቅመኝነት ላይ ብቻ መመሥረቱን አረጋግጧል
- ሀ/ስብከቱ ከኑሮ ውድነት አንጻር በአጥቢያዎች ተሳትፎ እያስጠናው የሚገኘው ጊዜያዊ የደመወዝ ጭማሪ ማስተከከያ ጥናት በመዋቅር፣ አደረጃጀትና ዝርዝር አሠራር መመሪያ ረቂቅ ውስጥ ካለው የአብያተ ክርስቲያናት ደረጃ መስፈርት፣ የሥራ መደብ ግምገማ፣ የአገልጋዮች ጥቅምና ጫና ጥናት ጋራ አንዳችም ግንኙነት የለውም፡፡
- ለፊርማ አቤቱታው የቀረቡት ጥያቄዎች ይዘት ‹ተቃዋሚዎቹ›÷ ሕገ ቤተ ክርስቲያኑ ከቃለ ዐዋዲ ደንቡ ጋራ ያለውን ልዩነትና በአዲስ አበባ ሀ/ስብከት ላይ ያለውን ተፈጻሚነት በቅጡ ለይተው እንደማያወቁ፣ ስለ ለውጥ አመራር መዋቅርና አደረጃጀት ጥናት ያላቸውን የተሳሳተ ግንዛቤ፣ የቤተ ክርስቲያን አስተዳደር በካህናትና ምእመናን አንድነት የተዋቀረ መኾኑንና ምእመናንም ድርሻ እንዳላቸው የማይቀበል፣ በፍትሕ ሥርዐት ቤተ ክርስቲያን የራሷን ጉዳዮች በራሷ ተቋማት ለመዳኘት ያላትን ሉዓላዊነት የማያምንና ኦርቶዶክሳዊ ውግንና የጎደለው፣ የለውጡ ከፍተኛ ተጠቃሚዎች የሚኾኑት ካህናትና ሊቃውንት በተወሰነላቸው የተሳትፎ ቁጥር ልክ በጥናታዊ ውይይቱ እንዳይሳተፉ በጥቅመኛ አለቆች፣ ጸሐፊዎችና የአስተዳደር ሠራተኞች አፈና መፈጸሙ፣ የቅ/ሲኖዶስ ምልአተ ጉባኤ ዕውቅና የሰጠውን የባለሞያ ቡድን ‹‹ኅቡእ አካል›› በማለትና የአፈጻጸም አቅጣጫ የሰጠበትን ጥናቱን ‹‹የኅቡእ አካሉ የግል ፍላጎት ነው›› የሚል ዐመፀኝነት፣ በፓትርያርኩና በረዳት ሊቀ ጳጳሳቸው መካከል ቅራኔ ፈጥሮ የተቋማዊ ለውጥ ሂደቱን በመቆጣጠርና በማክሸፍ ሕገ ወጥ ጥቅምን ለመከላከል ያለመ መኾኑ የተጋለጠበት ነው፡፡
- በጥናታዊ ውይይቱ ላይ ሳይሳተፉ ጥናቱን ከተቃወሙትና ካህናትን በግዳጅ ለተቃውሞ ከሚያነሣሡት አስተዳዳሪዎች መካከል የአፍሪቃ ኅብረት ደብረ ምሕረት ቅዱስ ሚካኤል ቤተ ክርስቲያን አስተዳዳሪ መልአከ ብሥራት መልአክ አበባው ይገኝበታል፡፡ በታዕካ ነገሥት በኣታ ለማርያም ገዳም ካህናት፣ ሊቃውንትና ሠራተኞች ስም በጸሐፊው ሊቀ ትጉሃን ሲሳይ ገብረ ማርያም የተሰበሰበው የተቃውሞ ፊርማ ገዳሙን እንደማይወክል ሊቀ ሊቃውንቱ አባ ኃይለ መስቀል ውቤ ለሀ/ስብከቱ በደብዳቤ ያስታወቁ ሲኾን ጥናታዊ ውይይቱን በጉጉት የማኅደረ ስብሐት ልደታ ለማርያም ካቴድራል አስተዳዳሪም እንደሚጠብቁት ለጽ/ቤቱ ተናግረዋል፡፡
- ከካህናት፣ የአብነት መምህራን፣ የሰንበት ት/ቤት አመራሮችና ምእመናን ተወጣጥተው በጥናታዊ ውይይቱ እንዲሳተፉ ለተጠሩ 16 ልኡካን በአግባቡ ጥሪውን ሳያስተላልፉ የአስተዳደር ሠራተኞችን ብቻ ይዘው ከተገኙትና በአጥኚው ቡድን ውስጥ ‹‹ካህናትና ሊቃውንት አልተካከተቱም›› በሚል ራሳቸውን በግንባር ቀደምነት ተቃዋሚ ካደረጉ የአጥቢያ አስተዳደሮች መካከል፡- ገነተ ጽጌ ቅዱስ ጊዮርጊስ (5 ተሳታፊዎች ብቻ የላከ)፣ ድል በር መድኃኔዓለም (1 ተሳታፊ ብቻ የላከ)፣ ደብረ ቢታንያ ጻድቁ አቡነ ተክለ ሃይማኖት(6 የቢሮ ሠራተኞች ብቻ የላከ)፣ መሪ ሎቄ ጻድቁ አቡነ ገብረ መንፈስ ቅዱስ (4 የቢሮ ሠራተኞች ብቻ የላከ) መኾኑ ተረጋግጧል፡፡
- በጥናት ላይ ለተመሠረተውና ወደኋላ ለማይመለሰው የሀ/ስብከቱ የተቋማዊ ለውጥ አመራር መዋቅር፣ አደረጃጀትና ዝርዝር የአሠራር መመሪያ ተግባራዊነት አገልጋዩ የለውጥ ሐዋርያ እንዲኾን ያሳሰቡት የፓትርያርኩ ምላሽ ዛሬ ይጠበቃል፡፡
ተጨማሪ መረጃዎችን ይከታተሉ
