በአ/አ ሀ/ስብከት የተቋማዊ ለውጥ አመራር ጥናታዊ ውይይት ካህናት፣ መምህራን፣ ሰባክያነ ወንጌል፣ የሰንበት ት/ቤት ተወካዮችና ምእመናን ሱታፌያቸውን እንዲያረጋግጡ ተጠየቀ

  • ለጥናታዊ ውይይቱ÷ ካህናት፣ የአብነት መምህራን፣ መዘምራን፣ ሰባክያነ ወንጌል፣ የሰንበት ት/ቤት ተጠሪዎች እና ምእመናን የሚወከሉበት ቁጥር ተወስኗል፡፡
  • የክፍላተ ከተማ ቤተ ክህነት ጽ/ቤቶች÷ ተሳታፊዎቹ በአገልግሎት ድርሻቸው እና በተወሰነላቸው ቁጥር መሠረት መወከላቸውን የማረጋገጥ ሓላፊነት ተጥሎባቸዋል፡፡
  • ሀ/ስብከቱ የተሳትፎ ጥሪ ያስተላለፈበትን ደብዳቤ በማፈንና የተለያዩ ሰበቦችን በመደርደር ጥናታዊ ውይይቱን ለማኮላሸት አሻጥር የሚሠሩ የለውጡ አደናቃፊዎች (አንዳንድ አስተዳዳሪዎችና ጸሐፊዎች) በጥንቃቄ ተለይተዋል፤ በጸጥታ አካሉ የታገዘ ጥብቅ ክትትል እየተደረገባቸው ስለ መኾኑም ተጠቁሟል፡፡
  • ከእነርሱም መካከል፣ የባለሞያ ቡድኑን እንዲያግዙ ሳይገባቸው የተመደቡትና ስለ ጥናቱ ሐሰተኛና የተሳሳተ መረጃ (lies and misinformation) በመንዛት ገዳማትና አድባራትን ለተቃውሞ እየቀሰቀሱ በአፍራሽ የሕዝብ ግንኙነት ሥራ ተጠምደው የቆዩት የቦሌ ደብረ ሳሌም መድኃኔዓለም ካቴድራል ጸሐፊ መ/ር ሰሎሞን በቀለ ይገኙበታል፡፡
  • የክፍላተ ከተማ ቤተ ክህነት ጽ/ቤቶች በግንባር ቀደምነት የማስተባበር ሚና የሚጫወቱበት የገዳማትና አድባራት የተቋማዊ ለውጥ አመራር ጥናታዊ ውይይት በውጤታማው የአራዳ ጉለሌ ክፍለ ከተማ አጥቢያ አብያተ ክርስቲያን ተሳትፎ ነገ ይጀመራል፡፡
  • ለክህነታዊ አገልግሎት ልዩ ትኩረት የተሰጠባቸው የአብያተ ክርስቲያን አምስቱ ደረጃዎችና ተነጻጻሪ መዋቅራቸው፤ የሒሳብ አያያዝ፣ ኦዲትና የልማት ተቋማት ማቋቋሚያና ማስፋፊያ ፖሊሲዎችና መመሪያዎች ተሳታፊዎችን በከፍተኛ ደረጃ እንደሚያወያዩ ይጠበቃል፡፡
  • ‹‹የለውጡ ተቃራኒዎች ጉዳይ አስፈጻሚ ኾነው አሉባልታ የሚነዙና አሻጥር የሚሠሩ አሉ፡፡ አሉባልታውና አሻጥሩ ለውጡን ወደ ኋላ አያስቀረውም፡፡ ችግር የሚፈታው በውይይት ነው፡፡ መመካከር፣ ሙስናን ማጥፋትና መልካም አስተዳደርን ማስፈን አለብን፡፡ ስለዚህ ጥናቱ ከየአብያተ ክርስቲያኑ የሚወከሉ 16፣ 16 ተሳታፊዎች በሚሰጡት ግብአት ከዳበረ በኋላ ትግበራው ይቀጥላል፡፡›› (ብፁዕ አቡነ እስጢፋኖስ)
A.A Diosces Head Office

የአዲስ አበባ ሀ/ስብከት ጽ/ቤት

በአዲስ አበባ ሀ/ስብከት የተቋማዊ ለውጥ አመራር መዋቅር፣ አደረጃጀትና ዝርዝር አሠራር ጥናት ረቂቅ ላይ የተጀመረው የሥርጸትና ግብአት ማሰባሰቢያ መድረክ ከነገ፣ ኅዳር ፳፯ ቀን ፳፻፮ ዓ.ም. አንሥቶ በሦስት ተከታታይ ዙሮች በአጥቢያ አብያተ ክርስቲያን ተወካዮች ደረጃ በሚካሄደው ጥናታዊ ውይይት ይቀጥላል፡፡ የተቋማዊ ለውጡ ዋና መሠረት እንደኾኑ የሚታመንባቸው የሀ/ስብከቱ ገዳማትና አድባራትም ተወካዮቻቸውን በአግባቡ በመላክ ለመዋቅራዊ የአደረጃጀትና አሠራር ጥናት ረቂቁ መዳበርና ተግባራዊነት የድርሻቸውን እንዲወጡ የሱታፌ (አንድነትና መተባበር) ጥሪ ተላልፎላቸዋል፡፡

ሀ/ስብከቱ በክፍላተ ከተማ ቤተ ክህነት ጽ/ቤቶች አማካይነት ባስተላለፈው የሱታፌ ጥሪ፣ ከሀ/ስብከቱ 166/169 ገዳማትና አድባራት ተውጣጥተው በግንዛቤ ማስጨበጫና የግብአት ማሰባሰቢያ ጥናታዊ ውይይቱ ላይ ስለሚሳተፉ አገልጋዮች ውክልናና ብዛት ያስታወቀ ሲኾን የተሳታፊዎች አላላክም በዚኹ አኳኋን እንዲከናወን አሳስቧል፡፡

በሀ/ስብከቱ የጥሪ ደብዳቤ መሠረት ከእያንዳንዱ አጥቢያ ቤተ ክርስቲያን የሚወከሉት ተሳታፊዎች ጠቅላላ ብዛት 16፣ 16 ሲኾን የውክልናቸው ኹኔታም፡-

  • ከቀሳውስት – 1
  • ከዲያቆናት – 1
  • ከመዘምራን – 1
  • ከአብነት መምህራን – 2
  • ከስብከተ ወንጌል – 1
  • ከሰንበት ት/ቤት – 2 (ሰብሳቢና በሰበካ ጉባኤው የሰንበት ት/ቤቱ ተወካይ)
  • ከምእመናን – 4 (የሰበካ ጉባኤ ምክትል ሰብሳቢን ጨምሮ)
  • አስተዳዳሪ፣ ጸሐፊ፣ ሒሳብ ሹም፣ ቁጥጥር – 4

እንደኾነ ተገልጦአል፡፡

አጥቢያ አብያተ ክርስቲያን ከላይ በተመለከተው አኳኋን ተወካዮቻቸውን በአግባቡ ለይተውና መርጠው ዝርዝራቸውን በሰበካ ጉባኤ ስብሰባ በቃለ ጉባኤ ይዘው ከወሰኑ በኋላ ይህንኑ ለጥናታዊ ውይይቱ ከወጣላቸው መርሐ ግብር ሦስት ቀናት በፊት ለየክፍላተ ከተማቸው ቤተ ክህነት ጽ/ቤቶች እንዲያሳውቁ መታዘዛቸው ተዘግቧል፡፡