የቅ/ሲኖዶስ የሲዳማና ጉጂ ቦረና አህጉረ ስብከት ልኡክ ነገ በሐዋሳ የዕርቀ ሰላም መግለጫ ያወጣል፤ ዕርቀ ሰላሙና መግለጫው የሐዋሳውን ውዝግብ ብቻ እንጂ በሊቃውንት ጉባኤው ፊት ቀርቦ እንዲጠየቅ የታዘዘውን በጋሻው ደሳለኝንና ሌሎች ሕገ ወጦችን አይመለከትም

  • ዕርቀ ሰላሙን በሚያወርደው የሁለቱም ወገኖች ስምምነት መሠረት ከኅዳር ወር ፳፻፫ ዓ.ም. ጀምሮ ከሐዋሳ ደብረ ምሕረት ቅ/ገብርኤል ቤተ ክርስቲያን ተለይተው ‹‹ወንዲታ›› በተባለው የግለሰብ ስቱዲዮ ውስጥ ሲሰበሰቡ የነበሩ ምእመናን÷ በሰንበት ት/ቤት፣ በስብከተ ወንጌል እና በልማት ኮሚቴዎች ውስጥ የመሳተፍና የማገልገል መብታቸው ይጠበቅላቸዋል፡፡ በዚህም መሠረት በሰንበት ት/ቤቱ አመራርና በስብከተ ወንጌል ኮሚቴ ሁለት፣ ሁለት፤ በልማት ኮሚቴ ውስጥ ደግሞ በሰበካ ሳይወሰኑ እስከ አምስት አባላትን በማሳተፍ የማገልገል መብት ይኖራቸዋል፡፡
  • የ‹‹ወንዲታ›› ተሰብሳቢዎች ጥያቄ ያነሡበት የደብረ ምሕረት ቅ/ገብርኤል ቤተ ክርስቲያን ሰበካ ጉባኤ በቃለ ዐዋዲው ደንብ መሠረት የተመረጠ በመኾኑ የሥራ ጊዜውን ሲጨርስ በሚያካሂደው አዲስ ምርጫ ብቻ ይተካል፡፡ በሌሎች የከተማው አጥቢያ አብያተ ክርስቲያን ያለ ሰበካቸው በሰበካ ጉባኤያት የተመረጡ ምእመናን ካሉ በአህጉረ ስብከቱ ተጣርቶ እርምት እንዲደረግበት ስምምነት ላይ ተደርሷል፡፡
  • ቅዱስ ሲኖዶስ በየጊዜው ባወጣቸው መመሪያዎች መሠረት በቤተ ክርስቲያናችን የስብከተ ወንጌል አገልግሎት የሚሰጡ ሰባክያንና መምህራን ሕጋዊነት የሚኖራቸው፡- 1) የቤተ ክህነቱ ሠራተኛ ሲኾኑ፣ 2) የጠቅላይ ቤተ ክህነት ማስረጃ ሲኖራቸው፣ 3) በአህጉረ ስብከት የመምህራን ይላክልን ጥያቄ ሲቀርብ ነው፡፡
  • ስለኾነም ተጠያቂነት ያለው አገልግሎት ለመስጠትና ለአገልግሎቱ መሳካት ይረዳ ዘንድ ሰባክያንና መምህራነ ወንጌል÷ ከመንበረ ፓትርያርክ ጠቅላይ ቤተ ክህነት የስብከተ ወንጌልና ሐዋርያዊ ተልእኮ መምሪያ ወይም ከአህጉረ ስብከት ጽ/ቤት ወይም ከአህጉረ ስብከቱ ሊቃነ ጳጳሳት ዕውቅናና ፈቃድ ሊያገኙ ይገባል፡፡
  • በዚህ መሠረት ያለ ጠቅላይ ቤተ ክህነቱ፣ ያለሀ/ስብከቱና ያለብፁዕ ሊቀ ጳጳሱ ፈቃድ የስብከተ ወንጌል ጉባኤ ማዘጋጀት ይኹን ሰባክያንና መምህራንን መጋበዝ እንደማይቻል፣ የስብከተ ወንጌል አገልግሎቱም ከቡድናዊ ተጽዕኖዎች ነጻ ኾኖ የኦርቶዶክሳዊት ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያንን ሐዋርያዊ አገልግሎት መጠናከርና መስፋፋት ማዕከል አድርጎ መፈጸም እንደሚገባው በሐዋሳው የዕርቀ ሰላም ስምምነት ላይ ተገልጦአል፡፡

*                      *                        *

  • ሁለቱ ወገኖች (የሐዋሳ ደ/ምሕ/ቅ/ገብርኤል ገዳም ልማት ኮሚቴ አባላት የኾኑ የምእመናን ተወካዮች እና በወንዲታ ስቱዲዮ ተሰብሳቢዎች) በቅ/ሲኖዶስ ጽ/ቤት በዋና ጸሐፊው ብፁዕ አቡነ ሉቃስ ሰብሳቢነት ባካሄዱት የሁለት ቀን የፊት ለፊት የዕርቀ ሰላም ውይይት÷ ‹‹ግለሰባዊ››፣ ‹‹ሀገረ ስብከታዊ›› እና ‹‹ሲኖዶሳዊ›› በሚል የተከፈሉ ችግሮች በዝርዝር መቅረባቸው ተገልጦአል፡፡
  • በቅዱስ ሲኖዶስ ጽ/ቤት ኅዳር ፭ እና ፮ ቀን ፳፻፮ ዓ.ም. በተካሄደው የሁለቱ ወገኖች የዕርቀ ሰላም ውይይት፣ ‹‹ሀገረ ስብከታዊ›› በሚል ከ‹‹ወንዲታ ስቱዲዮ ተሰብሳቢዎች›› ከቀረቡት ነጥቦች ውስጥ የሀ/ስብከቱ ሥራ አስኪያጅ ሊቀ ኅሩያን ዓለም እሸት ገብረ ጻድቅ ከሓላፊነታቸው መነሣት እንዳለባቸው የቀረበው ጥያቄ አንዱ እንደነበር ተመልክቷል፡፡
  • ይኸው ጥያቄ ሊቀ ጳጳሱ ብፁዕ አቡነ ገብርኤልም ከሀ/ስብከቱ እንዲነሡ ከሚጠይቀው የሐዋሳ፣ ክብረ መንግሥት፣ ነገሌ ቦረና ሠላሳ ጠርዘኛ ግለሰቦች ከባለሥልጣናት እንደተሰጣቸው በተነገረ ድጋፍ በቅ/ሲኖዶስ ምልአተ ጉባኤ መደበኛ ስብሰባ ፊት ካቀረቡት የተለየ እንደኾነ የገለጸው የዜና ምንጩ÷ ሥራ አስኪያጁ በአስተዳደርና በሥነ ምግባር ባለባቸው ግልጽ ችግር ሳቢያ ከሓላፊነት መነሣታቸው ሁለቱም ወገኖች የተስማሙበት መኾኑንና በዚህም መሠረት በሚመለከተው አካል ርምጃ መወሰዱን ገልጦአል፡፡
  • ‹‹ሲኖዶሳዊ›› በሚል እንደ ችግር የቀረበው፣ ‹‹የማኅበረ ቅዱሳን ሐዋሳ ማዕከል አባላት በቤተ ክርስቲያኒቱ አስተዳደራዊ ጉዳይ ጣልቃ አይግባ›› በሚል መነሻ በቀድሞው ፓትርያርክ ርእሰ መንበርነት የተመራው ቋሚ ሲኖዶስ በቁጥር 3378/56/2003 በቀን ፲፫/፰/፳፻፫ ዓ.ም. ለሀ/ስብከቱ ያስተላለፈውን በምልአተ ጉባኤው የጸደቀውን የማኅበሩን መተዳደርያ ደንብ በእጅጉ የሚፃረር ውሳኔ ተፈጻሚነት የሚጠይቅ ነው፡፡ በዚህ ውሳኔ ሽፋን የሐዋሳ ምእመናን አንገብጋቢ ጥያቄዎች ሲደፈቁ መኖራቸውን ያስታወሰው የመረጃ ምንጩ÷ የማኅበሩ አባላት በየአጥቢያቸው በሰበካ ጉባኤ፣ በሰንበት ት/ቤት፣ በስብከተ ወንጌልና በልማት ኮሚቴዎች የመምረጥና የመመረጥ መብታቸው የተጠበቀ እንደኾነ በዕርቀ ሰላም ስምምነቱ ላይ መስፈሩን ጠቅሷል፡፡

*                      *                        *

  • የቅ/ሲኖዶስ ምልአተ ጉባኤ ጥቅምት ፳፩ ቀን ፳፻፮ ዓ.ም. ዓመታዊ መደበኛ ስብሰባውን ሲያጠናቅቅ ባወጣው መግለጫ እንደጠቀሰው፣ ከ፳፻፫ ዓ.ም. ጀምሮ የተፈጠረው ‹‹ሁከት›› ‹‹በዕርቅ›› እንዲፈጸም ጥያቄ ያቀረቡት ሁለቱም ወገኖች ናቸው፡፡ ይኹንና ጉዳዩ ከዕርቅ መንገድ ይልቅ ከቤተ ክርስቲያን የወጡ ወገኖች ጥፋታቸው እንደ ግለሰብ መጠን በዝርዝር እየተለየ ስሕተታቸውን አምነው ንስሐ በመግባት ቀኖናዊ መንገድ እንዲመለሱ በማድረግ መፈጸም ይገባው እንደነበር በመጥቀስ የተደረሰውን የዕርቀ ሰላም ስምምነት የሚተቹ ወገኖች ተደምጠዋል፡፡   
  • በሌላ በኩል ዕርቀ ሰላሙና ስምምነቱ÷ ‹‹ሊቀ ጳጳሱ ይነሡ››፣ ‹‹ዐውደ ምሕረቱን መቆጣጠር ሀ/ስብከቱን መቆጣጠር ነው›› በሚል የስብከተ ወንጌል እንቅስቃሴውን፣ በተለይም በደብረ ምሕረት ቅዱስ ገብርኤል ቤተ ክርስቲያን ሰበካ ጉባኤና ሰንበት ት/ቤት ላይ ያለከልካይ ለመንሰራፋት ለሚያልሙቱ፤ ከእነርሱም መካከል የፕሮቴስታንት ባለሥልጣናት አስተዳደራዊ ድጋፍ እንደሚደረግላቸው የሚነገርላቸውን ግለሰቦች ጥፋት ለመከላከል እንደሚያስችል የሚያምኑ አስተያየት ሰጭዎች በበኩላቸው፣ ከ፳፻፫ ዓ.ም. ጀምሮ ከፕሮቴስታንታዊ ተሐድሶ ኑፋቄ አራማጆች ጋራ የዓላማና ጥቅም ግንኙነት ፈጥረው ከፍተኛ የገንዘብ ድጋፍ ሲደረግላቸው ለቆዩ አካላት የጅምላ ፈቃድ ና ሾልኮ መግቢያ እንዳይኾን አፈጻጸሙን በከፍተኛ ጥንቃቄና ያለማቋረጥ መከታተል እንደሚያስፈልግ ያሳስባሉ፡፡
  • የቅ/ሲኖዶስ ምልአተ ጉባኤ እዚያው ሐዋሳ ተገኝተው ዕርቀ ሰላሙን እንዲያወርዱ የሠየማቸው ብፁዓን አባቶች÷ ብፁዕ አቡነ ማትያስ የካናዳ ሀ/ስብከት ሊቀ ጳጳስ፣ ብፁዕ አቡነ እስጢፋኖስ በአዲስ አበባ ሀ/ስብከት የፓትርያርኩ ረዳት ሊቀ ጳጳስና የጅማ ሀ/ስብከት ሊቀ ጳጳስ እና ብፁዕ አቡነ ሉቃስ የቅ/ሲኖዶስ ዋና ጸሐፊና በክልል ትግራይ የምዕራብ ሰቲት ሑመራ ሀ/ስብከት ሊቀ ጳጳስ ነገ፣ ኅዳር ፳፱ ቀን ፳፻፮ ዓ.ም. በሐዋሳ ደብረ ምሕረት ቅ/ገብርኤል ገዳም ዐውደ ምሕረት ላይ ተገኝተው ሁለቱ ወገኖች የደረሱበትን የዕርቀ ሰላም ስምምነት በመግለጫ መልክ ለመላው የሐዋሳ ኦርቶዶክሳዊ ምእመን ይፋ ያደርጋሉ፡፡
  • ይኸው ዕርቀ ሰላም ስምምነት መግለጫ ሥነ ሥርዐት ስምምነቱን የሚፃረር አላስፈላጊ ትዕይንት ለማሳየት ሊጠቀሙበት ከሚያስቡ አካላት አደፍራሽ ድርጊት ሊጠበቅ እንደሚገባ በርካታ ወገኖች እያሳሰቡ ነው – ‹‹ጥቁር ጨርቅ አውለብልበን እንደወጣን ነጭ ጨርቅ እያውለበልብን እንገባለን፤ በጋሻውን በመካከል አድርገን እየዘመርን እንገባለን›› የሚሉት ተጠቅሰዋል፡፡

*                      *                        *

  • ኦርቶዶክሳዊ ትምህርተ ሃይማኖትንና ትውፊትን የሚፃረሩ ንግግሮችን ከመናገር አልፎ ‹‹እርስዎ ፈቃድ ሊሰጡኝም ሊነሱኝም አይችሉም›› እያለ መመሪያቸውን እየጣሰ ሕገ ወጥ ጉባኤያትን ሲያካሂድ የቆየው በጋሻው ደሳለኝ፣ ብፁዕ አቡነ ገብርኤል እግር ላይ ወድቆ ይቅርታ ጠይቋል፤ ብፁዕ ሊቀ ጳጳሱ የይቅርታ ጥያቄውን ሲቀበሉ ስለ ሃይማኖት ሕጸጽ የቀረበበት ጥያቄ በተጀመረበት ቀኖናዊ መንገድ ማለቅ ያለበት በመኾኑ የይቅርታ ጥያቄውን የሚቀበሉትና ይቅርታ የሚያደርጉለት በግላቸው እንደ መንፈሳዊ አባት መጠን መኾኑን ግልጽ አድርገውለታል – ‹‹በግሌ የተጣላኹት ሰው የለኝም፤ ብትሰድበኝም ድንጋይ ብትወረውርብኝም መጥተኽ ጉልበቴ ላይ ስትወድቅ አባት ነኝና ይቅርታ አደርግልሃለኹ፡፡››
YeBitsuan Liqane Papasat ena Likawunet Timir Gubae on Begashaw

የብፁዓን ሊቃነ ጳጳሳትና የሊቃውንት ጉባኤ አባላት ጥምር ጉባኤ ሚያዝያ ፴ ቀን ፳፻፬ ዓ.ም. ለጥያቄ ተፈልጎ ስላልቀረበው በጋሻው ደሳለኝ ለብፁዕ ወቅዱስ አቡነ ጳውሎስ ያቀረበው ሪፖርት

Holy Synod on Begashaw

የቅዱስ ሲኖዶስ ምልአተ ጉባኤ የፕሮቴስታንታዊ ተሐድሶ ኑፋቄ አራማጅ የኾኑ 7 ድርጅቶችንና 16 ግለሰቦችን ባወገዘበት ውሳኔው በብፁዓን ሊቃነ ጳጳሳትና በሊቃውንት ጉባኤ አባላት ጥምር ጉባኤ ለጥያቄ ተጠርቶ ስላልቀረበው በጋሻው ደሳለኝ የሰጠው ትእዛዝ

  • እንደ በጋሻው ለይቅርታ ጥያቄ ወደ ብፁዕ ሊቀ ጳጳሱ የቀረበው ዲ/ን ያሬድ አደመም ‹‹የሐዋሳ ችግር የምእመናኑ፣ የሰበካ ጉባኤውና የሀ/ስብከቱ ጉዳይ ስላለበት በእኔ ብቻ የሚያልቅ አይደለም፤›› የሚለው የሊቀ ጳጳሱ አቋም ከተገለጸለት በኋላ ነበር የዕርቀ ሰላሙ ሂደት ለደረሰበት ፍጻሜ ግንባር ቀደም ኾኖ የተንቀሳቀሰው፡፡ በዚህም የ‹‹ወንዲታ›› ስቱዲዮ ተሰብሳቢ ከኾኑና ለዕርቀ ሰላም ውይይቱ ተወክለው ከመጡ ዘጠኝ ግለሰቦች መካከል ከሦስቱ ከፍተኛ ተቃውሞ ገጥሞት እንደነበር ተዘግቧል፡፡
  • ‹‹ሊቀ ጳጳሱና ሥራ አስኪያጁ ከሀ/ስብከቱ ይነሡ፤ የሐዋሳ ደብረ ምሕረት ቅ/ገብርኤል ገዳም ሰበካ ጉባኤ፣ ሰንበት ት/ቤትና ልማት ኮሚቴ ፈርሶ ዳግመኛ ይዋቀር›› ለሚሉት ‹ጥያቄዎቻቸው› የሽምግልናን/የዕርቅን መንገድ ሳይኾን የቅ/ሲኖዶሱን ቀጥተኛ ውሳኔ እንደሚሹ መስከረም ፳፪ ቀን ፳፻፮ ዓ.ም. በቅ/ሲኖዶስ ጽ/ቤት በተካሄደ ውይይት ላይ ገልጸው የነበሩት ሦስቱ የዲ/ን ያሬድ አደመ ተቃዋሚዎች፣ ሕዝቡ ከእነርሱ ጋራ መሰለፉን በመናገር ብፁዕ አቡነ ሉቃስ የሚመሩትን ውይይት አቋርጠው መውጣታቸው ተሰምቷል፡፡