የቅርስ ማጥፋትና ከባድ የእምነት ማጉደል ወንጀሎች ተጠርጣሪው አባ ገብረ ኢየሱስ መኰንን ከቅዱስ ላሊበላ ደብር መምህርነት ተነሥተው የእንጦጦ ማርያምን መልአከ ፀሐይነት ተሾሙ፤ በደብሩ ገንዘብ በሚገዛ የመኪና ‹‹ሽልማት›› ለማሰናበት የሚደረገው የጥቅመኞቻቸው ሽር ጉድ የላሊበላ ካህናትና ምእመናንን ከፍተኛ ቁጣ ቀስቅሷል፤ የመኪና ‹‹ሽልማት›› የሙሰኛ አስተዳዳሪዎች ዋነኛ መክበርያ እየኾነ ነው
ለዘጠኝ ዓመታት በአስተዳዳሪነት ከቆዩበት የቅዱስ ላሊበላ ደብር መምህርነት በካህናትና ምእመናን ተቃውሞ ተነሥተው ወደ አዲስ አበባ – እንጦጦ ርእሰ አድባራት መንበረ ፀሐይ ቅድስት ማርያም ቤተ ክርስቲያን የተዛወሩት ‹ተሸላሚው› መምህር ቆሞስ አባ ገብረ ኢየሱስ መኰንን
- ከአስተዳዳሪው ጋራ የጥቅም ግንኙነት ያላቸው የቅ/ላሊበላ ደብር ሰበካ ጉባኤ አባላትና የአስተዳደር ሠራተኞች፣ ለመኪና ‹ሽልማቱ› ከግማሽ ሚልዮን ብር በላይ (በአንዳንድ ምንጮች መረጃ እስከ ብር 800,000) ከደብሩ ካዝና ወጪ ማድረጋቸው ተጠቁሟል፡፡
- ‹‹መነኩሴ ቢሸለም መስቀል እንጂ መኪና ምን ያደርግለታል?›› የሚሉ የቅ/ላሊበላ ደብር ካህናትና ምእመናን፣ ‹‹አባ ገብረ ኢየሱስ በሕግ መጠየቅ እንጂ ሽልማት አይገባቸውም›› በሚል ኅዳር ፲፮ ቀን ፳፻፮ ከቀትር በኋላ ለከተማው ከንቲባ ምሬቱን ገልጦአል፤ ፖሊስ ጣቢያን በአቤቱታ አጨናንቆ ውሏል፡፡ አባ ገብረ ኢየሱስ የመኪና ‹ሽልማቱን› ለመቀበል አሁን ካሉበት አዲስ አበባ ወደ ላሊበላ ተመልሰው በሚገኙበት የሽኝት መርሐ ግብር ላይም ከፍተኛ ተቃውሞውን ለማሰማት ተዘጋጅቷል፡፡
- የመኪና ግዥው ሂደት ወደ አዲስ አበባ በተላኩ የአስተዳዳሪው ጥቅመኞች እየተካሄደ የሚገኘው፣ አባ ገብረ ኢየሱስ የደብሩን ሰበካ ጉባኤና የአስተዳደር ሠራተኞች ሰብስበው ‹‹መሸኛ ይሰጠኝ›› በማለት የ‹መሸኛውን› ገንዘብ መጠን ጠቅሰው መጠየቃቸውን ተከትሎ ነው፡፡ ይህን ለማስፈጸም ‹‹የልደት በዓል አከባበርን በሚመለከት ለመወያየት›› በሚል ሰበብ በደብሩ ምክትል ሰብሳቢና ጸሐፊ አስተባባሪነት በተጠራ የካህናት ጉባኤ ላይ፣ ‹‹ከደብሩ ካዝና ገንዘብ ወጪ ተደርጎ እንድንሸኛቸው ብፁዕ አባታችን ፈቅደዋል›› እየተባለ የተሰበሰበ የተጭበረበረ የካህናት ፊርማ ለሀ/ስብከቱ መቅረቡ ተነግሯል፡፡
- ሀ/ስብከቱ ቀደም ሲል በተፈጸሙ ምዝበራዎች ምክንያት አባ ገብረ ኢየሱስ የደብሩን ሒሳብ እንዳያንቀሳቅሱ አግዷቸው ሳለ፣ ለተባለው የ‹ሽልማት› መኪና ግዥ ከግማሽ ሚልዮን ብር በላይ ገንዘብ ወጪ እንዲኾን መፍቀዱ ብፁዕ ሊቀ ጳጳሱን በከፍተኛ ደረጃ እያስወቀሰ ነው፡፡
- የከተማው ባህልና ቱሪዝም ጽ/ቤት በደብሩ አብያተ መቅደስ ባካሄደው ድንገተኛ የቅርስ ቆጠራ÷ በቤተ ገብርኤል በቅርስነት የተመዘገበው ጥንታዊ የብራና መጽሐፍ ከተመዘገበበት የተለየ ኾኖ ተገኝቷል፤ ከቤተ መርቆሬዎስ በቅርስነት የተመዘገበ ኵስኵስት በቦታው አልተገኘም፤ በዚኹ ቤተ መቅደስ የሚገኝ የወርቅ መስቀልም ስለ መቀየሩ እየተነገረ ነው፡፡ ጽ/ቤቱ ኹኔታውን ለሚመለከተው አካል በሪፖርቱ እንደሚያሳውቅ ተገልጦአል፡፡
- ባለፈው ሳምንት እሑድ የላሊበላ ከተማ ፍትሕ ጽ/ቤት በቅርስ አጠባበቅ ሕግ ነክ ጉዳዮች ላይ ሥልጠና ለመስጠት የደብሩን አስተዳደርና ካህናት በጠራበት ስብሰባ ላይ፣ ስለቅርስ ቆጠራና ርክክብ አስፈላጊነት ሐሳቦች በሚነሡበት ወቅት፣ አባ ገብረ ኢየሱስ አሠልጣኞቹን በተደጋጋሚ ተግሣጽ ለማሸማቀቅ ሲሞክሩ መስተዋላቸው ከጠፉትና ከተቀየሩት ቅርሶች ጋራ በተያያዘ ከፍተኛ የሕዝቡ ጥርጣሬዎች እየተናፈሱባቸው ነው፡፡ ወቅቱ አባ ገብረ ኢየሱስ ከሓላፊነታቸው ከመነሣታቸው ጋራ የተገናኘ ከመኾኑ አንጻር አዲሱ መምህር ጽ/ቤቱን ተረክበው ሥራ ከመጀመራቸው በፊት ጠቅላላ የቅርስ ቆጠራና የደብሩ ገቢዎችና ወጪዎች ኦዲት የማድረግ አስፈላጊነት ከመቼውም ጊዜ በላይ እየተጠየቀ ነው፡፡
- ከቤተ ደናግል በፈለሰ የደንጊያ መንበር እና ከአብያተ መቅደሱ ጋራ በቅርስነት በተመዘገቡ ጎጆ ቤቶች ቃጠሎ ጋራ በተያያዘ የቅርስ ማውደም ከፍተኛ ወንጀል ተጠርጣሪ የኾኑት አባ ገብረ ኢየሱስ÷ በርካታ የልማት ሥራ እንዳከናወኑበት የሚናገሩለትን ደብር የቱሪዝምና ልማት ተቋማት ገቢዎች ግልጽነትና ተጠያቂነት በጎደለው አሠራር በመመዝበር ከባድ የእምነት ማጉደልና በሐሰተኛ ሰነድ ፈጠራ ከፍተኛ ወንጀሎችም ተጠርጣሪ ናቸው፡፡
- ከሐሰተኛ ሰነድ ፈጠራ ጋራ በተያያዘ በተጠረጠሩበት ወንጀል የፖሊስ መጥሪያ የወጣባቸው አባ ገብረ ኢየሱስ፣ የተከሳሽነት ቃላቸውን የሰጡ ሲኾን ፖሊስ ምርመራውን አጠናቅቆና መዝገቡን አደራጅቶ ለከተማው ፍትሕ ጽ/ቤት ዐቃቤ ሕግ ማስተላለፉ ተዘግቧል፡፡ የተጣለባቸውን ሓላፊነት ወደ ጎን በመተው የቤተ ክርስቲያንን ሀብትና ንብረት በመመዝበርና ለግል መበልጸጊያ በማዋል በተጠረጠሩባቸው ከፍተኛ ወንጀሎች ጥፋተኛ ኾነው ከተገኙ ከ10 – 20 ዓመት የሚደርስ እስራትና ጽኑ እስራት ይጠብቃቸዋል፡፡
- በቃለ ዐዋዲው የተወሰነውን የሥራ ዘመን በመፃረር ለስድስት ተከታታይ ዓመታት በሥልጣን ላይ የቆየው የደብሩ ሰበካ ጉባኤ (በተለይ ተተኪውን አስተዳዳሪ ተቀባይነት ለማሳጣት ከወዲኹ እያሳደሙና የሥነ ልቡና ተጽዕኖ የሚፈጥሩ ክፉ ወሬዎችን እያስወሩ ናቸው የተባሉት የምክትል ሰብሳቢውና ጸሐፊው) ኹኔታና ከአስተዳዳሪው ጋራ ከፍተኛ የጥቅም ግንኙነት ያላቸው የደብሩ ሠራተኞች አፈጻጸም በጥልቀት እንዲፈተሽ እየተጠየቀ ነው – ‹‹አዲስ የወይን ጠጅ በአሮጌ አቁማዳ›› እንዳይኾን!!
- በአዲስ መልክ መዋቀር የሚገባው የደብሩ አስተዳደርና ተተኪው መምህር ሊፈጽሟቸው የሚገቡ አምስት የጥንቃቄ ርምጃዎች. . .
ተጨማሪ መረጃዎችን ይከታተሉ