ቤተ ክርስቲያን ለሳዑዲ ዓረቢያ ተመላሽ ወገኖች 2 ሚልዮን ብር ጊዜያዊ ርዳታ ሰጠች
- ‹‹ስደተኞችን በእንግድነት ተቀብለን እየተከባከብን አኑረናል፤ ሸኝተናል፡፡ እኛ ስደተኞች ኾነን እየተደበደብንና እየተገደልን መገኘት የለብንም፤ አይገባንም›› /ብፁዕ ወቅዱስ ፓትርያርክ አቡነ ማትያስ/
የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን ከሳዑዲ ዓረቢያ በመመለስ ላይ ለሚገኙ ወገኖች ማቋቋሚያ የሚኾን የሁለት ሚልዮን ብር ጊዜያዊ ርዳታ አበረከተች፡፡
ትላንት፣ ኅዳር ፳፬ ቀን ፳፻፮ ዓ.ም. ከቀትር በፊት በመንበረ ፓትርያርክ ጠቅላይ ቤተ ክህነት አዳራሽ በተጠራ ጉባኤ ላይ እንደተገለጸው÷ ረዳኤ ምንዱባን ምስካየ ኅዙናን ቤተ ክርስቲያን ከስደት ተመላሽ የኾኑ ወገኖች ተመልሰው እንዲቋቋሙና ሕይወታቸው በተረጋጋ ኹኔታ እንዲቀጥል፣ ከመጸለይና ከማስተማር ባሻገር የሰብአዊ ርኅራኄ ተግባሩ በመዲናይቱ አዲስ አበባ ሳይወሰን በየአህጉረ ስብከቱ ተጠናክሮ እንዲቀጥል ታደርጋለች፡፡
ተመላሾቹን በቦሌ የስደተኞች ጊዜያዊ መቀበያ ጣቢያ ተገኘተው ማጽናናታቸውን የገለጹት ብፁዕ ወቅዱስ ፓትርያርክ አቡነ ማትያስ፣ የተቻለውን ያህል ረድኤት ከስደት ተመላሽ ለኾኑ ወገኖች መፈጸም እንደሚገባው አሳስበዋል፡፡
የጉባኤው ተሳታፊዎች ለኾኑ የመንበረ ፓትርያርክ ጠቅላይ ቤተ ክህነት መምሪያዎችና ድርጅቶች ሓላፊዎች፣ የአዲስ አበባ ሀ/ስብከት 169 አድባራትና ገዳማት አስተዳዳሪዎችና የጽ/ቤት ሠራተኞች ቅዱስነታቸው እንደተናገሩት፣ ‹‹ባለን አቅም ለወገኖቻችን ቀዳሚ ደራሾች መኾን አለብን፡፡ እኛ ከዚህ እንደተቀበልናቸው ወደየቤታቸው ሲመለሱ ደግሞ አህጉረ ስብከት ሊቀበሏቸውና ሊደግፏቸው ያስፈልጋል፡፡ ስደተኞችን በእንግድነት ተቀብለን እየተከባከብን አኑረናል፤ ሸኝተናል፡፡ እኛ በሰው ሀገር ስደተኞች ኾነን እየተደበደብንና እየተገደልን መገኘት የለብንም፤ አይገባንም፡፡››
ለሳዑዲ ዓረቢያ ከስደት ተመላሽ ወገኖች በትላንትናው ዕለት የተደረገው የሁለት ሚልዮን ብር ጊዜያዊ ርዳታ፡- ከመንበረ ፓትርያርክ ጠቅላይ ቤተ ክህነት ብር 500,000፣ ከአዲስ አበባ ሀ/ስብከት ጽ/ቤት ብር 200,000፣ ከአዲስ አበባ ገዳማትና አድባራት ብር 1.3 ሚልዮን አስተዋፅኦ የተሰበሰበ መኾኑ ተገልጦአል፡፡
አዲሱ የአዲስ አበባ ሀ/ስብከት ዋና ሥራ አስኪያጅ ሊቀ አእላፍ በላይ መኰንን ምደባም በተገለጸበት በዚኹ ጉባኤ ላይ÷ በአዲስ አበባ ሀ/ስብከት የፓትርያርኩ ረዳት ሊቀ ጳጳስ ብፁዕ አቡነ እስጢፋኖስ፣ የጠቅላይ ቤተ ክህነት ጠቅላይ ሥራ አስኪያጅ ብፁዕ አቡነ ማቴዎስና የተባበሩት ዐረብ ኤምሬቶችና ሊባኖስ አህጉረ ስብከት ሊቀ ጳጳስ ብፁዕ አቡነ ድሜጥሮስ ተገኝተዋል፡፡
እስከ አሁን ባለው መረጃ፣ 79 ሺሕ ኢትዮጵያውያንን ወደ አገራቸው ለመመለስ የተቻለ ሲኾን ከተመለሱት ያላነሱ ወገኖች በመካከለኛው ምሥራቅ የተለያዩ አገሮች በከፍተኛ ችግር ላይ እንዳሉ እየተዘገበ ይገኛል፡፡ ለወገን ደራሽ ወገን ነውና በጠቅላይ ቤተ ክህነት፣ በአዲስ አበባ ሀ/ስብከት ጽ/ቤትና በሀ/ስብከቱ አድባራትና ገዳማት እንዲሁም በማኅበረ ቅዱሳን እየተደረጉ ያሉት በአቀባበል የመርዳትና በዘላቂነት የማቋቋም ተግባር በሌሎችም የቤተ ክርስቲያናችን አካላት፣ ገባሬ ሠናይ ድርጅቶችና ዜጎች ተጠናክሮ ሊቀጥል ይገባል፡፡

