ትግል እስከመቃብር።……..
የዛሬይቱ ቀን በህይወቴ አዲስ ምዕራፍ የጀመርኩባት ዕለት ናት።እናት ሐገሬ ኢትዮጵያን ለቅቄ የሞያሌን ኬላ ተሻግሬ የኬንያን ምድር የረገጥኩባት ታሪካዊ እለት ።ኅዳር ሠላሣ ቀን አስራ ዘጠኝ መቶ ዘጠና ስምንት ዓመተ ምሕረት ዕለተ ዐርብ ከቀትር በፊት።ከደቡብ ኢትዮጵያ ወደ ሰሜን ኬንያ ጋንቦ ቀበሌ የገባሁበት ቀን ስምንተኛ ዓመት መታሠቢያ።
የማቴዎስ ወንጌል ምዕራፍ አስር ቁጥር ሃያ ሦሥትን ይመልከቱ። ባላሠቡትና ባልጠበቁት ጊዜና ሰዓት ከትውልድ ቀዬዎ ሊሠደዱ ይችላሉ።ዛሬ ምስራቅ አፍሪቃ ምድር ወገብ አቅራቢያ ቪክቶርያ ሐይቅ ዳርቻ ላይ ሆኜ የተሠደድኩበትን ምክንያት ሣሠላስል መሠደዴ አግባብነት ነበረው ወይስ እንደ ኮነሬል መንግስቱ ፍርጠጣ ነው ለማለት ህሊናዬ ዘወትር እንደጠየቀኝ አለ።
ሟቹ የወያኔ ጠቅላይ ሚንስትር የግንቦት ሠባቱን የምርጫ ውጤት በአጋዚ ጥይት ከቀለበሡትና ሕገ መንግስቱ በሕገ አራዊት ከተለወጠ በኋላ የሐገር ቤት ሠላማዊ ትግልና የፕሬስ ነፃነት ጥቅምት ሃያ ሁለት ቀን አክትሟል።
ጋዜጠኞች፣የሠብዓዊ መብት ተሟጋቾች ተለቅመው ሲታሠሩ፣ወጣቱ ያለ ሀጥያቱ በየጦር ካምፑ ሲታጎር የኔ ዕጣ ፈንታ ምን ሊሆን እንደሚችል ለማንም ግልፅ ነበር። ጥቅምት ሃያ ሁለት አመሻሽ ላይ ሱፍና ከረባት፣መነፅርና ፕሮቶኮል ቀርተው አልባሌ በመልበስና በመምሠል ከቦታ ቦታ ስሽሎኮለክ ብቆይም ነገሮች ከመሻሻል ይልቅ እየተበላሹ በመምጣታቸው ወደ ኬንያ ለመጓዝ ህዳር ሃያ ሁለት አካባቢ የወሰንኩ ይመስለኛል።
ጠቅላይ ሚንስትር ለገሠ ዜናዊ በኛ ላይ ጦር ሲያውጁ ያቀረቧቸው አማራጮች ት<ዝ ይሉኛል።
፩ አርፎ መቀመጥ ፪መሠደድ ፫ጫካ መግባት ፬ቃሊቲ ።
ለነፃነት የሚደረገውን ትግል ለማገዝ በወቅቱ የኔ ምርጫ መሠደድ ነበር።ሠላማዊ ትግል አላዋጣ ሲል ጠመንጃ ማንሣት የግድና ተገቢ መሆኑን ከነማንዴላ ኤኤንሲ ፓርቲ ውሣኔ መማር ይቻላል።
አማርኛ ቃለ መጠይቅ ለቪኦኤ ለመስጠት የሚጠየፉት የብአዴኑ በረከት ስምዖን የማስታወቅያ ሚንስትር በነበሩበት ፩፱፱፪ የፓርላማ ምርጫ ወቅት በአፍሪቃ አዳራሽ የክርክር መድረክ ላይ ወያኔ ስልጣን በጠመንጃ እንደያዘና በምርጫ ቢሸነፍ ስልጣን ለመልቀቅ ዝግጁ ነወይ ስል ላቀረብኩላቸው ጥያቄ ደርግ መብታችንን በመርገጡ ጠመንጃ አንስተናል ሲሉ መናገራቸውን አስታውሣለሁ።መብቱ የተረገጠ ሕዝብ ጠመንጃ ሊያነሣ እንደሚገባ በረከት የተገነዘቡ ይመስላል።
የኔ ድርሻ እንደጋዜጠኛና የሠብዓዊ መብት ተሟጋች ከሐገር ከተሠደዱ ቦኋላ የፈረንጅ ሐገር ኑሮ ለምዶ ሆዳም ዲያስጶራ መሆን ሣይሆን የተሠደዱበትን ዓላማ ባለመዘንጋት ሐገራዊና ህሊናዊ ግዴታን መወጣት ነው።
የፓለቲካ ስደተኛ ነኝ ብሎ የኬዝ ደራሲ መሆንና የስደተኛ መታወቅያ ታቅፎ ከንቱ የተስፈኛ ህይወት መምራትን ልንጠየፈው ይገባል።ሁለት ሺ ኪሎ ሜትር ርቀት ላይ ሆኖ ወያኔን ወያኔ ብሎ መጥራት የሚፈራ ማንነት ይዞ መንከላወስ በታሪክና በትውልድ እንደሚያስወቅስም መረዳት ያስፈልጋል።
ሁለት ልብ ሆኖ ሁለት ማልያ እየለበሡ በአንድ ሜዳ ላይ መጫወት አይገባም።እኔ የፓለቲካ ስደተኛ ነኝ።የየትኛውም የፓለቲካ ድርጅት አባል አይደለሁም።መሆንም አልፈልግም።ያ ማለት ግን የሐገሬ ጉዳይ አያገባኝም፣ካናዳ ገብቼ የስደት ኑሮ ለመኖር የመጣሁ የኤኮኖሚ ስደተኛ ነኝ፣ኬዜ ተቀባይነት እንዲያገኝ ምርጥ የኬዝ ደራሲዎች የፃፉልኝን ገፀ ባህሪ በተገቢው መድረክ የምተውን ተወናይ።ካልሆነም ፍራሼ ስር የደበቅኩትን ፓስፓርት አድሼ ምሣዬን ካምፓላ በልቼ ለራቴ አዲስ አበባ የምበር ዋቴ።ዛሬ ይህን ሁሉ ያስቀባጠረኝ እንደዋዛ ከሐገር፣ከቤተሠብ፣ከጓደኛ ተለይቼ ሁለት ሺ ዘጠኝ መቶ ዘጠና ሁለት ቀናት በስደት መቆየቴን በመዘከር ነው።
ህይወት ይቀጥላል።አዲስ አበባ ላይ መፃፍና መኖር ብከለከልም ካምፓላ ላይ እየፃፍኩ እኖራለሁ።ብዕሬ ዝም አትልም።እውነትን፣ነፃነትን፣ፍትህን በሐገሬ ሠማይ ላይ እስክመለከት ድረስ እፅፋለሁ።ሕገመንግስቱ ከወሬና ከመነበብ ባሻገር በተግባር እስኪፈፀም፣ሕዝቤ በነፃና ዴሞክራሲያዊ ምርጫ ሕዝብ የሚመርጣቸው ፓርቲዎች ስልጣን እስኪረከቡ ድረስ እፅፋለሁ ፣እናገራለሁ።
ማንዴላን የታራክ ሠገነት ላይ የሠቀላቸው ለነፃነት የከፈሉት ክቡር ዋጋ ነው።ሞት እንደሆነ አይቀሬ ነው ።እየሞቱ ከመኖር ለትውልድ ነፃነት በየመስኩ የአቅማችንን እናበርክት መልክቴ ነው።
እስክንድር፣ውብሸት፣ርዕዬት፣አንዱዓለምና በርካቶች……..የኛ ማንዴሎች ናቸው።
እንደአንዳቸውም ባለመሆኔ ባዝንም ባለሁበትም ቢሆን ስለነሡና ስለሐገሬ ልጮህ እወዳለሁ።አምላኬም ይረዳኛል።ዛሬ አዲስ የልደት ቀኔ ናት።ዕድሜዬም ስምንት ነው።አዲስ ህይወት ከኬንያ ጋንቦ ጀምሬ አሁን ካባላጋላ ላይ ነኝ።የነፃነት ትግሌ ግን እስከመቃብሬ በብዕሬ ይቀጥላል።ትግልእስከመቃብር።
ደረጀ በጋሻው<pen Ethiopian>