እስክንድርን በፍትሐዊ ምርጫ እንደማንዴላ ለመሪነት ለማብቃትና …..
ታላቁ የነፃነት አርበኛ ኔልሰን ማንዴላ በአይቀሬው ሞት ሲረቱ ጆሀንስበርግ ብቻዋን የሀዘን ቡልኮ አላጠለቀችም።መላ ዓለም በሀዘን በረዶ ተመቷል።አፓርታይድን ወደ ከርሠ መቃብር ያወረደ ጀግና በአይቀሬው ሞት ተረታ።
እንደኔ ምኞት አፍሪቃ በየማዕዘኑ የማንዴላን አይነት መሪ ብታገኝ ምን ያህል የታደለች አህጉር በሆነች ነበር<>የተባበሩት የአፍሪቃ አንድ ገናና ስቴት በሆንን ነበረ።ነገ የሚሆነውን ለመተንበይ ነብይ መሆን ቢያስፈልግም አሁን ያለችው አፍሪቃ ከሃምሣ አራት ግዛትነት ወደ አንዲት አህጉር እንድትመጣና አንዲት ሐገር ለመሆን በየቤታችን ያለው ማነቆና የገዢ ፓርቲዎች ማቱሣላዊ ቆይታ ድቅድቅ ላይ መሆናችንን ጠቋሚ ነው።ወደ ስልሣና ሠባ ትናንሽ ሐገራት እንዳንከፋፈልም የሚያሠጉ ሁኔታዎችም መኖራቸውን መገንዘብ ይኖርብናል።
ከማንዴላ ጋር የጠበቀ ቁርኝት የነበራት የኔዋ ፀረ አፓርታይድ የነበረችው ኢትዮጵያ ጠያይም ሐገር በቀል አፓርታይዳዊ ስርዓት አራማጆች እያቆጠቆጠባት መሆኗን መደበቅ ለኔ ህሊና አይመጥንም።
የስራ ባልደረባዬ እስክንድር ነጋ በግፈኞች የተፈረደበት ጠበንጃ አንስቶ ወይም ፓርቲ መስርቶ ለስልጣን ስለታገለ እንዳልሆነ አሳሪዎቹ ጭምር የሚገነዘቡት መራራ ሐቅ ነው።
እስክንድርና ማንዴላ የነፃነት ታጋዮች ናቸው።ማንዴላ አፓርታይድን ለመዋጋት ቢያንስ ወታደራዊ ስልጠና በሐገራችን ጭምር እንደወሠዱ ከታሪክ ተገንዝበናል።እስክንድር የጦር መሣርያና የጦር ሠፈርፊትም ይሁን ወደፊት ከእስር ሲወጣ እንደማይረግጥ ስለማውቀው ላረጋግጥ እችላለሁ።የእስክንድር ኡዚ ብዕሩ ነው።ሟቹ ለገሠ ዜናዊ ጥይት በማይበሳው መኪና ታጅቦ ሲጓዝ አናቱን ብሎ ያዞረው ከእስክንድር ቀለም ተፊ ሠላማዊ ኡዚ ብዕሩ የተተኮሰ ህዝባዊ ማዕበል ቀስቃሽ ፅሁፉ ነው።ያሣሠረውም ሙያውና ሕዝባዊ አመለካከቱ ነው።
ከአሜሪካ ቅምጥል ኑሮን ንቆ የመጣው ለውጥ መጥቷል፣በሐገሬ በሙያዬ የበኩሌን ላበርክት ብሎ በመወሰኑ ነበር።ከሃያ ዓመታት በላይ ስርዓቱን በስክሪብቶ ሲፋለም የኖረው።
ማንዴላ ቢባል ኣይበዛበትም።ለሃገሩ ብሎ ያላጣው ነገር የለም።
ነገ እንደ እስክንድር ነጋ አይነት ዜጎች የሐገራችን ተስፋ ይሆናሉ።የነ ስብሐት ነጋ ስርዓት ሲመሽበትና የነብርሃኑ ነጋ ዘመን ሲመጣና እውነተኛ የሚተገበር ህገ መንግስት ሲዘርጋ ህዝቡ የመረጠው ፓርቲ ስልጣን ላይ ሲወጣ የዛሬ ስምንት ዓመት ጥያት ወደወሁባት የአፍሪቃ መዲናይቱ እትብቴ የተቀበረባት እውነተኛዎ ሪፐብሊክ ኦፍ ዴሞክራቲክ ኢትዮጵያ በወጣሁበት ሞያሌ ሳይሆን በቦሌ እገባለሁ።ዘወትር የምጠብቃት ቀን ደሞ ትመጣለች።
ማንዴላ ታሪክ ሰርቶ አልፏል።ኢትዮጵያዊያን የራሣችንን ኤኤንሲ መስርተን በማቆጥቆጥ ላይ ያለውን አፓርታይዳዊ ሥርዓት በህዝባዊ ሱናሚ ኣስወግደን እስክንድርን በፍትሐዊ ምርጫ እንደማንዴላ ለመሪነት ለማብቃትና ቃሊቲ ያሉ ጀግኖቻችንን ነፃ ለማውጣት የማንዴላን ፈልግ እንከተል የሚለው መልዕክቴ በዛሬዋ ዕለት በስደት ከምማቅቅባት ሐገር ይድረሳችሁ ።
ነፍስ ይማር ለታላቁ የአፍሪቃ ብርቅዬ ልጅ ኔልሠን ማንዴላ
ደረጀ በጋሻው
የቀድሞ የአስኳል ጋዜጣ
ዋና አዘጋጅ
ምስራቅ አፍሪቃ